የተጨበጠ ነገር ሳይያዝ ፕሮጀክቶችን እጀምራለሁ ማለትን ተለማምዳለች በሚል የምትታማው አዲስ አበባ ከዘጠኝ ዓመት በፊት (2002) እጀምረዋለሁ ያለችውን የከተማ ፈጣን አውቶቡስ መስመር ግንባታ እስካሁን አልጀመረችም።
ይኸው ፕሮጀክት የውሃ ሽታ ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ ከዓመታት በፊት ከፈረንሳይ ልማት ድርጅት (‘ኤኤፍዲ’) የተበደረው የ50 ሚሊዮን ዩሮና በቅርቡ እዳው ወደ 85 ሚሊዮን ዩሮ ያሻቀበው ገንዘብ ወዴት ሔደ የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ ከሚሠራው ፕሮጀክት ሳይሆን ከሚገኘው ብድር ኪሳቸውን ለማድለብ ያለ ፕሮጀክት አዋጭ ጥናት ዘለው ብድር በሚወስዱ የመንግሥት ባለሥልጣናት የእዳ ጫናዋ አናቷ ላይ ስለመውጣቱ የሚናገሩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ቆሞ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
የምን ፈጣን አውቶቡስ ነው?
አዲስ አበባ በ2016 እና በ2032 የምታልመውን የእድገት ደረጃ የሚያሳይ የተንቀሰቀቃሽ ምስል ንድፍ (‘አኒሜሽን’) በማዘጋጀት በ2006 ለመንግሥት ሠራተኞችና ነዋሪውም ጭምር ውይይት እያቀረበች ስለከተማዋ መፃዒ ተስፋ ብሩህነት ስትሰብክ ነበር። በወቅቱ በ‘አኒሜሽኑ’ ምራቁን ሲውጥ የነበረው ተወያይ የበረከተውን ያህል “አይ ኢሕአዴግ ልማዱ ነው፤ ምርጫ (በቀጣዩ ዓመት 2007 ምርጫ እንደነበር ይታወሳል) ሲደርስ ብዙ የማይሳኩ ዕቅዶችን በማቅረብ ቀልብ መግዛት ይወዳል›› በሚልም በውይይት መድረኮቹ ላይ ጥያቄና ትችት እያነሱ ሲሞግቱ፣ በአወያይነት የተሰየሙ የወረዳ ካቢኔዎችም ሲበሳጩ ነበር።
በንድፉ (‘ዲዛይን’) ከተካተቱት መካከል የመስቀል አደባባይ ስፍራ ይጠቀሳል። በስፍራው እንደ ጀት የሚወነጨፉ የከተማ ቀላል ባቡሮች፣ በየደቂቃው ለራሳቸው ብቻ ተለይቶ በተሠራ መንገድ የሚከንፉ ፈጣን አውቶቡሶች፣ ከቀጨኔ በሚወርደው ወንዝ ጀልባና ዓሣዎች ሲምነሸነሹ በየዳርቻውም ሰዎች ቁጭ ብለው ሲያወጉ፣ በብስክሌትም ሲጋልቡ የሚያመለክቱ ትዕይንቶች ታጭቀዋል።
የፈጣን አውቶቡስ መስመሩ እንግዲህ አንዱ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለልና ዘርፉን ለማዘመን ታስበው ከተቀረፁት ፕሮጀክቶች መካከል ነው።
አስተዳደሩ ለዚህም የአዋጭነት ጥናት አካሒዶ ስለጥቅሙ ማረጋገጡንና የንድፍ ቀረፃውን ማጠናቀቁን በመግለጽ ለሕዝብ ይፋ ካደረገ ዓመታት ይቆጠሩ እንጂ እስካሁን የታየ አንድም ሥራ በመሬት የለም።
ግንቦት 27/2006 የፈጣን አውቶቡስ መስመሩን ግንባታ ለማስጀመር የከተማዋ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ የመንገዶች ባለሥልጣን፣ የአንበሳ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅትና ሌሎችም ይመለከታቸዋል የተባሉ ተቋማት መክረው ነበር።
በጊዜውም ፕሮጀክቱ 16 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን፣ ግንባታውም መስከረም 2007 ተጀምሮ በ2009 ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገልጾ ነበር። የወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ስለፕሮጀክቱ አዋጭነት የኹለት ዓመታት ጥናት መካሔዱንና የንድፍ ሥራው መጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል። ከአራት ዓመት በፊት የንድፍ ሥራው መጠናቀቁ በቀድሞው ከንቲባ የተገለጸው ፕሮጀክት ግን የውሃ ሽታ እንደሆነ ቀርቷል።
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በ2010 መጀመሪያ “የ50 ሚሊዮኑን ዩሮ ፕሮጀክት ምን በላው?” ሲል የከተማዋን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ጠይቆ ነበር። እሳቸውም “ግንባታው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መግባት ይቅርና እስካሁንም የንድፍ ሥራው አልተጠናቀቀም” ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት።
ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ስለ ፕሮጀክቱ ምንም የተጨበጠ ነገር ሳይያዝ በሐሳብ ደረጃ ብቻ ባለ ነገር የፈጣን አውቶቡስ መስመር እንገነባለን ሲባል እንደነበርም ገልጸዋል። የሆነው ሆኖ “ብድር የተወሰደበትና ወለድ እየቆጠረበት ያለው ፕሮጀክቱ ዕጣ ፈንታው ምን ይሆን?” የተባሉት ሰለሞን በ2010 መጀመሪያ ላይ የንድፍ ሥራው 55 በመቶ ተጠናቆ እንደነበር ጠቅሰዋል። የአስተደዳሩ ዕቅድም ንድፉን በፍጥነት ጨርሶ የግንባታ ሥራውን 2010 መገባደጃ ወቅት ለመጀመር እንደሆነ ጠቅሰው ነበር። የተባለው ዓመት መገባደጃ ላይ ከጸሐፊው ጋር ዳግም ቃለ ምልልስ የነበራቸው ሰለሞን ንድፉ እየተገባደደ መሆኑን አንስተው የመንገዱ ግንባታ በ2011 መጀመሪያ ላይ ሊጀመር እንደታሰበ ነግረውታል።
ይሁንና የተባለው 2011 ተጋምሶም ፕሮጀክቱም በተግባር መሬት ላይ አልተጀመረም። ከሰሞኑም ቀጠሮ የበዛበትና ከይጀመራል ማለፍ ያልቻለው የፈጣን አውቶቡሰ መስመር “ወዴት አለ?” ስንል አሁን ላይ ከመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊነት በተጨማሪ ከተማዋንም በምክትል ከንቲባነት እያገለገሉ የሚገኙትን ሰለሞን ኪዳኔን (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ አነጋግረናቸዋል።
ሰለሞን ፕሮጀክቱ በተደጋጋሚ ይጀመራል እየተባለ መራዘሙን በመግለፅ ችግሩ መነሻው ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዘጠኝ ዓመት በፊት ይገነባል የተባለው የፈጣን አውቶቡስ መስመር ምንም የተጨበጠ እንዳልነበረውና እስካሁን መጓተቱን ይገልፃሉ።
አሁንስ ምን ላይ ነው?
የፈጣን አውቶቡስ መስመር ዕቅዱ ከዊንጌት አደባባይ ተነስቶ በፓስተር-አውቶቡስ ተራ- አንዋር መስጊድ-ተክለሃይማኖት ጎፋ ገብርኤል አድርጐ ጀርመን አደባባይ ጀሞ የሚደርስ ነው። የመንገዱ አጠቃላይ ርዝመት 17 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ሲሆን ስፋቱም ከ25 እስከ 40 ሜትር የሚደርስ ስለመሆኑ ሰለሞን ይናገራሉ። የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማጠናቀቅ የተያዘው ጊዜም ኹለት ዓመት ነበር።
አስተዳደሩ ፕሮጀክቱን በኹለት ምዕራፍ ከፍሎ እንደሚገነባ በመግለፅ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአስኮ፣ መርካቶ ጎፋ የሚዘልቀውን ስምንት ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት አቅዶም ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰኔ 23/2007 ውሎው “የአዲስ አበባ ፈጣን አውቶቡስ መስመር ግንባታን ለመዘርጋት ከፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ የተገኘውን የ50 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት አፅድቄያለሁ” ሲል ተስማማ። ይህም የተጨበጠ ነገር አልነበረም በሚባልበት ጊዜ የተፈጸመ ሲሆን፣ የቀድሞው ከንቲባ ድሪባ ኩማ ግንባታው መስከረም 2007 ይጀመራል ካሉበት ጊዜ ደግሞ 10 ወራት ዘግይቶ የጸደቀ ነው።
የፕሮጀክቱን የንድፍና የማማከር ሥራ ለመከወን ‘ሳፌጅ’ ከተሰኘ አማካሪ ኩባንያ ጋር ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ውል የተፈረመው ደግሞ ብድሩ በሕዝብ ተወካዮች ከፀደቀ ከ10 ወራት በኋላ መጋቢት 11/2008 ነበር.። ይህ ሁሉ ነገር የሚሳየው “በጨበጣ” የተጀመረ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የሚሉ አሉ።
በኋላም ለፈጣን አውቶቡስ የታሰበው ከመስቀል አደባባይ ወደ ሳሪስ የሚወስደው መስመር በከተማዋ ቀላል ባቡር ግንባታ ምክንያት ተወስዷል።
በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ውስጥ ለሕዝቡ ሳይታይ ዛሬ ላይ የደረሰው የፕሮጀክት ሐሳብ (‘ህልም’) ታዲያ ዛሬስ ምን እየተባለለት ነው ለሚለው ጥያቄ ሰለሞን የፕሮጀክቱ ዋጋ ወደ 85 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ማለቱንና ተጨማሪው 35 ሚሊዮን ዩሮ ከቀድሞው አበዳሪ መገኘቱን ይጠቅሳሉ። ፕሮጀክቱ ዘገየ በሚባልባቸው ዓመታት የተሠራው “ትልቅ የንድፍና አዋጭነት ጥናት” ዋጋውን እንዳሳደገውም አክለዋል።
ከ2005 ጀምሮ አማካሪ ኩባንያ ተቀጥሮ አዋጭነት ሲጠና እንደነበር የሚገልጹት ሰለሞን አሁን የንድፍ ሥራው መጠናቀቁንና ከኹለት ወር በፊት ለግንባታ ጨረታ ወጥቶ እንደነበር ነግረውናል። የወጣው ዓለም ዐቀፍ ጨረታ የተወሰኑ ተቋራጮችን በልምድና አቅማቸው አወዳድሮ የተወሰኑትን ከመረጡ በኋላ መንገዱን ለመሥራት በሚያቀርቡት የገንዘብ መጠን (አነስተኛነት) እንዲወዳደሩ ለማድረግ የሚስችል እንደነበረና ለምርጫ ከቀረቡት ውስጥም የሚፈለገውን የሚያሟሉ ባለመገኘታቸው ጨረታው አለመሳካቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አሁንም ግልፅ ዓለም ዐቀፍ ጨረታ ሊወጣ እየተዘጋጀ መሆኑንና የሚያሟላ ተቋራጭ ከተገኘ የግንባታ ሥራውን በተሟላ አቅም በ2012 ለመጀመር እንደታሰበ አክለዋል። “በየዓመቱ በቀጣዩ ዓመት ይጀመራል እያሉ መሔድ ምን ያክል ታማኝ ይሆናል?” ለሚለው የአዲስ ማለዳ ጥያቄም ሰለሞን “አማካሪው እያጠናው ሲሔድ መነሳት ያለባቸው ተጨማሪ የውሃ መስመሮችና መስፋት ያለባቸው መንገዶች በመገኘታቸው ነው” ይላሉ። የወሰን ማስከበር ሥራው በአብዛኛው መጠናቀቁን በመግለፅ መጪው ክረምት ስለሆነ ትልልቅ ቁፋሮዎች ስለማይደረጉ እንጂ በዓመቱ መጨረሻ ግንባታውን በጥቂቱ የመጀመር ነገር እንደሚኖርም አስረድተዋል።
የማይበደር አገርም የለም የሚሉት ምሁሩ፣ የኢትዮጵያ የፕሮጀክቶች ብድር ችግሩ ፕሮጀክቶቹ ሳይጠኑ የሚፈጸም መሆኑና ፕሮጀክቶቹ ለምተው የሚያስገኙት ገቢ ሳይሆን በብድሩ ሒደት ከመሳተፍ የሚገኝ የሙስና ብር ታላሚ ተደርጎ የሚፈፀም በመሆኑ ነው ይላሉ።
የፕሮጀክቱ መልኮች
እንደ ሰለሞን ማብራሪያ 23 ጣቢዎች (መጫኛና ማውረጃ) ሲኖሩት ሙሉ በሙሉ ቤት ወይም ዋሻ መሳይ ስፍራዎች ውስጥ የሚገነቡ ናቸው። ወደ ጣቢያዎቹ የሚገባው ሰው የከፈለ ብቻ ሲሆን ክፍያው በኤሌክትሮኒክስ ካርድ ይፈፀማል። በመስመሩ እስከ 176 (ትንሽና ትልቅ ሲሆኑ ትልቁ በአንዴ እስከ 170 ሰዎችን የሚጭን ይሆናል) አውቶቡሶች ሲሰማሩ በነዳጅና በኤሌክትሪክ እንዲሠሩ የሚሆኑ ናቸው። የመብራት ችግር እስኪፈታ በነዳጅ ሠርተው አቅርቦቱ ሲስተካከል ወደ ኤሌክልትሪክ ተጠቃሚነት መቀየር የሚችሉ ሆነው ይሠራሉ፣ ባለ ኹለት አቅጣጫ መስመሩም ለዚህ ተስማሚ ሆኖ ይለማል። አውቶቡሶቹ አንድ ጣቢያ ላይ 20 ሰከንድ ብቻ ሲቆም በዚህ ቅፅበት የሚወርደው ወርዶ የሚገባው ይገባል። ሰው እስኪለምድ ግን እስከ ሦስት ደቂቃ ይቆማሉ። አውቶቡሶቹ ከጀሞ ጫፍ እስከ ዊንጌት በ40 ደቂቃ ይፈተለካሉ። “ይህም ከጫፍ ጫፍ በታክሲ ለመሔድ ሰዓታትን ለሚፈጁት አዲስ አበቤዎች ፍቱን ይሆናል” የሚሉት ሰለሞን 170 ሰው የሚጭነው አንድ አውቶቡስ ከሰዓት ማሳጠሩም በላይ በአንድ ዙር ጉዞ ብቻ ከ10 በላይ ሚኒባሶችን እንደሚተካ ያስረዳሉ።
ሰለሞን ይህ ሁሉ ስለተባለለት ፕሮጀክት “የተለየ ነገር ካላጋጠመን በኹለት ዓመት ይጠናቀቃል፣ ቢበዛ በኹለት ዓመት ተኩል አልቆ አገልግሎት ይጀምራል” ብለዋል።
ሐሳብ ይዞ ብድር!
ሰለሞን እንደሚሉት ብድሩ ንድፉንም ለማሠራት አስፈላጊ ነበር። ነገር ግን ሳይሠራ ጊዜ በነጎደ ቁጥር አገር ላይ ጫና እንደሚያሳድርና ተገቢም እንዳልሆነ በመግለጽ የብድሩ ዓይነት የንግድ አለመሆኑና በረጅም ጊዜ የሚከፈል የልማት ብድር በመሆኑ ጫናው ከባድ እንደማይሆን ይገልፃሉ።
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ የብድር ጫናው የሚመጣው በብድሩ ዓይነት ሳይሆን በገንዘቡ መጠንም ጭምር መሆኑን በመግለፅ 50 ሚሊዮን ዩሮው ኢትዮጵያ ካለባት 27 ቢሊዮን ዶላር በላይ እዳ አንፃር ከታየ ትንሽ መሆኑን ያብራራሉ። የማይበደር አገርም የለም የሚሉት ምሁሩ፣ የኢትዮጵያ የፕሮጀክቶች ብድር ችግሩ ፕሮጀክቶቹ ሳይጠኑ የሚፈጸም መሆኑና ፕሮጀክቶቹ ለምተው የሚያስገኙት ገቢ ሳይሆን በብድሩ ሒደት ከመሳተፍ የሚገኝ የሙስና ብር ታላሚ ተደርጎ የሚፈፀም በመሆኑ ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያ የተበደረችው 10 የስኳር ፕሮጀክቶችን አዋጭነት አጥንታ ሳይሆን ሲበደሩ ግለሰቦች በሚያገኙት የሙስና ገንዘብ እንደሆነ በምሳሌ የሚያስረዱት አለማየሁ የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ውልም አይደለም የአማርኛ የእንግሊዘኛ ትርጉም እንኳን እንደሌለው ይልቁንም፣ ውሉ በቻይንኛ የሰፈረና ማንም የማያውቀው እንደሆነ ያክላሉ። በብድር የሚሠሩ ፕሮጀክቶች በዘገዩ ቁጥር ሳይሠሩ የብድር መክፈያ ጊዜው ይደርስባቸዋል፤ ይህም ሌላ ተጨማሪ ወለድ እንዲቆጠር ያደርጋል የሚሉት ምሁሩ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስምርም ይኸው እጣ ፈንታ እንደደረሰውና ጠቅላይ ሚንስትሩን (ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)) የብድር መክፈያ ጊዜው እንዲራዘም እንዲጠይቁ ማስገደዱን ይገልፃሉ።
ፕሮጀክቶች ሳይጠኑ መበደር አገር ላይ ጫና እየፈጠረ ነው፤ ስለዚህም መንግሥት የአዋጭነት ጥናት የሚያደርግ የራሱን አደረጃጀት ሊፈጥር ይገባል፤ ጥናቶቹም በተገቢ ባለሙያዎች መደረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011