የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ሳምንታዊ መግለጫ ዋና ዋና ነጥቦች

0
1134

ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በሳምንታዊ መግለጫው ላይ ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦

1. በጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ኢትዮጵያ ደምቃ እንድትታይ ያደረጉ በዓላት
• የገና በአል ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ መከበርን ተከትሎ በጥር ወር የመጀመሪዎቹ ሳምንታት የከተራ፣ የጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ በዓላት በመላ አገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብረዋል።

• በወይብላ ማርያም ከተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ዉጭ ከባድ የፀጥታ ስጋት አለባቸው በሚባሉት እነ ቄለም ወለጋና በዋግ ኸምራ እንዲሁም በሌሎችም ቦታዎች በዓላቱ በሰላምና በድምቀት ተከብረዋል።

በወይብላ ማርያም አካባቢ የተፈጠረዉን ችግር ከፌደራል፣ ከአዲስ አበባና ከአሮሚያ ፖሊስ የተዉጣጣ ግብረ ሃይል ጉዳዩን በዝርዝር እየመረመረ ይገኛል፡፡ የግብረ ሃይሉ የምርመራ ዉጤትም እንደተጠናቀቀ ለህዝቡ የሚገለፅ ይሆናል፡፡

እንዲህ አይነቱ ችግር በዚህ አካባቢ ለሶስተኛ ጊዜ የተከሰተ በመሆኑ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት የአካባቢው አስተዳደር፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች በችግሩ ሥር መሰረት ላይ ተወያይተዉ የመፍትሄ አካል በማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

• በተጨማሪም አዲስ አበባ የታላቁ ሩጫን በደማቅ ቀለማት አስውባ በተሳካ ሁኔታ አስተናግዳለች።

2. የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ
• 35ተኛዉ የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የእንቅስቃሴ ገደብን ተከትሎ ከሁለት ዓመታት በላይ የቆይታ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሪዎች በአካል በመገኘት የሚያካሂዱት ጉባኤ ነው፡፡

• በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት መስፋፋትና በወቅታዊዉ የኢትዮጵያ ሁኔታ ምክንያት ጉባኤው የህብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ እንዳይካሄድ ጫና ሲደረግ ቢቆይም የአፍሪካ መሪዎች ለአፍሪካ ህብረት ህገ መንግስታዊ መርሆዎች ተጓዥ በመሆናቸው፤ ለኢትዮጵያም ካላቸው አጋርነት ተቋርጦ የነበረው ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰኑ ለአገራችን ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው፡፡

ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች በራሷ ፈትታ፤ አንድነቷን ጠብቃ የቀጠለች አገር መሆኗንና ሰላምና መረጋጋቷ የተጠበቀ መሆኑን አጉልተን ለዓለም የምናሳይበት ይሆናል፡፡

• የጉባኤው ተሳታፊዎች ሁሉንም አይነት ዓለም አቀፍ ጫናዎች ወደ ጎን በመተው ጉባኤው በህብረቱ ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸው መሪዎቹን የሚያስመሰግናቸው ነው።

• መላዉ ህዝብ በተለይም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የጉባኤው ተሳታፊዎች ደህንነት እንዲሰማቸው፣ በጎ ትውስታን ይዘው እንዲመለሱ፣ ቤታቸውና አገራቸው ያሉ ያህል እንዲሰማቸው አፍሪካዊ ባህሎች፣ ወጎች፣ እሴቶችን የሚያንፀባርቅ፣ የእንግዳ አቀባበል ሁኔታን በማሳየት ችግሮች ካጋጠሙም ለፀጥታ አካላት በመጠቆም ለጉባኤዉ መሳካት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡

3. መልሶ ግንባታና የበጋ ልማት ስራዎች
• ከወራሪዉ ሃይል ነጻ በወጡ የአማራና የአፋር ክልሎች የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አብዛኞቹ ወደ ተጨባጭ ሥራ ገብተዋል፣ ህብረተሰቡም ወደ ተሟሟቀ የበጋ የግብርና ልማት ሥራዎች በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡ የክልል መንግስታትም የፀጥታ ስጋቶችን ከመቅረፍ ጎን ለጎን ህብረተሰቡን በዘላቂነት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ትኩራት አድርገዉ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በየክልሎቹ በህዝባዊ ንቅናቄ የሚፈፀሙ የተፋሳስ ልማትና የበጋ መስኖ ልማት ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ቀጥለዋል፣

4. የድርቅ አደጋን ለመመከት እየተደረገ ያለዉ ጥረት

• በሱማሌ ክልል በአብዛኞቹ ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል በቦረና፣ በጉጂና በባሌ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ኦሞ ዞን የተወሰኑ ወረዳዎች የመኸርና የበልግ ወቅት ዝናብ ከመደበኛ በታች በመዝነቡና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ምንም ዝናብ ባለመዝነቡ በአካባቢዎቹ ድርቅ ተከስቷል፡፡

• በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች በእንስሳት ሃብት ላይ መጠነኛ ጉዳት እየደረሰ ነዉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስት ከክልል መንግስታት ጋር በመሆን ጊዜያዊ ችግሩን ለማቅለል የእለት ደራሽ እህል፣ የእንስሳት መኖ፣ መድሃኒቶችና ዉሃ እያቀረበ ነዉ። በድጋፍ አቅርቦቱ ህብረተሰቡም ሆነ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ መንግስት ይጠይቃል፡፡

5. የትግራይ ሁኔታን በተመለከተ
• አጋር አካላት ወደ ትግራይ ክልል ለሚኖራቸው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት የአየርና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎትን መንግስት አመቻችቷል፡፡

• ይሁንና ከሠመራ ወደ መቀሌ በአብአላ ኮሪደር የሚደረገው የየብስ ጉዞ ወራሪው ኃይል በተደጋጋሚ በአካባቢዉ የጦርነት ትንኮሳ በመፈፀሙ ተስተጓጉሏል፡፡

ባሳለፍናቸዉ ቀናት ብቻ በርካታ የእርዳታ እህልና መድሃኒት የጫኑ ተሽከሪካሪዎች ወራሪዉ ሃይል በእነዚህ አካባቢዎች በከፈተዉ ጦርነት ምክንያት ብዙ ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ ወደ ኋላ እንዲመለሱ ተገደዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተዉ የሽብር ቡድኑ ዛሬም ረሃብን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ለመጠቀም እየሞከረ መሆኑን ነው፡፡

6. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ
• የሽብር ቡድኑ ሕወሃትና ግብረአበሮቹ በአገራችን ህልውናና ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀናቸዉ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 ፀድቆ በስራ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

• ይህን ተከትሎ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልል የፀጥታ ሀይሎች፣ እንዲሁም መላ የሀገሪቱ ህዝብ በአንድነት ተቀናጅተዉ በተለያዩ የውጊያ ግንባሮች ባደረጉት የጀግንነት ተጋድሎ ቀድሞ የነበረዉ ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑና አሁን ያለውን የጸጥታ ስጋት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥራ መቆጣጠር የሚቻል በመሆኑ፣ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ይህንኑ ውሳኔ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here