“ሕወሃት ለፖለቲካ ትርፍ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ እያደረገና አፋር ክልል ህዝብ ላይ አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸመ ነው” የአፋር ክልላዊ መንግስት

0
1028

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የሕወሃት ቡድን ለፖለቲካ ትርፍ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ እያደረገ መሆኑን እና አፋር ክልል ህዝብ ላይ አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን የአፋር ክልላዊ መንግስት ገለጸ።

የአፋር ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ሰላም ወዳዱ የአፋር ህዝብ ሁሌም ለሰላም እና ለሰብአዊነት ቅድሚያ በመስጠት የሚታወቅ ህዝብ በመሆኑ ትናንትም ዛሬም ሰብአዊነትን ያስቀደመ ስራ እየሰራ ይገኛል። ይህም በመሆኑ አሸባሪው ህወሀት በአፋር ህዝብ ላይ ከሁለት አመት ተኩል በላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቢፈጽምበትም ለወንድም የትግራይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በርካታ ስራዎች በክልሉ መንግስት በኩል ተሰርተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርም የአለም አቀፍ ድርጅት መሪዎችን ለምሳሌ እንደ WFP እና OCHA ሃላፊዎች ጋር በቅርበት በመስራት ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።

ይሁንና በውሸት እና በሴራ አፉን የፈታው አሸባሪው ህወሀት በአፋር ኪልበቲ ረሱ /ዞን ሁለት/ በተለያያዩ ወረዳዎች ወሰን ጥሶ ገብቶ በንፁሃን አፋሮች ላይ የከፈተውን ጦርነት አስመልክቶ መሰረተ ቢስ የሆነ የተሞላ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው ራስ በራሱ የሚጋጭ በበርካታ ውሸቶች የታጨቀ የአፋርን እና የትግራይ ህዝቦችን በማጋጨት የማይረባ ትርፍን ለማጋበስ ቆርጦ እንደተነሳ በግልፅ ቃላቶች በማሳየት እና የአፋርን መልካም ገጽታ ጥላሸት ለመቀባት በሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ አሰራጭቷል።

ከአሁን በፊት በአፋር ክልል በርካታ ወረዳዎች ወሰን ጥሶ በመግባት በአሰ ዳ፥ በጋሊኮማ፥ በኡዋ፥ በጭፍራ፥ በሀደሌ ኤላ፥ በደርሳ ጊታ እና ሌሎች አካባቢዎች አሰቃቂ የዘር ማጥፋትን (Genocide) ጨምሮ በርካታ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ያደረሰው ቡድኑ “ለሰላም ስል ወጥቻለሁ” የሚል የውሸት ማደናገሪያ ቢነዛም ወሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች እንዲወጣ ቢደረግም በማግስቱ ከታህሳስ 10/2014 ጀምሮ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የደረሰበትን ኪሳራ ለማካካስ እና ለመበቀል በኪልበቲ ረሱ በአብኣላ በኩል እና በተለያዩ ወረዳዎች በኩል ግን ጥቃቶችን አቁሞ አያውቅም።

ይህንንም የሽብር ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃቶች እንዲያቆም የክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ የቆየ ቢሆንም ቡድኑ የከባድ መሳሪያ ወደ ንፁሀን ዜጎች በመተኮስ ንፁሃን ሴቶች፤ ህጻናት እና አዛውንቶችን ህይወት እየቀጠፈ እና ሆስፒታሎች፤ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን ዒላማ ያደረገ የከባድ መሳሪያ ድብደባ በመፈጸም በተቋማቱ የነበሩ ንጹሀን ህይወት እንዲቀጠፍ እና ተቋማት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ አድርጓል።

ከሰሞኑ ደግሞ በተደራጀ መልኩ በአብአላ፥ በመጋሌ፥ ኤረብቲ ወረዳዎችን በመቆጣጠር እና በራህሌ ወረዳንም ከፊል ቀበሌዎች ድረስ ዘልቆ በመግባት ከ150 ኪሎ ሜትሮች በላይ ወደ አፋር ወሰን በመግባት ከባድ ጥቃት ከፍቶ ንፁሀንን በመግደል እና በማሳደድ ወረዳዎቹን እያወደመ ይገኛል። በነዚህ ወረዳዎች ብቻ ጁንታው በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከ220 ሺህ በላይ ንጹሀን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ለህዝብ ሰላም ጭራሽ ግድ የማይሰጠው አሸባሪው ህወሀት ሁለቱ የአፋር እና የትግራይ ህዝቦች እንዲጋጩ ተደጋጋሚ ጦርነት እየከፈተ እና እያሸበረ ቢቀጥልም ለሁለቱ ህዝቦች አንድነት እና ሰላም ሲባል በትዕግስት ቢታለፍም፣ ከሰሞኑ ቡድኑ ሀይሉን አጠናክሮ በመግባት ለሶስተኛ ዙር ህፃናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶችን ያለ ርህራሄ በከባድ መሳሪያ በመጨፍጨፍ አረመኔያዊነቱን ዳግም አሳይቷል።

ጁንታው ባወጣው መግለጫ በአካባቢው ፈጽሞ የሌሉትን “የኤርትራ ወታደሮች እና የቀይ ባህር አፋር” በሚል መሰረተ ቢስ የውሸት ውንጀላ ሽፋን በማድረግ በሌላ አካባቢ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ የአፋር ወሰንን ከ150 ኪሎ ሜትሮች በላይ ዘልቆ በመግባት ንጹሀንን በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛል።

አሸባሪው ቡድን ይህን የተካነበትን የውሸት ዘዴ እየነዛ የሚገኘው ቀድሞውንም እንዳስቀመጡት የአፋርን መሬት በሀይል በመውሰድ እና በዚያውም የትግራይ ሪፐብሊክ መንግስት ለመመስረት ያለው የረዥም ጊዜ ህልምን ለማሳካት መሆኑ ግልጽ ነው።

ለሶስተኛ ጊዜ በንጹሀን አፋሮች ላይ የዘር ማጥፋት ለመፈጸም ቆርጦ የተነሳው ይህ እኩይ ወንበዴ ቡድን በውሸት ፕሮፖጋንዳ የአለምን ህዝብ ለማወናበድ ትንኮሳ እንደተፈጸመበት አስመስሎ ቢያቀርብም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከአፋር በኩልም አንድ ኪሎ ሜትር እንኳን ወደ ትግራይ ወሰን ዘልቆ ያልገባ እና ድሮም ቢሆን ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም ቁርሾ የሌለበት ህዝብ መሆኑ የሚታወቅ እውነታ ነው።

የአፋር ሱልጣኖች፥ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችም ጁንታው በአፋር ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲታቀብ እና ወንድም የትግራይ ህዝብም ይህን ቡድን ሊያስቆመው እንደሚገባ በተደጋጋሚ አሳስቧል።

የክልሉ መንግስትም ጁንታው እንደ አዲስ በኪልበቲ ረሱ አብአላ በኩል ጥቃት ሲከፍት ቡድኑ ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ እና በወንድም የትግራይ እና የአፋር ህዝብ መካከል ቁርሾ በመፍጠር ቡድኑ እድሜውን ለማራዘም የሚያደርገውን ጥቃት እንዲያቆም በተደጋጋሚ ጠይቋል።ይሁንና አሸባሪው ቡድን የክልሉ መንግስት፤ የአፋር ሱልጣኖች፤ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የሚያቀርቡትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አሻፈረኝ በማለት ንጹሀን የክልሉ አርብቶ አደር ማህበረሰብን የጥቃት ሰለባ አድርጓል።

አሸባሪው ቡድን መግለጫ ብሎ በሰጠው የውሸት ተረት ተረት ለአፋር እና ለትግራይ ህዝብ አሳቢ መስሎ የራሱን የሽብር ዕድሜውን ለማራዘም እና ህዝቦችን ለማባላት ባለፉት ሶስት አመታት የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምበት የመጣ ሴራ በመሆኑ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች የሽብር ቡድኑ የሚያሰራጫቸው የውሸት ፕሮፖጋንዳ እና ድራማዎች ሰለባ ሳይሆኑ ከወንድም የአፋር ህዝብ እና መንግስት ጎን በመሆን የትግራይ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና አፈና ጊዜውን ሊያሳጥር ይገባል።

አሸባሪው ቡድን የራሱን እድሜ ከማራዘም ውጭ ጭራሽ ቅንጣት ታክል ለህዝብ ሰብአዊነት የሚሰማው አለመሆኑ የአፋር ንፁሀንን በመግደልና በማሸበር ብቻ ሳይሆን እየገለፀ ያለው፣ ከትግራይ እናቶች ጉያ መንጥቆ የሚያወጣቸውን በጦርነቱ በማሰለፍ እና በኪልበቲ ረሱ በኩል ለትግራይ ህዝብ ይደርስ የነበረውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲስተጓጎል አካባቢው የጦርነት ቀጠና እንዲሆን ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈፀም ነው።

ቡድኑ ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እና የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ እየፈጸመ ካለው የሽብር ተግባር እንዲወጣ የአለም ማህበረሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እና የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን የውሸት ማወናበጃ መግለጫዎችን ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመረዳት እና በመገንዘብ ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ያለውን ድርጊት በቃህ ሊለው ይገባል።

በአካባቢው አንድም የመንግስት ሀይል በሌለበት እና “የኤርትራ ወታደሮች እና ቀይ ባህር አፋር” በሚል በሬ ወለደ ወሬ ሽፋን ንጹሀን ላይ የሚያደርሰውን የጅምላ ጭፍጨፋ እንዲያቆም እና ገብቶ ከነበረባቸው የአፋር ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በአስቸኳይ እንዲያወጣ ሊደረግ ይገባል።

በመጨረሻም የአለም ማህበረሰብ ቡድኑ ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያና ለፖለቲካ ትርፍ መጠቀሚያ ለማዋል ጥረት እያደረገ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል።

ቡድኑም እንደ አዲስ ከገባባቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጣና በቀጠናው የከፈተውን ጦርነት እና ወረራ ሊያቆም የሚገባ ሲሆን የክልሉ መንግስትም ሆነ የአፋር ህዝብ ለትግራይ ህዝብ በቡድኑ ወረራና ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ ይሆናል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ጥር 18/ 2014

ሰመራ

______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here