የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2014 ግማሽ ዓመት 21.59 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሰበሰበ

0
936

ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1.9 ሚሊዮን ዶላር አድጓል

የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወር ወስጥ ወደ ውጭ አገራት ከላካቸው የቆዳ ምርቶች 21.59 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ገቢው የተገኘው በኢንስቲትዩቱ ሥር የሚገኙ የተለያዩ ዘርፎች ወደ ውጭ ከላኳቸው ምርቶች መሆኑን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርሃኑ ሰርጀቦ ተናግረዋል። ብርሃኑ አክለውም የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከምርት ስብጥር አንጻር ሲታይ ከቆዳ 14.64 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጫማ 1.8 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቆዳ ጓንት 1.83 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ከቆዳ አልባሳት እና ዕቃዎች 3.31 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ከዕቅድ ጋር ሲነጻጸር በቆዳ 64.4፣ በጫማ 34፣ በቆዳ ጓንት 96.2፣ በቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች 99.3 በመቶ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወር የኤክስፖርት አፈጻጸም ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ1.9 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አሳይቷል ነው የተባለው።

በተያያዘም፣ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወር በጠቅላላ ኢንስቲትዩቱ ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች የሠበሰበው ገቢ 19.7 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ተብራርቷል።

በ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ከዘንድሮው ተመሳሳይ ወቅት ጋር በምርት ዓይነት ዝርዝር ሲነጻጸርም፣ በቆዳ የ2.73፣ በጫማ የ1.16፣ በቆዳ ጓንት 0.24፣ እንዲሁም በቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች 0.54 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አሳይቷል ነው የተባለው።

ብርሃኑ አክለውም፣ በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ የሚገኙ የቆዳና የጫማ ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ ካቆሙ ከዓመት በላይ እንደሆናቸውና በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የቆዳና የቆዳ ዕቃ ፋብሪካዎችም ለወራት ሥራ አቁመው እንደነበር ገልጸዋል።

ሆኖም ግን፣ በጦርነቱ ምክንያት ሥራ ያቆሙ ተቋማት የሚያስከትሉትን ክፍተት ግምት ውስጥ በማስገባት ጎዶሎው እንዲካካስ ለማድረግ የተለያዩ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የቆዳና ሌጦ አቅርቦት ይበልጥ በማጠናከር እና በመሳሰሉት ምትክ ተግባራት የተሻለ ገቢ ሊመዘገብ መቻሉን ነው ዳይሬክተሩ ጨምረው የገለጹት።

ከዚህ በፊት ምርቱ ከሚላክባቸው አገራት በተጨማሪ ሌሎች የገበያ መዳረሻዎች መጨመራቸው፣ በምርምር ሥራዎች የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ምርት የመጠቀምና ወደ ውጭ መላክ መጀመሩ ለተሠበሰበው ገቢ ከፍ ማለት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑ ተብራርቷል።

ምንም እንኳ የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ የስድስት ወር ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ቢያሳይም፣ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያሉ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ሥራ በማቆማቸውና ከእነዚህ አካባቢዎች ይገኝ የነበረው ምርት በመቋረጡ የዘርፉ የውጭ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ከመጉዳቱም ባሻገር፣ በፋብሪካዎቹ ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ ዜጎች ለችግር መዳረጋቸው ተጠቁሟል።

ብርሃኑ አክለውም፣ ቁጥራቸው ቢለያይም በመቀሌ፣ በባህር ዳር እና ኮምቦልቻ ያሉት የቆዳና የጓንት ፋብሪካዎች ባይዘጉ ከዚህ የበለጠ ገቢ ማስመዝገብ ይቻል እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ በተለይም የአፍሪካ እና እስያ አገራትን ትኩረት አድርጎ የውጭ ገበያ የማስፋት ሥራ፣ የኢንዱስትሪዎችና ዩኒቨርስቲዎች አብሮ የመሥራት ሁኔታ እንዲጠናከር የማድረግ እንቅስቃሴ እና የዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ ምርቶች እንዲመረቱ የምርምርና የምርት ልማት ሥራዎች በብዛት የማከናወን ተግባር እየተፈፀሙ መሆናቸውን ብርሃኑ ጠቁመዋል።

ተመሳሳይ ጽሁፎች

ለ10 ዓመት የተጓተተው የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ በ2014 ወደ ፕሮጀክት ትግበራ እንደሚገባ ተገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የቆዳ ኢንዱስትሪው ለማግኘት ካቀደው የውጭ ምንዛሬ ከግማሽ በታች ማሳካቱን አስታወቀ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here