ከሥራ የታገዱ የአዲስ አበባ ሊስትሮዎች እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

0
729

ርብቃ ወልደኪዳን ይባላሉ። በአዲስ አበባ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመስቀል አደባባይ ወደ መገናኛ በሚወስደፈው ጎዳና ባምቢስ መሻገሪያ ላይ በሊስትሮ (ጫማ በማጽዳት) ሥራ ከተሠማሩ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

ርብቃ ለድፍን ዘጠኝ ዓመታት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት ከሊስትሮ ሥራ በሚያገኙት ገቢ ነው። ባለቤታቸው ‹‹የሚጥል በሽታ›› ስላለባቸው የቤቱን አስቤዛ የማሟላት፣ ልጆችን የማስተማር፣ እንዲሁም የቤት ኪራይ የመክፈል ግደታ ኑሮ በሳቸው ላይ ጥሎባቸዋል። ግለሰቧ ቤተሰብን ለማስተዳደሩ የተሠጣቸውን ኃላፊነት በሊስትሮ ሥራ ከሚገኝ ገቢ ለመምራ ትግል እንደሆነባቸው በመዲናዋ ከሚስተዋለው ሰማይ ጠቀስ የኑሮ ውድነት ጋር በማነጻጸር ይናገራሉ።

ያሳለፉትንና ያሉበትን ሁኔታ ለመናገር ሲሞክሩ እንባቸው ንግግራቸውን ቀድሞ ሲፈስ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

አሁን ላይ በአጼ ቴዎድሮስ ትምህርት ቤት የሦስተኛ ክፍል ትምህርቱን በመከታተል ላይ ያለው የመጀመሪያ ልጃቸው ሚኪያስ ደሳለኝን ሲወልዱ፣ የሊስትሮ ሥራቸው እንዳይቋረጥ የከፈሉት መስዋዕትነት የሕይወት ዘመን አይረሴና ፈታኝ ታሪካቸው መሆኑን ደጋግመው ያወሳሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው፡- በወለዱበት ወቅት የቤቱን አስቤዛ የሚያሟላ ሌላ አካል ማግኘት አልተቻለም ነበር። ርብቃ ጨቅላ ሕጻናቸውን ለመመገብ ቅድሚያ ራሳቸው መመገብ ቢኖርባቸውም፣ የቤቱ አስቤዛ ሥራ ሲያቆሙ አብሮ ተመናምኖ አብቅቷል። በዚህ ወቅት አራስነትና ርሃብ በአንድ ቤት ጣሪያ ውስጥ ተፋጠጡ አሉ።

ይህ በእንዲህ እያለ ርብቃ አንድ ሐሳብ መጣላቸው። የተለመደውን የሊስትሮ ሥራቸውን ለመሥራት በምጥ የመነመነ ወገባቸውን አደግድገው መነሳት እንዳለባቸው ወሰኑ።

ቢሆንም ግን፣ ርብቃን ሌላ ችግር ከፊታቸው ተደቀነባቸው። ተደራቢው ችግር ልጃቸውን የሚጠብቅላቸው ሰው ማጣታቸው ነው። ጨቅላ ሕጻን ታቅፌ ርሃብ ልሙት ወይስ መንገድ ዳር ይዠ ልውጣ? ለራሳቸው የጠየቁት ጥያቄ ነበር። እንደ ገለጻቸው ከሆነ፣ በወቅቱ መፈጠርን ወደ መጥላት ደረጃ ደርሰው ነበር። ይህም መፍትሔ እንደማያመጣ ብዙ ጊዜ ሳያጠፉ ገባቸው። ልጃቸውን ይዘው ጎዳና ዳር በመቀመጥ የተቋረጠ የሊስትሮ ሥራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አመኑ።

ውሳኔያቸውን ወደተግባር የቀየሩት ርብቃ፣ መንገድ ዳር የሊስትሮ ዕቃቸውን ዘርግተው፣ ልጃቸውን ጎን በጎን በተጠጋገነ ካርቶን ውስጥ አስተኝተው እየዋሉ መግባት እንደጀመሩ አልደበቁም።

ልጃቸው መጥባት በፈለገበት ሰዓት ጫማ አስጠራጊዎች ይመጣሉ። ሥራ ለመሥራት በሚነሱበት ወቅት ጡቱን ሲነጥቁት ሕጻኑ ያለቅሳል። አንዳንዶቹ ጫማ አስጠራጊዎች፣ በቅንነት “ከንፈራቸውን በመምጠጥ አጥቢው እንጠብቅሻለን” ሲሉ፣ አንዳንዶቹ “ጊዜ የለኝም” በማለት “ፈጠን አድርጊው” የሚል ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ።

ልጃቸው ከተቀመጠበት የካርቶን መጋረጃ በመግባት ጋደም ብለው በሚያጠቡበት ወቅት በጎዳናው ሲያልፉ የሚመለከቷቸው ሌላኛዎቹ ሰዎች ደግሞ “እዚህ የታመመ ሰው አለ” በማለት ድቃቂ ሳንቲም ጥለውላቸው እንደሚያልፉ ርብቃ ያስታውሳሉ።

በእንደዚህ ዓይነት ኹኔታ መኖር ቀጥሎ ዘመናት ተሸኝተዋል። ልጃቸውም አድጎ ትምህርት ቤት ገብቶ አሁን የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ለመሆን እንደበቃ የሚናገሩት ርብቃ፣ ይህን ሲናገሩ በእንባ ረጥቦ የነበረው ጉንጫቸው የደስታ ጭላጭልን ሲላበስ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

የሆነው ሆነና ርብቃ ካሳለፉት የሕይወት ውጣ ውረድ ይልቅ አሁን ላይ ያሉበት ኹኔታ ይበልጥ ከባድ እንደሆነባቸው አልሸሸጉም። የተለመደና ያሳደጋቸውን ሥራቸውን እንዳይሠሩ በመታገዳቸው ከሊስትሮ ሥራ የሚያገኙት ገቢ ተቋርጧል። ከሥራ ከታገዱ ወር እያስቆጠሩ ሲሆን፤ ቡርሾችን፣ ወንበሮችንና የጫማ ቀለሞችን ደንብ አስከባሪዎች እንደነጠቋቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከቂርቆስ ወረዳ የመጡ ሰዎች “እዚህ መሥራት አትችሉም ተነሱ” እንዳሏቸው በማዘን የሚናገሩት ርብቃ፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተጨንቀው “እሺ ልጀን ውሰዱና አሳድጉት” እስከማለት ደርሻለሁ ብለዋል።

“እኔስ ካገኘሁ ቆሎ ቆርጥሜ፣ ካጣሁም ውኃ ጠጥቸ ላድር እችላለሁ። ልጀን ግን ምን ላብላው? የቤት ኪራይ እንዴት ልክፈል?” የሚሉት ርብቃ፣ መንግሥት በሊስትሮ ሥራ አትሠማሩ ካለ ሌላ የሥራ መስክና ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ከዚህ በፊት ታኅሣሥ 29/ 2014 የተከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ የተደረገላቸውን ዳያስፖራዎች መነሻ በማድረግ፣ በጫማ ጽዳት ሥራ የተሠማሩ ዜጎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ መደረጋቸውን አዲስ ማለዳ ስትዘግብ መቆየቷ አይዘነጋም።

አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ደርሷት የነበረው መረጃ ዳያስፖራዎች ከመጡ ከ15 ቀን በኋላ ሥራ መጀመር ትችላላችሁ የሚል ቢሆንም፣ ሠሞኑን የአፍሪካ ሕብረት ለስብስባ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ በጫማ ሥራ የተሠማሩት ዜጎች በድጋሚ ሥራቸውን እንዲያቆሙ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ከቦሌ እስከ ስድስት ኪሎ መጽሐፍ እና ጋዜጣ ሲሸጡ የነበሩ ሰዎች ከሥራ መታገዳቸውን አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በማየት ማረጋገጥ ችላለች።

በአገራችን ኢትዮጵያ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የትምህርት ዕድል ያላገኘና ትምህርቱን ያቋረጠው ይቅርና፣ ፊደል ቆጥሮ ዲግሪ ጫነ የሚባለው ሳይቀር በሥራ አጥነት ውስጥ እንዳለ መንግሥት ራሱ ጥንቅቅ አድሮጎ ያውቀዋል።

በተለይም በመዲናችን የኑሮ ውድነት ጣሪያ መንካቱን ተከትሎ እንኳን ሥራ የሌላቸው፣ በሥራ የተሠማሩ ሰዎችም ደሞዛቸው ከወሩ ሳይደርስ እንደሚጠናቀቅ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲነግሩ መስማት አዲስ ነገር አይደለም።

ታዲያ ይህ በእንዲህ እያለ፣ ሠርተህ ተለወጥ የሚለውን መርህ ተከትለው የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ቤተሰብ እያስተዳደሩ ያሉ የመንገድ ዳር ሠራተኞችን ሥራ አቁሙ ማለት ምን ስያሜ እንደሚሰጠው ግራ መጋባታቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ እየተናገሩ ነው።

ከሥራ የታገዱት ሌላኛው ጫማ በማጽዳት ሥራ በሚያገኙት ገቢ አራት ቤተሰብ አስተዳድራለሁ የሚሉት ዋሲሁን አለሙ የተባሉት ግለሰብ ናቸው። ዋሲሁን ሥራ እንዲያቆሙ ከመደረጋቸው በተጨማሪ ደንቦች ከአራት ጊዜ በላይ የሥራ ዕቃቸውን እንደነጠቋቸው ተናግረዋል።

አንድ ጊዜ ዕቃው የተወሰደባቸው “ደንቦች መጥተው ወረዳ ስብሰባ አለ ሒዱ ችግራችሁን ግለጹ” ብለው ከላኳቸው በኋላ ሲሆን፣ ከስብሰባው ተመልሰው ሲመጡ ዕቃውን ወስደውት እንዳገኙ እና ደንቦችን ሒደው ሲጠይቁ ደግሞ “እኛ አይደለንም መንግሥት ነው ያዘዘን፤ ከፈለጋችሁ እነርሱን ሒዳችሁ ጠይቁ” እንዳሏቸው አክለው አብራርተዋል።

ወሩን ሙሉ ሥራ አልሠራሁም የሚሉት ግለሰቡ፣ በመጨረሻም የላሜራ ሱቆች ቢከፈቱልን የከተማዋን ገጽታ በማያደበዝዝ መልኩ ሥራችንን መሥራት እንችላላን ሲሉ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል።

አክለውም፣ መንግሥት መፍትሄ ይስጠን፤ ሠርተን ካልበላን ምን እናድርግ? እንስረቅ? እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም? ሲሉ ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም የዳያስፖራዎችን መምጣት ተከትሎ በመሃል ከተማ ካሉት በጫማ ሥራ የተሠማሩ ሰዎች በተጨማሪ፣ ሻይና ቡና በመሸጥ የሚተዳደሩ ዜጎችም ከሥራቸው ታግደው መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሰሞኑን ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ተከትሎ በድጋሚ ሥራ አቁሙ እንደተባሉ ነው አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ የቻለችው።

መንገድ ዳር ሻይ፣ ቡና፣ እንዲሁም አትክልት በመሸጥ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ሰዎች በበኩላቸው በደንቦች በኩል፣ “ሕገ ወጥ ናችሁ” በመባል በአገራቸው ላይ ሁሌ እየተሳደዱ መሆናቸውንና ምን ሠርተው መኖር እንዳለባቸው መፍትሔ ይሠጠን ሲሉ ቅሬታ እያነሱ ነው።

“ዳያስፖራ ይገባል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ሥራ አትሠሪም ተብዬ እየተንከራተትኩ ነው ያለሁት” የሚሉት፣ ባለቤታቸው የአዕምሮ ሕመምተኛ በመሆናቸው ሻይ እና ቡና በማፍላት ኹለት ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉት ዙሪያሽ አብራር ናቸው።

“ልንሠራ እንጅ ልንሰርቅ አልወጣንም፤ ልጅ የምናስተምረው፣ የቤት ኪራይ የምንከፍለው፣ ከዚህ ሥራ በምናገኘው ገቢ ነው” ያሉት ግለሰቧ፣ “በአገራችን ላይ አትሥሩ ብለው እንደ ሌባ እያሳደዱን ነው። ሊደበድቡን ሁሉ ይደርሳሉ። ምን እንደምልህ አላቅም” ብለው እንባቸውን አፍስሰዋል።

ከደንቦች በደረሳቸው ምላሽ መሠረት ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ መረዳት የተቻለው፣ ከዚህ በኋላ በሊስትሮ ሥራ መሠማራት የማይችሉበት አዝማሚያ መኖሩን ነው።

አዲስ ማለዳ የሊስትሮ ዕቃ ዘርግተው በሥራ ላይ የነበሩ ሠራተኞችን ከሥራ ሲያስነሱ በተመለከተችበት ወቅት ለምንድነው የምታስነሷቸው? ሥራ የሚያቆሙትስ እስከመቼ ነው? ስትል ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ከበላይ አካለት ትዕዛዝ ተሠጥቷቸው እንደሆነ ገልጸው፣ ሠራተኞቹ እስከመቼ እንደሚታገዱ ግን ዕውቀቱ እንደሌላቸው ነው ምላሽ የሠጡት።

ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት ግን አንዳንድ ደንቦች እስከመጨረሻው በሊስትሮ ሥራ መሠማራት እንደማይችሉ ነው የነገሯቸው።

ይህን በተመለከተም መስፍን አርሳዶ ተባሉት በሊስትሮ ሥራ ዘርፍ ተዳዳሪ፣ ከዚህ በፊት የዳያስፖራውን መምጣት ተከትሎ ከሥራ ሲታገዱ፣ ከ15 ቀን በኋላ ትጀምራላችሁ በተባሉት መሠረት የተለመደውን ሥራቸውን ቢጀምሩም፣ የአፍሪካ ኅብረት መምጣቱን ተከትሎ እንዳስነሷቸውና እስከመጨረሻው እንደማይሠሩ እንደነገሯቸው አብራርተዋል።

አዲስ ማለዳም ጉዳዩን በማስመልከት ለደንቦች ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በዋና መንገድ ላይ መሥራት እንደማይችሉ መወሰኑን አረጋግጣለች።

“ሚስቴ የዘጠኝ ወር ነፍሰጡር ናት” የሚሉት መስፍን፣ ምን ልሥራ? በጣም ጨንቆኛል። “ሥራ በማጣቴ ቁርስ ከበላሁ ምሳ አልበላም፤ ምሳ ከበላሁ እራት አልበላም። መንግሥት መፍትሔ ይስጠን” ነው ያሉት።

ከሥራ ታገድን የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ሥራ የማግኘት ዕድል እንደ ሰማይ በራቀባት አገር የምንሠራውን ሥራ አትሥሩ ከተባልን፣ የጎዳና ተዳዳሪ፣ እንዲሁም ሌባ ከመሆን የዘለለ ምን አማራጭ ሊኖረን ይችላል? ሲሉ ይጠይቃሉ።

በኢትዮጵያ በጠቅላላ 88ሺሕ 960 የሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉ ይነገራል። ከእነዚህም መካከል 3ሺሕ የሚሆኑት ሰዎች ድጋፍ ባደረጉላቸው የመንግስትና የበጎ አድራጎት ድርጆቶች ከጎዳና ሕይወት መገላግል የቻሉ ናቸው።

በሌላ በኩል 85ሺሕ 960 የሚሆኑት ቀሪዎቹ ደግሞ፣ የጎዳና ሕይወትን በመምራት ላይ መሆናቸውን በተለያየ ወቅት የወጡ ጥናቶች ያመላክታሉ።

ታዲያ ከጎዳና ተዳዳሪዎቹ መካከል ከፍኛውን ቁጥር የሚይዙት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉት ሰዎች መሆናቸውም የተረጋገጠ ሲሆን፤ ቁጥራቸውም ሕጻናትን ጨምሮ 50 ሺሕ እንደሆነ ይነገራል።

በመንገድ ዳር ሻይ ቡና በማፍላት፣ እንዲሁም የሊስትሮ ሥራዎችን በመሥራት የሚተዳደሩ በርካታ ሰዎች ከሥራቸው ከታገዱ ጎዳና ተዳዳሪ ከመሆን የዘለለ ዕድል እንደማይኖራቸው ለአዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ሥራ ከታገዱት ሰዎች ንግግር የተረዳቸው፣ የከተማዋን ገጽታ ታደበዝዛላችሁ በማለት ደንቦች ከሥራ ሲያስነሷቸው በችግር ከመውደቃቸው በተጨማሪ፣ እንደ ቆሻሻ የመቆጠርና የመገለል ስሜት እንደተሠማቸው ነው።

ይህን በተመለከተም አዲስ ማለዳ ከሥነ አዕምሮ ምሁራን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ምሁራኑም በሚከተለው መልኩ የሚደርስባቸውን ጉዳትና ምክረ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ሠራተኞቹ የከተማዋን ገፅታ ታደበዝዛላችሁ በሚል ሰበብ የአዲስ አበባ ደንቦች ከሥራ ሲያግዷቸው የብቸኝነትና የዝቅተኝነት ስሜት እንዳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ይህን በተመለከተም የሥነ አዕምሮ ባለሙያው ቴዎድሮስ ድልነሳው፣ ሰዎች በሌሎች አካላት የመጠላት፣ የመገፋት ፣እንዲሁም የመገለል ስሜት ሲሰማቸው፣ የዝቅተኝነት ስሜት ሊሰማቸው፣ አካላዊ ሕመማቸው ሊጨምር፣ ለበቀል ሊነሳሱ ፣ እንዲሁም ወደ ስርቆትና አላስፈላጊ ሱሶች የመግባት ዕድላቸው ሊጨምር ይችላል ነው ያሉት።

አክለውም፣ ከሥራ ታገዱ የተባሉት ሠራተኞቹ ይህ ስሜት ተሰምቷቸው ችግር ላይ እንዳይወድቁ፣ የተሻለ ቦታ ተሠጥቷቸው እንዲሠሩ ማድረግ እንጂ፣ ከዕይታ እንዲሠወሩ ለማድረግ ከዋናው መንገድ ማስነሳቱ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ነው የግል አስተያየታቸውን የሰጡት።

ሰዎች ብዙ ጊዜ ያለ ሥራ ሲቆዩ “ነገ ምን በልቼ አድራለሁ” በሚል ጭንቀት ስለሚጠመዱ ለአዕምሮ ሕመም ሊዳረጉ ይችላሉ የሚሉት ቴዎድሮስ፣ ለእነዚህ ሠራተኞች አግባብነት ያለው ነገር ማድረጉ ለአገርም ለግለሰብም ይበልጥ መልካም ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በሊስትሮ ሥራየተሠማሩ ሠራተኞች እና መንገድ ዳር ላይ ሻይ ቡና በመሸጥ ቤተሰብ የሚመሩ ሰዎች ከሥራ በመታገዳቸው ችግር ላይ እንደሆኑ ስላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት ወደ ደንቦች ጽ/ቤት አቅንታ ነበር።

ደንቦችም፣ በዚህ ሳምንት ብቻ ከ100 እስከ 150 የሚሆኑ ሊስትሮዎችን በተደጋጋሚ መንገድ ላይ እንዳስነሷቸውና በዋና መንገድ ላይ መሥራት እንደማይችሉ ነው የገለጹት።

ሻይ፣ ቡና፣ እንዲሁም አትክልትና መሰል ነገሮችን መንገድ ዳር የሚሸጡትን በተመለከተም፣ ሕገ ወጥ ሥራ እንደሆነና በየትኛውም ቦታ መሥራት እንደማይችሉ ነው አዲስ ማለዳ ከደንቦች ማረጋገጥ የቻለችው።

ቦንቦሊኖ፣ ብስኩት፣ ሻይ፣ ቡና፣ እንዲሁም አትክልት መንገድ ላይ ዘርግተው በመሸጥ ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ የሚያስረዱ ዜጎች በበኩላቸው፣ ከሥራ በመታገዳቸው ችግር ላይ ስለሆኑ መንግሥት መፍትሔ እንዲሠጣቸው አሳስበዋል።

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል መሰረት አንዱአለም የተባሉት ግለሰብ፣ እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም? ሠርተን እንለወጥ አልን እንጅ አልሰረቅን፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ድሃ መሆናችን ይታወቃል ብለዋል።

አክለውም፣ “እንደ ቆሻሻ ነው የቆጠሩን እኮ፤ ምን ሠርቸ ልጆቼን ላሳድግ በጣም ጨንቆኛል” በማለት ተናግረዋል።

በተለያዩ የሥነ ልቦና ምሁራን በኩል ጭንቀት የአዕምሮ ሕመምን እንደሚያስከትል ይነገራል።

የሺጥላ ሞገስ (ዲ/ን) የተባሉት ጸሐፊ በ2010 ለንባብ ባበቁት ‹‹ያለ ጭንቀት የመኖር ምሥጢር›› በሚለው መጽሐፋቸው ብዙ ጊዜ የሚጨነቁና የሚበሳጩ ሰዎች ከጭንቀታቸው ለመውጣት ጠጥቶ መስከር፣ እንዲሁም አደንዛዥ ዕጽ መጠቀምን እንደ መፍትሔ ስለሚወስዱ

ራሳቸውን ከመጉዳት አልፈው በምጣኔ ሀብቱ ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ አስቀምጠዋል።

የሥነ ልቦና ምሁሩ ቴዎድሮስ በበኩላቸው፣ በርካታ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ወደ ማጨስ፣ መቃም ሕይወት የሚገቡት በሥራ አጥነት እንደሆነ በአገሪቱ የሚስተዋለውን ነባራዊ ሁኔታ በማንሳት ያብራራሉ።

አክለውም፣ የሥራ አጥነት መጠን በአንድ ፐርሰንት በጨመረ ቁጥር ወደ 40 ሺሕ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት እንደሚሞክሩና በዓመት ውስጥም በርካታ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ በአንድ ወቅት አሜሪካ ውስጥ የተጠና ጥናት አረጋግጧል ብለዋል።
በመሆኑም፣ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ወይም የገቢ ምንጭ አለመኖር መሠረታዊ የሆኑ ጭንቀቶችን በመፍጠር በሰዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ተጎጅዎችም ቢሆኑ በዚህ ችግር ውስጥ ሲሆኑ ትዕግስተኛ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ባለሙያው፣ በሠራተኞቹ ላይ የተፈጸመው ድርጊት በማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ችግር እንደሚያስከትል አልደበቁም።

በተያያዘም፣ መንግሥትም ለችግሩ መፍትሔ ቢሰጥ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹም እስካሁን ችግር ሲገጥማቸው በብስጭት ወደ አጉል ሱስና መጥፎ ውሳኔ እንደሚገቡት ሰዎች ከማድረግ ይልቅ፣ በማኅበር ተደራጀተው ጥያቄ ማቅረብና ትዕግስተኛ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል።

ተመሳሳይ ጽሁፎች

እስከ መቼ ወደጓዳ?

በአዲስ አበባ ጫማ በማጽዳት ላይ የተሠማሩ ወጣቶች ከሥራ መታገዳቸውን ገለጹ

በአዲስ አበባ ጫማ በማጽዳት የሚተዳደሩ ወጣቶች የመሥሪያ ቦታቸውን እየተነጠቁ ነው


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here