ዕሮብ ጥር 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አለምአቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ከመስከረም ወር ወዲህ የመጀመሪያውን የህክምና እርዳታ ዛሬ ዕሮብ ጥር 18 ቀን 2014 ወደ ትግራይ ክልል ማድረሱን አስታውቋል።
ኮሚቴው ከባለፈው መስከረም ወር ወዲህ ወደ ትግራይ ክልል የሚያደረገውን ድጋፍ በጦርነቱ ምክንያት አቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ቢሆንም ግን ዛሬ ወደ መቀሌ ከተማ መሰረታዊ የሆኑ የመድሃኒት አቅርቦቶችን ማጓጓዙን በኢትዮጵያ የሚገኘው የኮሚቴው ቅርንጫፍ አስተባባሪው አፖሎ ባራሳ ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው እንዳሉት ከሆነም ወደ ክልሉ የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደርሱ ሲባል፤ ከሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች ጋር ባደረግነው ምክክር መሰረት ድጋፉ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እርዳታዎቹም መቀሌ ከተማ መድረሳቸውን ገልጸው፤ ምንም እንኳን ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በቂ ይሆናሉ ብለን አሁን መናገር ባንችልም ወደፊት ግን መሰል ድጋፎችን ማድረስ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
የአሁኖቹ መድሃኒቶች በክልሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ይደረሳሉ የሚሉት አስተባባሪው፤ ኮሚቴው ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የአማራና አፋር ክልሎችም የመድሃኒት ድጋፎችን እንደሚያደርግም ጠቁሟል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገውን የመድሃኒት ድጋፍ ለማድረግ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር አውስተው፤ በዚሁ የኢትዮጵያ ክፍል መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በርካታ መሆናቸውን ኮሚቴው አስታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



