እስከ መቼ ወደጓዳ?

0
899

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን ለማዘጋጀት ሽር ጉድ እየጨረሰች ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊትም አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎችን ለመቀበል በብዙ ስትደክም ነበር። በዚህ መካከል ግን ጎዳናዎቿ ላይ ጥግ ጥግ ይዘው የሚሠሩ ጫማ በመጥረግ፣ ጥቃቅን ሸቀጦችን በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዎች የእንግዶችን መምጣት ተከትለው ለቀናት እንዲነሱ ሲደረጉ ተስተውሏል። አሁን ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን ምክንያት በማድረግ እንደውም ከነአካቴው እንዲነሱ የተደረጉ መኖራቸው እየተሰማ ነው። ምንም እንኳ ‹የምትሠሩበትን አማራጭ አዘጋጅተንላችኋል ተብለዋል› ቢባልም፤ መቅደስ ቹቹ ይህን መነሻ በማድረግ እስከ መቼ ሸሽጎ ይቻላል ስትል ትጠይቃለች፤ የመፍትሄ ሐሳብ ያለችውንም አቅርባለች።

መገናኛ አካባቢ መሄጃና መምጫ፤ መመላሻ መንገዴ ነው። እንደውም እንደማንኛውም የአዲስ አበባ ነዋሪ መገናኛን ሳልረግጥ አላልፍም ብል፤ የአካባቢውን ግርግርና የሕዝብ መጨናነቅ ከገለጸልኝ እንደማጋነን አይቆጠርም ብዬ አስባለሁ። ግርግሩ ለጉድ ነው! በዛ አካባቢ ታድያ ብዙ ጊዜ ደንብ አስከባሪዎች ወፈር ያለ ዱላ ይዘው ‹ሕገወጥ› የሚባሉ ነጋዴዎችን ሲያሳድዱ መመልከት እንግዳ ጉዳይ አይደለም።

በአንጻሩ መኪና ይዘው ‹እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ› የሚል ሙዚቃ ከፍተው ድምጽ የሚበክሉና የሚለምነኑ እንዲሁም በርከት ብለው የሚታዩ የኔቢጤዎች ላይ ምንም አስተያየት አይሰጡም። አንድ ጊዜ ታድያ ጠየቅኩኝ፤ ‹ሥራ የሚሠራውን ወጣት ከማባረር ይልቅ የሚለምኑትን ቦታ ቦታ ማስያዝ አይሻልም ወይ? የሚሠራውን እያባረራችሁ ቁጭ ብሎ እየለመነ ብር የሚሰበስበውን ዝም ማለትስ አግባብ ነው ወይ?› አልኩኝ።

በዚህ ጥያቄ የኮነነኝ አለ። እርግጥ ነው የቸገረው ወጥቶ እርዳታ ሊጠይቅ ወይም ሊለምን ይችላል። እናም አይባልም ተባልኩኝ። አይባልም የተባልኩት ‹የኔቢጤው በፈጣሪው ስም ለምኖ ይደርበት፣ የምን መመቅኘት ነው? ይህን ፈጣሪም አይወደውም!› ከሚል ነጥብ አንጻር ነው። የእኔ ጉዳይ ግን ይህ ሳይሆን ‹ሕገወጥ› ቢባሉም ሥራ እየሠሩ ያሉትስ ምን በልተው ይደሩ? ለምኖ አዳሪውን ዐይተው ‹ሠርቶ ከመብላት ለምኖ ማደር ይሻላል!› ብለው በልመና ይሰማሩ ወይ?

በእርግጥ ተሯሩጠው የሚነግዱት እነዛ ወጣቶችም እንደ እኔ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ አይመስለኝም። ለየኔቢጤው ያዝናሉ እንጂ ‹እነሱን ሳትነኩ እኛን ለምን ታባርራላችሁ?› አይሉም። ምንአልባት እኔም ታሬ ልኮነን ሳይገባኝ አይቀረም!
ነገሩን ግን በዚህ ቁንጽል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ጠቅለል አድርገን ለማየት ስንሞክር፤ ይህን ጉዳይ በሚመለከት መንግሥት ብዙ ጊዜ የፈሰሰን ውሃ ለማፈስ ጥረት የሚያደርግ አካል ሆኖ ይታየኛል። ከምንጩ ማድረቅና መከላከል የሚችላቸውን ሕገወጥ ንግዶች መሀል ከተማ ገብተው መንገድ እስኪዘጉ ድረስ ይጠብቃል። ወደ ከተማ የሚደርግ ፍልሰትን አጥንቶ መላ ከማበጀት ይልቅ በድንገቴ ‹መንገድ ላይ እንዳላያችሁ!› ያውጃል።

ይህን ነጥብ ያስታወሰኝ ጉዳይ በቅርቡ የሆነውና አሁንም እየሆነ ያለው ነገር ነው። እንደሚታወቀው የ2014 የገና በዓልን አጋጣሚ በማድረግ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው እንዲመጡ ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር። እነዚህን ዜጎች ለመቀበልም አዲስ አበባ ስትኳኳል ቆየች። ግዙፍና ትልልቅ ሆቴሎች ‹እንኳን ወደ ቤታችሁ ደኅና መጣችሁ› ብለው ማስታወቂያ ሰቅለው ጥሪ እንዲያቀርቡና እንዲጠሩ ተፈቀደላቸው። ድርጅቶች የዛን ሰሞን በየመግለጫው ‹ለዳያስፖራው ይህን አዘጋጅተናል፤ አኛ ጋር ኑ!› እያሉ ድግስ አዘጋጁ።

የከተማ አስተዳደሩም ታድያ በበኩሉ በየክፍለ ከተማው በኩል የራሱን ዝግጅት ለማድረግ በየጎዳናው የሚሠሩ፣ በደሳሳ ላስቲክና ሸራ ስር ሆነው ጫማ የሚያጸዱና ሶፍትና ውሃ የሚሸጡ ልጆችን ‹አንዴ እንግዳ ሊመጣ ስለሆነ መንገድ ላይ አትታዩ! እንግዶች ሲሄድ ሥራ ትጀምራላችሁ!› ብሎ አስነሳቸው። ለሆቴሎች እንጂ ለለፊው ሠርቶ አደር ከዳያስፖራው አንድም ይሁን ዐስር ብር ማግኘት ከነውር የተቆጠረ ይመስላል።

የሚገርመውኮ እንግዳ ሆነው የሚመጡት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያ የሆኑ ዜጎች አገራቸው በድህነት ውስጥ እንዳለች ያውቃሉ። እንደውም መምጣታቸውኮ አንድም ከተፈጠረው ወቅታዊ ቀውስና መፈናቀል አንጻር ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው።

እነዚህ ሰዎች አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ እንድትሆን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችንና አሁንም ያሉ ችግሮችን ለመረዳት የሚያንሱ አይደሉም። መቼም በበጋው መምጣታቸው በጀ እንጂ ጥሪው ለቡሄ ቢሆን ኖሮ፣ ዝናባማው የክረምት ወቅት ይመሰክር ነበር። ዳያስፖራው አስፋልት ለመሻገር አዛይና አሻጋሪ ሲጠራ፣ ጎዳና መንገዱ አባጣና ጎርባጣ እንዳለው ያለነጋሪ ያውቅ ነበር። አሁንም ማኅበራዊ ሚድያ ይህን ችግርና እንከን አልደበቀውም።

ታድያ ከመንገድ ላይ ሊስትሮውንና ለፍቶ አዳሪውን ሁሉ ማንሳት ምን የሚሉት ነው? በድህነት ውስጥ መገኘታችን ግልጽ ጉዳይ ነው። እውነቱ አዲስ አበባን ለማልማት እየተሠራ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ የእለት ጉርሱን በእለት ሥራው ላይ ያደረገውን ሰው በማባረር የሚመጣ አይደለም። ባይሆን ጉዳዩን ከስር ጀምሮ አጥንቶ ምንጩ ላይ ማስተካከልና መፍትሄ መፈለግ፣ መመካከር ነው ወሳኙ ተግባር።

ይህ የዳያስፖራን መምጣት ተከትሎ የተስተዋለ ጉዳይ ታድያ በዚሁ በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ላይ መዘገቡን አስታውሳለሁ። ብዙዎችም በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ነገሩን በማንሳት ማዘናቸውን ሳይገልጹ አልቀሩም። ግን ለውጥ የለም! የባሰ አታምጣ እንደሚባለው አሁን ደግሞ አፍሪካ ኅብረት ስብሰባ መጣ። እንግዲህ ለቤተኛው ተደበቁ የተባሉት ለጎረቤቶች መምጣት ደግሞ ጭራሽ ወንበራችሁ ሁላ እንዳይታይ ተባሉ። ይቀመጡባቸው የነበሩ ድንጋዮች ሳይቀር ተነስተው እንዲሸሸጉ ተደረገ።

‹ሌላ ቦታ እንሰጣችኋለን! ትደራጃላችሁ!› የተባሉ አሉ። እነዚህ ሰዎች በዚህ ገቢ ላይ መሠረት አድርገውና በየእለትም ያንን ተስፋ በማድረግ ኑሮአቸውን የሚገፉ ናቸው። እንዲህ በየአጋጣሚው ‹ተነሱ!› እያሉ እንዲማረሩ ማድረግ ተገቢ አይደለም። አገር ደሃ የምትባለው የደሃ ሕዝቦቿን መጠን ተከትሎ ነው። ሕዝብ ሠርቶ፣ መንግሥትም አስተባብሮ ካልበረቱ በቀር በድህነት ውስጥ መዝለቅ የማይቀር ነው።

እናም በድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን በየአፍታው ‹ዞር በሉ! አትታዩ!› ማለት መፍትሄ አይሆንም። ‹እያወቅን ምን አስደበቃቸው! ለማያውቅሽ ታጠኝ!› ዓይነት ተረት ነው የሚያስተርትብን። ይልቁንም እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ከድህነት ማላቀቅ ሲችሉ ነውና አገርም በሂደትና በዚህ ጥርቅም እድገት የምታመጣው፣ ነገሩን ልብ ማለትና ማጤን ያሻል።

እንዲህ ያሉ እርምጃዎችም ሌብነትንና ዝርፊያን የሚያባብሱ ናቸው። ሥራ ማጣትና ተስፋ መቁረጥ፣ ምሬትና ጥላቻ ወደ ዝርፊያ ያመራሉ። ቀላል በሚመስል ኪስ ማውለቅ የተጀመረ ስርቆት አሁን በመኪና አግቶ እስከመዝረፍ ዘልቋል። አስቡት! መኪና ተከራይቶ ዝርፊያ! ዘራፊው ሁሉ ሠርቶ የሚበላበት እድል ያጣ ነው ብሎ ለሌባ ለመከራከር አይደለም፤ ነገር ግን ሥራ ያጣ ልመና ካወጣ በቀር በዝርፊያ ውስጥ ከተገኘ እንግዳ ሊሆን እንደማይገባ ለመጠቆም ነው።

ሠራተኞችን እንዲህ በየአጋጣሚው ተነሱ ብሎ ከሥራ ቦታቸው ማፈናቀል በእጅጉ የሚያሳዝን ድርጊት ነው። እንዳልኩት የማንክዳቸው እውነቶች አሉ። አዲስ አበባ የሁሉም መናኽሪያ ናት። አሳማኝ በሆነ አልያም ባልሆነ ምክንያት ‹ብር ይታፈስባታል› በሚል ብዙዎች ፈልሰው ይገኙባታል። የሁሉም ከተማ እንደመሆኗ የምትገፋው የለም። ነገር ግን ሁሉ በስርዓት ሊሆን ስለሚገባ ጉዳዩን ከምንጩ በማጥራት ፍልሰቱን መከታተል የአስተዳደሯ ድርሻ ነው።

በተለያየ የዋና መንገዶች ላይ የሚገኙ በድንጋይ ወንበርና በሸራ ጣሪያ ጫማ በመጥረግና ጥቃቅን ነገሮችን በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ ባሉበት ክፍለ ከተማ ወይም ወረዳ የሚታወቁ ናቸው። ‹አሁን ምን ልንሆን ነው?› ብለው ግራ እንዲጋቡ መተው የለባቸውም።

ለምሳሌ ቀላሉ መንገድ እነዚህ በመንገድ ላይ ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች የሚሠሩበትን አካባቢ በጥንቃቄ እንዲይዙ ማድረግ አንዱ ነው። እንዲሁም ዘመናዊ የጫማ መጥረጊያና ጀብሎ መሸጫ ቦታዎችን እንዲያመቻቹ ማደራጀትና ማስቻልም ጥሩ አማራጭ ነው። እንደምናውቀው በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ የሚሠሩ አሉ። ለእነርሱ ሥራ በሚፈጥር መልኩ መንገድ ላይ ያሉ ድንጋይ ወንበሮችን በዘመናዊ ወንበሮችና መጠለያዎች መተካት ይቻላል።

ይህን በማድረግ በአንድ በኩል ቋሚና ለዕይታ የማይረብሹ መልኮችን መፍጠር ይቻላል። በሌላ በኩል አገልግሎቱም ሳይጓል ይቆያል። ይህ ትንሽ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። የተወሰኑ ትስስሮችን መፍጠር ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ይህን ደግሞ የወረዳና የክፍለ ከተማ አስተዳደሮች ከላይ ቀድሞ ካልተጨበጨበና የምስጋና ቀብድ ካልበላን አናደርገውም ካላሉ በቀር፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ሊያከናውኑት የሚችሉት ቀላሉ ተግባር ነው።

ይህ እኔ እንደ ጨዋና ነገሩ ስሜቱን እንደረበሸበት ሰው የምሰጠው ሐሳብ ነው። በተጓዳኝ የበሰሉና የተሸሉ ሐሳቦችን ሊያነሱ የሚችሉ ባለሞያዎችና ሥራ ፈጣሪዎች እንደሚኖሩ አልጠራጠርም። በተረፈ ግን መንገዶችን በዚህ መልኩ ‹ማጽዳት› አይቻልም። እንጦጦ ላይ ትልቅ ፕሮጀክት ሲታሰብ እንጨት ተሸክመው የሚያድሩ እናቶች እንዳልተዘነጉ ሁሉ፣ አዲስ አበባም እንግዳ ሲመጣባት ሠርቶ አዳሪዋን ተደበቁ ከማለትና ወደጓዳ ከመሸሸግ የተሻለ መፍትሄ ሊኖር ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here