“የምዕራቡን ኮሪደር ለመጠበቅ እስከ ደማችን ጠብታ ድረስ እንዋጋለን” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

0
938

አርብ ጥር 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የምዕራቡ ኮሪደር ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማጥፋት በቅንጅት እየሠሩበት ያለ ኮሪደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህንን ኮሪደር ለመጠበቅ እስከ ደማችን ጠብታ ድረስ እንዋጋለን ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሁመራ አየር ማረፊያ በተካሄደው የሰሜን ምዕራብ እዝ የሜዳሊያ ሽልማትና የማዕረግ ማልበስ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት የሽብር ቡድኑ የምዕራቡን ኮሪደር ለማስከፈት እየተደንደረ ነው ብለዋል፡፡

“ከዚህ በፊት ጁንታው ለስምንተኛ ጊዜ ተሳሰቷል“ ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፣ አሁንም የምዕራቡን ኮሪደር ለማስከፈትና ለዘጠነኛ ጊዜ ለመሳሳት እየተንደረደረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የምዕራቡ ኮሪደር ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማጥፋት በቅንጅት እየሠሩበት ያለ ኮሪደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህንን ኮሪደር ለመጠበቅ እስከ ደማችን ጠብታ ድረስ እንዋጋለን ሲሉም ፊልድ ማርሻሉ አመላክተዋል፡፡

ይህን ኮሪደር ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ፊልድ ማርሻሉ ፣ ለዘጠነኛ ጊዜ ህወሃት ስህተት ከሠራ የቡድኑ ማክተሚያ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ድረስ እየተዋጋ ምርጥ ጦር መገንባት የቻለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ብቻ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ አሁን ላይ አገሩን የሚወድና የተሰናዳ ሠራዊት ለመገንባት ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በአፍሪካ ከተቻለ አንደኛ ወይንም ሁለተኛ ደረጃ ሠራዊትን ለመገንባት፣ ካልተቻለ ግን ከሦሥተኛ ደረጃ ያላነሰ ሠራዊትን ለመገንባት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ያመላከቱት ጠቅላይ ኤታማጆር ሹሙ፣ ለወታደሩ የተሰጠው ሽልማት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ሁሉም ሠራዊት ተገንዝቦ አገሩን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለመጠበቅ በተጠንቀቅ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሜዳሊያ ሽልማቱና በማዕረግ ማልበስ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ጄኔራል ጌታቸው የአገራቸውን ታሪክ በአመዛኙ የጦርነት ታሪክ ነው ሲሉ ተናግረው፣ በዚህም አባቶቻችን ጠላትን ደምስሰው ታሪክ ሠርተዋል፣ አሁን የምንኖርባትን ኢትዮጵያን አስረክበውናል፣ አባቶቻችን ያስረከቡንን አገር እኛም የአባቶቻችንን ገድል በመድገም ጠላትን ደምስሰን ለልጆቻችን ታሪክ እናስቀምጣለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ አገር የተጋረጠብን አደጋ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በጋራ በመቀናጀት የፈጠሩት ነው ያሉት ጄኔራል ጌታቸው፣ ኢትዮጵያም ይህን በመረዳት የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ለመመከትና ለማንኮታኮት ዝግጅት ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

ጠላት የፈጸመብን በደል በዚህ ዓለም ታይቶ አይታወቅም ያሉት ጄኔራሉ፣ ጠላት የፈጸመው ክህደት ወላጅ ልጁን ወልዶ ልጁን እንደመብላት ዓይነት ነው ብለዋል፡፡

ይህ ሽልማትና እውቅና የመጀመሪያችን እንጂ የመጨረሻችን አይደለም ያሉት ጄኔራሉ፣ ሽልማቱ ወደፊት ጀግኖችን ለመፍጠር የተቀመጠ የመሠረት ድንጋይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጠላቶቻችን የሚፈልጉት ትንንሽ አጀንዳዎችን እየሰጡን እኛን በትንንሽ አጀንዳዎቻቸው እያናከሱ እኛን ትንሽ ማድረግ ነው ሲሉ የተናገሩት ጄኔራሉ፣ ይህን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተገንዝቦ እንደ ከዚህ ቀደሙ አንድነቱን ጠብቆ መቆም አለበት ብለዋል፡፡

የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም የደቡብ ጎንደር ሕዝብና አስተዳደር፣የሰሜን ወሎ ሕዝብና አስተዳደር በጋሸና ግንባር ለነበራቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

በሁመራ አየር ማረፊያ በተካሄደው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የማዕረግ ማልበስና የሜዳሊያ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በተገኙበት ወታደራዊ ትርኢቶች ተካሂደዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here