በቤሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሽ ዞን የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት ወንጀል በፈፅሙ ተከሳሾች ላይ እስከ 18 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ተወሰነባቸው

0
964
ሐሙስ ጥር 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በቤሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሽ ዞን የእርስ በእርስ ጦርነት በማስነሳት ወንጀል ፈፅመው ዐቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው ተከሳሾች እስከ 18 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ እንደተወሰነባቸው ተገለጸ።
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾች የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)(ሀ)(ለ)፣35 :38 ፣240(2)(3)(4)፣ 539(1)(ሀ)፣ እና 555 (ሀ) ሥር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፋቸው ነበር ክስ ሊመሰረትባቸው የቻለው፡፡
ተከሳሾች ከየካቲት ወር 2010 ጀምሮ እስከ መስከረም ወር 2011 ባሉት ጊዜያት ውስጥ የካማሽ ዞን አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎችን መሳሪያ በማስታጠቅ ወይም አንዱ ህዝብ በሌላው ህዝብ ላይ የጦር መሳርያ አንስቶ በህዝቡ ደህንነት እና ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንዲያስከትል ለማድረግ በማሰብ ተንቀሳቅሰዋል ተብሏ።
በዚህም በቤሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሽ ዞን መደበኛና ልዩ ሃይል ፖሊሶችን ሰብስበው የካማሽ ዞን ወደ ኦሮሚያ ክልል ሊካለል ስለሆነ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ከካማሽ ከተማ ጀምሮ እስከ ጎጥ ያሉትን ኦሮሞዎች ግደሉ በማለትና “ጋሸላ” የተባለ ህገ ወጥ ቡድን በማደራጀት፤ የእኛ ወጣቶችና አመራሮች በኦሮሚያ ተገለዋል ስለዚህ በግምጃ ቤት ያለውን የጦር መሳርያ ለወጣቶችና ለሚሊሻዎች አስታጥቁ በማለት ገንዘብና መመርያ በመስጠት በአጠቃላይ ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌላ መዝገብ ከሚታይ ሌሎች በርካታ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በህብረት በመሆን በመንግስት ላይ በማደምና በማሳደም እንዲሁም፦
• 194 ንፁሀን ሰዎች በቀስትና በጥይት እንዲገደሉ
• በ28 ግለሰቦች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት አንዲደርስ
• 83 ሺህ 269 ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉና
• 27 ሚሊየን 483 ሺህ 300 ብር ግምት ያለው ንብረት አንዲወድም እና ጉዳት እንዲደርስበት በማድረግ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በመሳተፍ በመንግስት ላይ በሚደረግ ወንጀል፣ በከባድ የሰው ግድያና በከባድ የንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን በፈፀሟቸወ ወንጀሎች በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸዋል ።
ዐቃቤ ህግ ከወንጀል ምርመራው አንስቶ ክስ መስርቶ ሲከራከር አንዲሁም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሶሳና አካባቢው 1ኛ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎትም ጉዳዩን ሲመለከት ከቆየ በኋላ በዐቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው 21 ተከሳሾች ውስጥ 11 (አስራ አንዱ) ላይ እንደየ ወንጀል ተሳትፏቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲያሳለፍ 10 (አስር) ተከሳሾችን ደግሞ ወንጀላቸውን መርምሮ በነፃ አሰናብቷል።
ችሎቱ ጥር 24/2014 ባስቻለው ችሎት ጥፋተኛ በተባሉት ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም መሰረት ደሳለኝ ደረሰና ታደሰ ኩኩ የተባሉት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት፣ ዘካርያስ ገለታ በ16 ዓመት፣ ደረጀ ልጅማን፣ ወርቁ ኩሜና ተፈሪ ነጋዋ የተባሉት 3 ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ከ8 ወር፣ አስናቀ ዲንቃ የተባለው ተከሳሽ በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲወሰን ሃይላይ ግደይ የተባለው ተከሳሽ በ9 ወር ቀላል እስራት አንዲቀጣ ችሎቱ መወሰኑን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here