ሐሙስ ጥር 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍራካ ህብረት የመሪዎች የአካል ስብሰባ ቀደም ብሎ የሚካሄደው የአባል አገራቱ 40 ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናንትናው ዕለት መጀመሩ ይታወሳል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ደመቀ መኮንን ጉባኤውን ለመታደም ለተገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የዲኘሎማቲክ ማህበረብ አባላት በትናንትናው ዕለት ምሽቱን የእራት ግብዣ አድርገዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ደመቀ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና አንዳንድ አገራት ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካውያን እገዛ ነው ብለዋል።
አክለውም የተቀናጀውን የአንዳንድ አለምአቀፍ ተቋማት እና አገራት ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በአፍሪካውያን ወንድማዊ ድጋፍ ማሸነፍ መቻሉን የገለፁ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተጠርቶ የነበረው የጄኔቫው ጉባኤ የዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተው፤ ልዩ ጉባኤው የአንድም አፍሪካ አገርን ድጋፍ እንዳላገኘ በንግግራቸው በመግለፅ የአፍሪካውያን ምን ያህል ከኢትዮጵያ ጎን እንደቆሙ አሳይተዋል።
ደመቀ በንግግራቸው ኢትዮጵያዊያን በድምፃቸው መንግስታቸውን መምረጣቸውን አስታውሰው፣ ተመራጩ መንግስት ከቀደሙት በተለየ በካቢኔው ውስጥ ተቃዋሚዎችን ማቀፉን ጠቅሰዋል።
አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደች ሲሆን በቅርቡ በእስር ላይ የሚገኙ የፓለቲካ ሰዎችን መፍታቷን አንስተዋል።
በተግዳሮቶችም ውስጥ ሆና ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ እየጣረች እንደምትገኝ ያመለከቱ ሲሆን፤ ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ህደሴ ግድብን እንደ አንድ ማሳያ ጠቅሰዋል።
ተለዋዋጭ በሆነው አለምአቀፍ ጉዳዮች አፍራካ ተገቢ ስፍራ እንዲኖራት ብዙ መሰራት እንዳለበት የጠቀሱትን ፤ደመቀ ለዚህም ስኬት ኢትዮጵያ አብዝታ እንደምትሰራ ማስገንዘባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የተባበረች እና የበለፀገች አፍሪካ እውን እንድትሆን ሁሉም የህብረቱ አባል አገር እንዲተባበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጨምረው በንግግራቸው ጥሪ አቅርበዋል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






