የድሃ ቅንጡ ከመሆን ይሰውረን!

0
438

አገራችን ኢትዮጵያ በፀጋ የታደለች ብትሆንም፣ በቁሳዊ ሀብት ግን ድሃ የምትባል ያልበለፀገች አገር መሆኗ አይካድም። ሀብታም እንደሚባሉት አገራት ያሻትን ማድረግ የማትችል፣ የእነሱን እጅ እያየች የምትኖር አቅመ ደካማ አገር እንድትሆን የተፈረደባት ናት።

ድሃ መሆን የሚያስነውር ባይሆንም፣ እንድናፍርበትና አንገታችንን እንድንደፋ የሚያደርጉን ዜጎቻችንም ቢሆኑ ከጎናችንና ከበላያችን አሉ። መስሎ ለማደር ሲሉ ተለቅተው፣ ተበድረውና ለምነው የሚገኘውን ገንዘብ ለቅንጡ ተግባራት ሲያውሉ ማየት እየተለመደ ነው። ይህ ዓይነት መቀናጣት ከቃል ውግዘት ባለፈ ቅጣትም ሆነ ሌላ አስተማሪ ማስተካከያ ዕርምጃ ስላልተወሰደበት አሁንም ድረስ እየተባባሰ እንደቀጠለ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በድሃ አገር ገንዘብ ሀብታሞቹ እንኳን የማያደርጉትን ማድረግ እንደዘመናዊነት፣ እንደመሻሻልና ገፅታ ግንባታ አድርጎ ማቅረብ ፋሽን ሆኗል። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገራችን የብድር መጠን ጣሪያ እየነካ፣ ትውልዱ የሚከፍለው ዕዳ እየተቆለለ፣ በአንፃሩ ለሀብታምና ለባለሥልጣናቱ ምቾት ሲባል በቅንጡ ሁኔታ የሚሠሩና የሚገዙ ነገሮች በዝተዋል።

በፊት በፊት ውድ ቪ8 መኪኖች ለባለሥልጣናት አላግባብ ስለተገዙ ከተማ ውስጥ እንዳያገለግሉ ተብሎ ሌላ ተጨማሪ ወጪ ተደርጎ ውድ መኪና ቢገዛላቸውም፣ ኹለቱንም ሳይመልሱ እያፈራረቁ ከነቤተሰቦቻቸው እንደሚጠቀሙበት ይነገራል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት አመራሮች ለራሳቸው ቅንጡ የሆኑ መኪናዎችን እየገዙ፣ “ውድ አይደለም” እያሉ የሌላ መሥሪያ ቤት አመራሮች ያደረጉትን የተጋነነ ግዢ ማነፃፀሪያ በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብን ወጪ ያደርጋሉ። ጉምሩክ ቅንጡ መኪኖች ናቸው ብሎ ‹ኤክሳይዝ ታክስ› የሚያስከፍልባቸውን መኪኖች፣ በድሃ አገር ገንዘብ እየገዙ ራሳቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ለመካድ ሲሞክሩ ማየት ከማነጋገር ባለፈ ዕርምጃ አላስወሰደም።

ይህ የቅንጡ መኪኖች ግዢ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ለቢሮ ዕቃዎችም ሆነ መገልገያ ቁሳቁሶች የሚወጣው፣ እንዲሁም ለስብሰባና ጉብኝት የሚታረፉባቸው ሆቴሎች በጣም የተጋነነ ወጪ የሚወጣባቸው የሀብታሞች መዝናኛ መሆናቸው ይታያል። ቻይናን የመሳሰሉ ሀብታም አገራት እንኳን ባለሥልጣናቶቻቸው ለመሰብሰብ ሲፈልጉ ከባለ ሦስት ኮከብ ሆቴል በላይ እንዳይጠቀሙ፣ ግዢያቸውም የተጋነነ እንዳይሆን በማገድ ነው ከድህነት ወጥተው አሁን ወዳሉበት የስኬት ማማ የደረሱት።

ኢትዮጵያ ጥንት ድሃ በማትባልበት ጊዜ መሪዎች ከሕዝቡ እንዳይለዩ ሲባል ውድና የተቀናጣ ተግባር ላይ ሲሳተፉ እምብዛም አይታይም ነበር። አብዛኛው ምርት አገራችን የሚመረትና ውድ ያልሆነ ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱም ስለነበረ ያን ያህል አገርን የሚጎዳ ተግባራትን ሹመኞችም ሆኑ ሀብታም ግለሰቦች አያደርጉም ነበር ይባላል።

ካለፉት ጥቂት ዐሥርት ዓመታት ወዲህ ግን ለመዘመን በሚል ዕሳቤ ስልጡን መስሎ ለመታየት የሚደረገው እሽቅድምድም፣ “ውስጡን ለቄስ” እንደሚባለው ውጭ ውጩን ለመምሰል በሚደረግ ጥረት አገሪቷን ለከፍተኛ ወጪ ዳርጓል። እንግሊዝን የመሳሰሉ ሀብታም አገራት እንኳን፣ ነገስታቶቻቸው ከነቤተሰቦቻቸው በአገር ውስጥ የሚመረትን ተመሳሳይ ምርት ከውጭ እንዲገዙ አይፈቀድላቸውም። ቅንጡ የሆኑ የውጭ ግዢዎችንም ሆነ መዝናናቶችን እንዳይፈፅሙ የሚያግድ ሕግ እንዳላቸውም ይነገራል። ይህ ዓይነት ገዳቢ መመሪያም ሆነ ሕግ በድሃ አገራችንም እንዲኖረንና ተፈፃሚ እንዲሆን መሠራት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።

በአገራችን ኢትዮጵያ ኹሉም ያማረውን እየገዛ በቅንጦት እንዳይኖር ሕግ ብቻ ሳይሆን ሕሊናችንም ሊያግደን ይገባል። አብዛኛው ከተሜ የሚያገኘው ገቢ በደሞዝ የሚከፈለው ወይም አትርፎ የሚያገኘው እንደሆነ ይታወቃል። መንግሥት ከሚያገኘው ግብር ላይ የሚከፍላቸው የመኖራቸውን ያህል፣ የገበሬውንና አርብቶ አደሩን ያህል ሀብትን በራሳቸው አምርተው በመገበር ለሕዝብ አሌንታ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሉም። ከውጭ ከሚገባው በስተቀር የአብዛኛው ገቢ ከእነሱ ምርት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ነጋዴው የሚያተርፈው ዞሮ ዞሮ ለእነሱ በሚያቀርበው ላይ እንደሆነ ልንረዳ ያስፈልጋል። የአንበሳውን ድርሻ ማለት በሚያስችል መልኩ ለከፍተኛ ግብር ምንጭ በመሆንም የአገሪቱን የመንግሥት ተቀጣሪ የሚያንቀሳቅሱት እነሱ ናቸው ለማለት ያስደፍራል።

ከማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች የሚገኝ ገቢ ቢኖርም፣ ከልፋታቸውም ሆነ ከብዛታቸው አኳያ እንደአርሶና አርብቶ አደሮቹ ለአገር ባለውለታ የሆነ የለም። ታዲያ የእነሱ ኑሮ ካለፈው ሺሕ ዘመን አኗኗር እምብዛም ሳይለይ፣ የባለሥልጣኖቻችን ውሎ ግን ጣሪያ ቀዶ መውጣት አልነበረበትም። ድሃው ካለበት ችግር እንዲወጣና አገሪቷንም ከአቅመቢስነት እንዲያላቅቅ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ሲገባ፣ ከፍተኛ የቅንጡ ዕቃዎችን በመግዛትም ሆነ የተጋነነ ውድ ሕንፃ በመገንባት ጥቂቶች እንዲጠቀሙበት በማድረግ ሥር ነቀል ለውጥ እንደማይመጣ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

የውጭ አገር ኑሮን የለመዱ ባለሥልጣኖች፣ የለመዱትን ምቾት በዙሪያቸው ብቻ ለማምጣት ብለው የድሃውን ሕዝብ ሀብት ቅድሚያ ተጠቅመው እስከልጅ ልጆቹ የማይከፍለው ዕዳ ትተውለት ወደለመዱት ቅንጡ ሕይወትና አገር መመለሳቸው ላይቀር ይችላል። ይበልጥ ድሃ የተደረገው ሕዝብ ግን ችግሩ ተጭኖት እያለ፣ ከፍሎ የማይጠቀምበትንም ሆነ የማይፈቀድለትን በእሱ ሀብት ስም እየተገነባም ሆነ እየታደሰ ሲመለከት ከርሟል።

ይህ የቆየ የመንግሥት አሠራርም ሆነ ልማድ በቀላሉ የሚቀረፍ ባይመስልም፣ ቢያንስ ፍላጎቱ ያላቸው ባለሥልጣናት ቢኖሩ ለመቀነስ ይቀል ነበር። ይህ ዓይነት የተጋነነ አሠራርን እንዲያስቀር የተቋቋመ የመንግሥት ኦዲት ቢሮ፣ በአመራሮች ከዓመታት በፊት ያጋጠመውን ማስታወስ ይጠቅማል። “ባለሥልጣን ተሹሞ ይመጣላችኋል፤ አዲስ የቢሮ ዕቃ ግዙለት” ተብለው በከፍተኛ ወጪ የአመራሩን ቢሮ ጨምሮ ለእንግዳ መቀበያ የሚሆኑ በርካታ የቢሮ ዕቃዎች ይገዛሉ። የተባለው ባለሥልጣን ግን ይቀራል። የተወሰኑ ጊዜያት ካለፉ በኋላ ሌላ አዲስ ሰው ስለተሾመ ሙሉ ቢሮው ለእሱ በሚሆን ዕቃ ተገዝቶ ይተካ ተብሎ፣ ተገዝቶ የነበረው ላስቲኩ ያልተነሳ አዲስ ምንም ያላገለገለ ዕቃ በሙሉ ወደአንድ ክፍል ገብቶ እንዲታሸግ ተደርጎ፣ ለኹለተኛ ጊዜ አዳዲስ ውድ ዕቃ እንዲገዛ መደረጉን ሁኔታውን በትዝብት የተመለከቱ ኃላፊዎች ተናግረው ነበር።

እንዲህ ዓይነት በእንዝህላልነት የሚደረጉ ግዢዎች ሳይቀረፉ፣ ግዙፍ ወጪ የተደረገባቸው ተግባራትም በተመሳሳይ ከድሃዋ አገራችን ላይ እንደሚመዘበር ይፋ ተደርጎ ነበር። ሜቴክ ያለጨረታ ሥራ በመስጠት ከፍተኛ ሀብት አባክኗል ተብሎ በሚከሰስበት ወቅት፣ የለገኃሩ ፕሮጀክት ያለምንም ውድድር ለውጭ አገር ባለሀብቶች መሠጠቱ ይወሳል። የእንጦጦው፣ የመስቀል አደባባዩ፣ የምኒልክ ቤተ-መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎችና ዕድሳቶች፣ እንዲሁም ከፍተኛ ሀብት የሚወጣባቸው ሥራዎች በዘፈቀደ ያለጨረታ እየተሠጡ የአገር ገቢ አላግባብ መውጣቱ ይሰማ ከጀመረ ቆይቷል። በእነዚህ ውሱን አገልግሎት መስጪያዎች የመስተንግዶ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቀድላቸው የንግድ ተቋማትም ሕጋዊ ባልሆነ አሠራር በትውውቅ ዕድሉ እንደሚሰጣቸው ይወራል።

ለግንባታዎቹ የሚውለው ገንዘብ ከውጭ የተገኘ ነው እየተባለ ማስተባባያውን ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ለማሠራጨት ቢሞከርም፣ ስጦታ ለአገር መሪ እንኳን ያለ ሕግ ስለማይሰጥና በሕዝብ ስም የተገኘ እስከሆነ ድረስ ተጠያቂ እንደሚያደርግ የታወቀ አይመስልም። አዲስ ማለዳ በእንዲህ ዐይነት ግንባታዎችም ሆነ ዕድሳቶች ላይ የተሳተፉም ሆኑ ገንዘብ የሰጡና የተቀበሉ ፣እንዲሁም የተከፈላቸውን አጠቃላይ ገንዘብም ሆነ ወጪው ከነሒደቱ በአስቸኳይ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት ትላለች።

አንድ ግዙፍ አዲስ ሕንፃን የሚሠራ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን፣ መዘጋጃን ለማደስ ወጪ ተደረገ ብሎ ለማውራት መንግሥት ማፈር የነበረበት ቢሆንም አላደረገውም። ድሃው የሚበላውና የሚኖርበት እያጣ በሚሰቃይበት አገር፣ ይህን ያህል ወጪ አወጣን ተብሎ መደስኮሩ ተገቢ ሊሆን የሚችልበት አሳማኝ ምክንያት አይኖርም። አፍ ሞልቶ፣ “ሕንፃው የታደሰው በባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ደረጃ ነው” የማለት ድፍረት መኖር አልነበረበትም። ባለሥልጣናት የሚኖሩበትም ሆነ የሚሠሩበት ቦታ ቆሻሻ ወይም የተበላሸ ይሁን ማለት ሳይሆን፣ ከአብዛኛው ሕዝብ ያልተለየና ያልተቀናጣ መሆን እንዳበት መታመን ይኖርበታል።

“የምትለብሰው የላት የምትከናነበው አማራት” እንደሚባለው ራሳችንን በምግብ ችለን መኖር ያልቻልን ሰዎች፣ “ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ” እያልን የምንንቀባረርበት ሕዝብ ሊኖር አይገባም። ድህነታችንና ውስጣችን ለማንም ግልጽ በሆነበት ዘመን፣ ጥቂቱ ብቻ መስሎ እንዲታይ ማድረግ ይበልጥ ገጽታችንን እንደሚያበላሸው ልናውቅ ይገባል። የዘነጠም ሆነ የወፈረ ችግረኛ ሰው ሲለምነን የመስጠታችንም ሆነ የማገዛችን አጋጣሚ ዝቅተኛ እንደመሆኑ፣ በድጋፍና በግድ አስገብረን ባገኘነው ገቢ መንቀባረር እንደማይገባን አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here