በአማራ ክልል 42 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 869 ባለሀብቶች ፈቃድ ተሠጠ

0
797

በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ብቻ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶች በጦርነቱ ወድመዋል

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በስድስት ወር ውስጥ ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 869 ባለሀብቶች፣ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን ገለጸ።

በ2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ፣ 42.2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደተሠጡ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይኸነው አለም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ባለሀብቶቹ ፈቃድ በተሠጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሥራ ሲጀምሩ፣ ለሥራ አጥ ዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ነው ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አያይዘውም፣ ባለሀብቶቹ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ሥራ ሲጀምሩ ከ78 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ማሳተፍ ይችላሉ የሚል ተስፋ እንደተጣለ ነው ያብራሩት።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሠጣጡ በአብዛኛው ትኩረት ያደረገው በአግሮ ፕሮሰሲንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ማኑፋክቸሪንግ፣ እንስሳት ልማት፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ እንዲሁም ሌሎች መሠል ዘርፎች እንደሚገኙበት ይኸነው ጨምረው አስረድተዋል።

የኢንቨስመንት ፈቃዱ የመሬት ስፋት በተለያዩ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፕሮጀክቶች ላይ ተከፋፍሎ ተቀምጧል ያሉት ይኸነው፣ ለጊዜው ትክክለኛውን ቁጥር ማስታወስ ባይችሉም ለ869 ባለሃብቶቹ የተፈቀደው የኢንቨስትመንት መሬት ብዙ ሔክታር እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የስድስት ወር የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሆነ ቅናሽ እንዳሳየ ኃላፊው አልደበቁም። አያይዘውም፣ የ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የኢቨስትመንት ፈቃድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በባለሀብቶቹም ቁጥር ሆነ ባስመዘገቡት ካፒታል ያሳየውን ዝቅተኛነት ለማነጻጸር እንደማያስደፍር አስረድተዋል።

ለኢንቨስትመንቱ ዝቅተኛነት በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ዋነኛ ምክንያትም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ለተከታታይ ወራት በሠነዘረው ጥቃት የክልሉ ማኅበረሰቦች ቤታቸውን ዘግተው ተፈናቅለው መቆየታቸው መሆኑን ነው ኃላፊው የገለጹት።

የህውሓት ቡድን በሠነዘረው ጥቃት በደሴና በኮምቦልቻ ከተማ ብቻ በርካታ ፕሮጀክቶች መውደማቸውን አዲስ ማለዳ ከኃላፊው ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በተደረገው ጥናት፣ በደሴና በኮምቦልቻ ከተማ ብቻ በጦርነቱ ከ200 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መውደማቸውን የሚናገሩት ኃላፊው፣ በሌሎች የጦርነቱ ቀጠና በነበሩ በርካታ ሥፍራዎች የሚደረገው ጥናት ሲጠቃለል ቁጥሩ ከዚህም በላይ ያለጥርጥር እንደሚያሻቅብ አመላክተዋል።

በደረሰው ውድመት በርካታ ዜጎች ከሥራ መፈናቀላቸውና የውጭ ምንዛሬ መታጣቱ በኢንቨስትመንቱ ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳስከተለ ተመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ በጦርነቱ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ አነቃቅቶ ከተከሠተው ችግር ለመውጣት በባለሀብት፣ በከተማ አስተዳደር፣ በክልል፣ እንዲሁም በፌደራል ደረጃ መሻሻል የሚገባቸውን መመሪያዎች ለማሻሻል ሰሞኑን በደሴ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የተጎዱ ባለሀብቶችንና ከሥራ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀደመ ሥራቸው ለመመለስ የደረሰውን ውድመት ለመገምገም በጀመሩት እንቅስቃሴ ሕዝቡም፣ ባለሀብቱም፣ መንግሥትም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በ2012 በጀት ዓመት 153 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 42 ሺሕ 908 ባለሀብቶች ፈቃድ ሠጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥም 291 የሚሆኑት ባለሀብቶች ብቻ ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወሳል። ኢንቨስትመንቶቹ ለ395 ሺሕ 804 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ናቸው።

ተመሳሳይ ጽሁፎች

በጦርነቱ ምክንያት ያልታረሱ ማሳዎች የሚያስከትሉት የምርት ማሽቆልቆል – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በአማራ ክልል በኹለት ጥብቅ ሥፍራዎች ብቻ ከ367 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወድሟል ተባለ (addismaleda.com)

ጥቃት እና ውድመት የተደጋገመባት ከተማ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here