የእለት ዜና

ታስረው የነበሩ የኦነግ አመራሮች ተፈቱ

ቅዳሜ የካቲት 21/2012 በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች ትላንት እሁድ አመሻሹ ላይ ከእስር የተፈቱ ሲሆን የቀድሞው የኦነግ ጦር አዛዥ የነበሩት እና አሁን የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አብዲ ረጋሳ ግን እስካሁን ያለመፈታታቸውን ፓርቲው አስታውቋል።

የፓርቲው ነባር አባል የሆኑት ለሚ ቤኛ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት አመራሮቹ እሁድ ማታ ታስረው ከቆዩበት በተለምዶ ሶስተኛ ተብሎ ከሚጠራው ፖሊስ ጣቢያ የተፈቱ ሲሆን ‹‹ እንዲሁ ተለቀቁ እንጂ ዋስትናም ጥሩ አልተባሉም›› ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹አብዲ እስካሁን ያሉበትን አናውቅም›› ያሉት ለሚ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ግዜ ጀምሮ ቤተሰብም ሆነ ጠበቃ እንዲያገኛቸው ባለመደረጉ ምክኒያት ፓርቲያቸው ስጋት እንደገባውም ገልፀዋል። ‹‹አብዲ መንግስት እና ፓርቲው ባደረገው ድርድር ከኤርትራ በሰላም ለመታገል የተመለሱ ሲሆን የኦነግ ሰራዊት ዋና አዛዥ የነበሩ ናቸው። ስለዚህ የእሳቸውን ጉዳይ በቀላሉ የምናየው አይደለም›› ሲሉ ለሚ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እሁድ የካቲት 22/2012 ጠዋት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተካሂዶ የነበረው የጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ ጉባኤ ላይ ኦነግ ሳይገኝ መቅረቱን የተናገሩት ለሚ ለዚህም ‹‹አመራሮቻችን ታስረውብን ለማስፈታት እየተሯሯጥን ስለነበር በጉባኤው አልተሳተፍንም›› ብለዋል። ‹‹ጉባኤው መንግስት እና ፓርቲዎች መካከል ውይይት ለማሰለጥ ተጀመረ እንጂ ተቋማዊ አይደለም። አሁን ባlው ሁኔታ ብዙም ለውጥ አይታይበትም፤ ከዚህ በኋላም እያየን ወይ እንሄዳለን ወይ እንቀራለን›› ብለዋል።

‹‹ኦነግ ለጋዲሳው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ነበር አሁንም ይህንን እንቀጥላለን፤ ነገር ግን ተቃውሞ ሲኖረን ተቃውሟችንን እናሰማለን›› ሲሉ ገልፀዋል።

አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦረና፣ ሽጉጥ ገለታ (ዶ/ር)፣ ያዲ አብዱልሽኩር፣ ኬናሳ አያና፣ ተስፋዬ ማኮ፣ አብዱልከሪም አብዱራህማን፣ ሙሄ ራያ፣ ሶሎሞን ተሾመ፣ ደቻሳ ዊርቱ በቁጥጥር ስር ውለው አንደነበር ይታወሳል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com