በ2014 የበጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ለውጪ ገበያ የቀረበ የቅባት እህል፣ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 135 በመቶ መሻሻል ማሳየቱ ታውቋል። በግማሽ በጀት ዓመቱ ለዓለም ገበያ ለማቀረብ ታስቦ ከነበረው 7160 ቶን የቅባት እህል እና ፕሮሰሲንግ ውስጥ 13 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፣ ለዓለም ገበያ ከቀረበው 994 ቶን የቅባት እህል እና ፕሮሰሲንግ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ይህም፣ በግማሽ በጀት ዓመቱ ውስጥ ለማግኘት ከታቀደው 13 ነጠብ 2 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር 124 በመቶ የላቀ ቢሆንም፣ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ከታቀደው የቅባት እህል እና ፕሮሰሲንግ 13 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተመሳሳይ በታኅሣሥ ወር ብቻ ለዓለም ገበያ ቀርቦ ይገኛል ተብሎ ከታሰበው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ፣ 50 በመቶ ገደማ የሚሆንውን በማሳካት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን ከምግብ፣መጠጥ እና መድኃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የወጣው ሪፖርት ያሳያል። ይህም፣ ከ2013 ታኅሣሥ ወር ጋር ሲነጻጸር የ 80 በመቶ መሻሻል አሳይቷል ።
ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ እንደ ሰሊጥ እና ሱፍ ያሉ የቅባት እህሎች የሚሠጡት የዘይት ጭማቂ መጥን ወደ አገር ከሚገባው የፓልም ድፍድፍ ዘይት አንጻር አነስተኛ በመሆኑ፣ ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሬ ማግኘቱ የተሻለ እንደሆነ የምግብ፣ መጠጥ እና መድኃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባልደረባ በተለይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባጠናዉ ጥናት መሠረት፣ በአማካይ አንድ ሰው በየወሩ በምግብ ውስጥ የሚጠቀመው የምግብ ዘይት መጠን 0.72 ሊትር እንደሆነ ነው። ይህም በዓመት 8.64 ሊትር ያስፈልገዋል ማለት ነው። በመሆኑም፣ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ምግብ ዘይት መጠን በየወሩ 47,702,948 ሊትር ወይም በዓመት 572,435,376 ሊትር ነው።
ሆኖም፣ በ2011 ዓ.ም. ባለው የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አንጻር የተሠላው ስሌት በየወሩ 70,946,640 ሊትር ፍላጎት እንዳለ ያሳያል። ይህም በተግባር ሲቀርብ ከነበረው ወርሃዊ የፍላጎት መጠን 23,243,692 ሊትር ጉድለት ያሳያል። የአገሪቱ የምግብ ዘይት ፍላጎት 84 በመቶው የሚሸፈነው ከውጪ በሚገባው ፓልም የምግብ ዘይት ሲሆን፣ 11 በመቶ ከውጪ በተለያዩ ነጋዴዎች ወደ አገር ዉስጥ በሚገባ የምግብ ዘይት እና ቀሪው 5 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በአገር ውስጥ ባሉ ኢንዱስትሪዎች ምርት የሚሸፈን ነው።
በአገር ውስጥ ካለው የምግብ ዘይት ፍላጎት አንጻር አቅርቦቱን ከፍ ለማድረግ ያስችላሉ ተብለው ግምት የተሠጣቸው፣ በትግበራ ሒደት ላይ ያሉ እና ወደ መጠናቀቅ ደረጃ የተቃረቡ የኢንቨስትመንት ፕጀክቶች ተጠናቀው ወደ ምርት ሲገቡ፣ በወር 50 ነጥብ 55 ሚሊዮን ሊትር ፓልም፣ 27 ሚሊዮን ሊትር የሱፍ እና 21 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊተር የአኩሪ አተር፣ በድምሩ 99 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ምግብ ዘይት አጣርተው ለገበያ ያቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ በውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት የታለመውን ማሳካት አለመቻሉን የተቋሙ ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ገበያ ላይ ያለውን የአቅርቦት እና ፍላጎት ክፍተት ለመሙላት እንዲያስችል በቀድሞ ስሙ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለብሔራዊ ባንክ የ 600 ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክም ቅድሚያ የዶላር አቅርቦት ከሚያገኙ መስኮች መካከል የምግብ ዘይት አምራች ፋብሪካዎች እንዲሆኑ መወስኑ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014



