‘ቤት የራባቸው’ የአዲስ አበባ ቦታዎች

0
855

በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 9 ለሪል እስቴት ግንባታ የተሰጠና እስካሁን ቤት ሳይገነባበት ያለ 92 ሺ 721 ካሬ ሜትር ቦታ

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ ቤት አልባ የሆኑባት አዲስ አበባ “ጣሪያ የነካውን የቤት ፍላጎት ያቃልሉልኛል” በሚል የቤት አልሚ ኩባንያዎች (‘ሪል ኢስቴት’) ልማትን ከተዋወቀች ዐሥርት ዓመታት አልፈዋል። የቤት ፍላጎቱ ጣሪያ ስለመንካቱና አቅርቦቱ ደግሞ የተገላቢጦሽ መሆኑን በ2005 በ20/80 እና 40/60 ብቻ 960 ሺሕ ሰዎች ቤት ለማግኘት ተመዝግበው እንደሚገኙና ያልተመዘገበው ነዋሪ እንደሚበዛ የከተማዋ አስተዳደርና የፌደራሉ መንግሥት ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር (በወቅቱ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስቴር ይባል የነበረው) በ2008 ያወጣው ሪፖርት በአዲስ አበባ ተመዝግቦ ቤት ለሚጠብቀው ሁሉ በመንግሥት በጀት ገንብቶ የማስረከቡ አቅም እንደማይሆን አመልክቷል። በምክረ ሐሳቡም አዲስ አበባ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ቤት ግንባታ ዘርፍ የተሻለ ተመክሮ አላቸው ከሚባሉት ትግራይና አማራ ክልል ተምራ ዘርፉን ትኩረት እንድትሰጠው አስቀምጧል። የቤት አልሚ ኩባንያዎችን ግንባታንም ችላ ማለቷን ትታ መሬት ከማስተላለፍ ባሻገር በቅርበት እንድትከታተል ይመክራል።

የማኅራትና የቤት አልሚ ኩባንያዎችን ቤት ግንባታ ትኩረት አልነፈኩትም የምትለው አዲስ አበባም በተለይም ከ2000 በፊት በነበሩት ዓመታት ሰፋፊ ቦታዎችን በሊዝ ጨረታና በካቢኔ ውሳኔ የተላለፉትን ጨምሮ በተለያዩ አግባቦች በርካታ ቦታዎችን አስተላልፋለች። ይሁንና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስቴር የአገሪቱን የቤት ልማትና በጀት አጠቃቀም በተመለከተ የስድስት ወራት የግምገማ ውጤትን ለክልል የዘርፍ ባለሥልጣናት በ2009 አጋማሽ ሲያቀርብ ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚያመለክተው ከሆነ በአዲስ አበባ የቤት ግንባታ ላይ ለመሰማራት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው መሬት የወሰዱ አልሚ ኩባንያዎች ቁጥር በርካታ ቢሆንም ምን ያክል ቤት እንደተገነባ እንኳን የከተማ አስተዳሩም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት አኃዛዊ መረጃ የላቸውም። በዚህም ከተላለፉት ቦታዎች ምን ያህሉ ለሙ ምን ያክሉስ ያለ ጥቅም ተቀምጠው ይገኛሉ የሚለውን ለማወቅ እንዳላስቻለ በመጥቀስ ወቀሳውን የሰነዘረው ሰነዱ አስተዳደሩ ሊነቃ እንዲመገባው ይመክራል። ይሁንና እስካሁን የተሠራ ነገር የለም።

በቅርቡ ወደ ሥልጣን የመጣውና በምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የሚመራው የከተማዋ አስተዳደር እርምጃ ከወሰደባቸው መካከል አንዱ ይኸው ዘርፍ ሲሆን ለቤት ማልማት በሚል የተወሰዱ ቦታዎች ምን ላይ ይገኛሉ ሲል ጥናት አካሒዶ የካቲት 6 ለምክትል ከንቲባውና ለካቢኔያቸው አቅርቧል።
ጥናቱ የተካሄደው በቦሌ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ፣ ኮልፌ ቀራኒዮና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች መሆኑ ታውቋል። በከተማዋ 139 ኩባንያዎች በቤት ልማት ለመሰማራት ፍቃድና ቦታ በወስዱም በጥናቱ መሰረት 19ኙ የት እንዳሉ አይታወቅም ወይም በአስተዳደሩ ከዚህ ቀደም በነበሩ እርምጃዎች ሕጋዊነታቸው ተገፍፎ ከዘርፉ ተሰናብተዋል።

ጥናቱ 120 ኩባያዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን ለመገንባት በተረከቧቸው ቦታዎች የመስክ ምልከታ ተደርጎ የተገኘው ውጤት ለምክትል ከንቲባው ቀርቧል። ጥናቱ ግኝቱን በሦስት ዘርፎች የከፋፈላቸው ሲሆን የመጀመሪያው ከፍተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡና ቤት ገንብተው ለመዘገቧቸው ደንበኞች ያስተላለፉትን የሚመለከት ሲሆን ቁጥራቸውም 19 ስለመሆኑ የአጥኚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መለሰ አለቃ ተናግረዋል።

በኹለተኛነት የሚገኙት መካከለኛ የተባሉ ሲሆን እነዚህም በሥራ ላይ ያሉና ግንባታቸው በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ናቸው፤ ቁጥራቸውም 52 ነው።
ሌሎች 29ኙ ደግሞ አፈፃፀማቸው ከ30 በመቶ በታች የሆነና ረጅም ጊዜ ያለሥራ የቆዩና በዝቅተኛ ደረጃ የተቀመጡ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል። በሦስት ደረጃ የተፈረጁት ኩባንያዎች ቁጥር 120 አልሞላም ለሚለው ጥያቄም ሰብሳቢው ሲያብራሩ አንዳንድ ኩባንያዎች የተለያዩ አካባቢዎች (‘ሳይቶች’) ላይ የግንባታ ቦታ ስላላቸው ቁጥሩ ከኩባንያዎቹ እንደሚበልጥ አስገንዝበዋል። ይህን ያዳመጡት ምክትል ከንቲባው “የሠሩትን እናመሰግናለን፤ ያልሰሩትን ደግሞ መሬቱን ነጥቀን ቀድሞም ለቤት ልማት የተላለፉ ቦታዎች ስለሆኑ ለቤት ልማት እንዲውሉ እናስተላልፋለን። ይኼ ነው ውሳኔያችን፥ እንዴትና መቼ ይተላለፉ የሚለውን በዝርዝር እንመክራለን” በማለት የአስተዳደራቸውን አቋምና ውሳኔ ይፋ አድርገዋል። ምክትል ከንቲባው አክለውም የሚነጠቁት ቤቶች በከተማዋ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በኩል ለቤት ልማት እንደሚተላለፉ ነው ያስረዱት።

ይሁንና ከ2009 ጀምሮ የአዳዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን (የ20/80 እና 40/60 ኮንዶሚኒየም) ያቋረጠው የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ቀድሞውኑ በመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት በተረከበው መሬት ላይ ቤት ገንብቶ ሳይጨርስ ተጨማሪ መሬት መስጠቱ ቦታዎቹን ለተጨማሪ ዓመታት ያለሥራ ማስቀመጥ አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄን ያስነሳል። ስለዚህ ጉዳይ የጠየቅናቸው የቢሮ ኃላፊዋ ሰናይት ዳምጠው አቅጣጫቸው ነዋሪው እየተደራጀ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቤትን እንዲገነባ በመሆኑ ቦታዎቹ ወደዚሁ እንደሚዞሩ ለዚህም እየተሰናዱ ስለመሆኑ ገልፀዋል። በጋራ ማኖሪያ ቤት ግንባታ ተመዝግበው ዛሬም ቤት የሚጠባበቁት ከ960 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ዕጣ ፈንታም ወደዚሁ የኅብረት ሥራ ዘርፍ እየተደራጁ መግባት መሆኑም ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት፣ የካቲት 2/2011 ዕትሟ ባስነበበችው ዜና ባንኮች በማኅበራት ተደራጅተው ቤት ለሚገነቡ አዲስ አበቤዎች የረጅም ጊዜ ብድር እንዲሰጡ አስተዳደሩ ሊያግባባ ስለመሆኑ ከምንጮቿ ስለማረጋገጧ መዘገቧ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የኅብረት ሥራ ማደራጃ መመሪያው ቤት ለመገንባት ከሚደራጁ ሰዎች ቅድሚያ 50 በመቶ ቁጠባን እንደሚያስገድድ በመግለጽ ይህም ለተደራጆች አቅም ፈታኝ መሆኑን ማስነበቧ ይታወሳል። ይህን በማንሳት የቤቱን ጥቅል ዋጋ ግማሽ በመቶ ቀድሞ የመቆጠብ አቅሙ ከወዴት ይመጣል ያልናቸው ሰናይት ባንኮች እንዲያግዙ ከማድረግ ባሻገር የማኅበራት ማደራጃ መመሪያው ላይ ያለው የቅድመ ቁጠባ መስፈርት እንደሚሻሻልና በ20/80 ተመዝግቦ የነበረ ኮንዶሚኒየም ተጠባባቂ ወደ ኅብረት ሥራ ቤት ሲዞር 20 በመቶውን ብቻ ቆጥቦ እንዲደራጅና ቤቱን እንዲገነባ እንዲሁም በ40/60 ተመዝግቦ የነበረውም ቅድሚያ 40 በመቶውን ቆጥቦ ወደ ግንባታው እንዲገባ የሚደረግ መሆኑን ነግረውናል።

እንዚህ ቦታዎች ‘ጦማቸውን ሲያድሩ’ አስተዳደሩ የት ነበር?
በጥናቱ መሰረት ዝቅተኛ አፈፃፀም አላቸው የተባሉትና ሊነጠቁ የተወሰነባቸው ኩባንያዎች በአብዛኛው ቦታውን የተረከቡት በ1998 ነው። ኩባንያዎቹ ደግሞ በአጠቃላይ 960 ሺሕ 72 ካሬ ሜትር ቦታ ይዘዋል። ለመሆኑ ይህ ሁሉ ቦታ ያለልማት ዓመታትን ሲቀመጥ አስተዳደሩ ቦታ ከማስተላለፍ ባለፈ ለመከታተል ያልቻለው ምን ሲሠራ ነው ያልናቸው የአዲስ አበባ መሬት ባንክና ማስተላላፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ጥላሁን ጽሕፈት ቤታቸው የተቋቋመው በ2004 እንደሆነና ቦታዎቹ የተሰጡት ከዚያ ቀደም በነበሩ ዓመታት መሆኑን ያስቀድማሉ። በወቅቱም መሬት ላይ የረባ ክትትል እንደማይደረግ ለሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ “እናንተስ ከ2004 ጀምሮ የት ነበራችሁ?” በሚል አዲስ ማለዳ ላነሳችላቸው ጥያቄ አላሠራ ያሏቸው ችግሮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። በማያያዝም ከተሰጣቸው በላይ አስፍቶ ቦታን ከመያዝና ረጅም ዓመታትን ሳያለሙ ከመቆየት ባሻገር ሕጋዊ ፍቃድ ሳይወስዱና የከተማ አስተዳደሩ ሳያውቀው ከግለሰቦች ቦታ እየገዙ የቤት ልማት ሥራ ውስጥ የገቡ ስለመኖራቸው አሁን በተደረገው ጥናት መታወቁን ገልፀዋል።

ያላለሙት እንደሚነጠቁ የሚገልፁት ተስፋዬ መቼ የሚለው ግን በውል የተቆረጠ ቀን እንደሌለው አክለዋል፤ ከ30 በመቶ በታች የገነቡ ምንም ክፍያ ሳይፈጸምላቸው እንደሚነጠቁ፣ በአንፃሩ ከ30 በመቶ በላይ የገነቡ (ኮለን ብቻ ማቆምን ጨምሮ) ደግሞ አስተዳደሩ እስካሁን ላለማልማታቸው ከሚጥልባቸው መቀጮ የሚተርፍ ተመን የሚያወጣ ግንባታን ከሠሩ የተረፈውን የገንዘብ ግምት ወስደው ቦታውን ግን እንደሚነጠቁ ሕግ መቀመጡን አስረድተዋል።
“ፈቃድ ሳይወስዱ እየገነቡ ያሉት በሀብታቸው እየቀለዱ ነው” ሲሉም ከመነጠቅ እንደማይድኑ ተስፋዬ አሳስበዋል።

የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ መለሰ ቦታዎቹ እስካሁን ያለሙበት ምክንያት አንድም በመንግሥት ችግር ሲሆን ኹለተኛው በራሳቸው በአልሚ ኩባንያዎቹ እንደሆነ ገልፀዋል። በመንግሥት በኩል የነበረው ችግር ክትትል ያለማድረግ እና ቦታን ያለማፅዳት (ለአብነት የአቬሽን ክልል ነው በሚል እስካሁን በወሰዱት ቦታ ላይ ቤት እንዳይገነቡ የሆኑ ኩባንያዎች አሉ) እንዲሁም የተናጠል ካርታ ቶሎ ያለመስጠት ይጠቀሳል።

ተደጋጋሚ የውል ማራዘመያ መጠየቅና የንድፍ ማሻሻያ ማድረግ፣ በተሰጠው ፕላንና ውል መሰረት ያለመሥራት ችግሮች ደግሞ በአልሚዎቹ በኩል የታዩ ድክመቶች እንደሆኑ ሰብሳቢው አስረድተዋል።

የመንግሥት ክትትልና መረጃ አያያዝ ደካማ ስለነበረም አሁን የት እንዳሉ ሊታወቁ ያልቻሉ ኩባንያዎችና ለቤት ግንባታ የተሰጡ ቦታዎች መኖራቸውን የጥናት ቡድኑ መረጃ ያስረዳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here