በኢትዮጵያ የኤርፖርት ላውንጅ የአገልግሎት ደረጃን ለማሳደግ ሥምምነት ተደረገ

0
285

በኤርፖርት የመንገደኞች መስተንግዶ አገልግሎት ከዓለም ቀዳሚ የሆነው ፕላዛ ፕሪሚየም ግሩፕ እና በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጉዞ ንግድ እና መስተንግዶ ዘርፍ ግንባር ቀደም የሆነው ኤን.ኤች.ዋይ መካከል በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያለውን የተጓዦች አቀባበል እና የላውንጅ አገልግሎት ደረጃን እንደሚያሳድግ ዕምነት የተጣለበት የሽርክና አጋርነት ሥምምነት ተደረገ።

ፕላዛ ፕሪሚየም ላውንጅ ኢትዮጵያ፣ በተያዘው ዓመት መጋቢት ወር በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በተርሚናል ኹለት የሚከፈት ይሆናል ነው የተባለው።

ይህ አዲስ የተመሠረተ የሽርክና አጋርነትም የፕላዛ ፕሪሚየም ግሩፕን የ24 ዓመታት የላቀ ልምድ እና የኤን.ኤች.ዋይን የአገር ውስጥ የእንግዳ መስተንግዶ ልምድ በማዋሃድ በአየር ማረፊያ ውስጥ ያለውን የመንገደኞች አቀባበል እና የላውንጅ አገልግሎት ደረጃን የበለጠ ለማዘመን ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በ1000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፕላዛ ፕሪሚየም ላውንጅ ኢትዮጵያ፣ በአንድ ጊዜ ለ325 እንግዶች ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ መስተንግዶ ለመስጠት እንዲያስችል ታልሞ መደራጀቱና በዚህም መሠረት የተለያዩ ተጓዦችን ታላሚ ያደረጉ በርካታ አማራጮችንም ይዞ መቅረቡ ታውቋል።

በመሆኑም፣ ዓለም አቀፍ ተጓዦች ወደ መዳረሻቸው ከመሔዳቸው በፊት አረፍ የሚሉበት እና የሚገለገሉበት የተሟላ የቢዝነስ ማዕከል፣ የገላ መታጠቢያ እና ማረፊያ ክፍሎች፣ የሲጋራ ማጨሻ ላውንጅ፣ ካፌ እና ሬስቶራንት የያዘ እንደሆነም ተመላክቷል።

እንዲሁም ላውንጁ ባህልን መሰረት ባደረገ ዲዛይን እና ልዩ በሆነ የኢትዮጵያ ምግብ አሠራር ደምበኞቹን ምቹ ተሞክሮ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታቅዶ የተሠናዳ ነው ተብሏል።

ኤን.ኤች.ዋይ ከ20 ዓመት በፊት በድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኑር ሁሴን የተመሠረተ ሲሆን፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ብራንዶች ጋር አጋርነት በመፍጠር ቀዳሚ አስመጪ እና አከፋፋይ ሆኖ የቆየ መሆኑ ተመልክቷል።

ፕላዛ ፕሪሚየም ግሩፕም እንዲሁ፣ በዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች የመስተንግዶ አቀባበል አገልግሎት እና ፋሲሊቲዎች በመፍጠር ጉዞን የተሻለ ማድረግን ተልዕኮው በማድረግ በ1990 የተመሠረተ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ ዋና ቢሮውን በኾንግኮንግ በማድረግ፣ ኤርፖርት ላውንጅ ፕላዛ ፕሪሚየም፣ ፕላዛ ፕሪሚየም ላውንጅ፣ ኤርፖርት ተርሚናል ኤሮቴል ሆቴሎች እና የመሳሰሉትን፣ በዋናነት አራት የቢዝነስ ክፍሎችን በጋራ አጠቃሎ የያዘ መሆኑ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here