የማዕድን ሚኒስቴር በስደስት ወራት ከማዕድን የውጭ ገበያ 283 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታወቀ

0
834

የማዕድን ሚኒሰቴር በ2014 ግማሽ በጀት ዓመት ለውጪ ገበያ ካቀረበው አጠቃላይ፣ ከወርቅ ጌጣ ጌጥ ኢንዱስትሪ እና ከመሳስሉት ማዕድናት 283 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን አስታውቋል።

በዘርፉ ከተገኘው የውጪ ምንዛሬ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለውጪ ገበያ የቀረበ ወርቅ መሆኑ ተመላክቷል። በዚህም ለውጭ ገበያ ከቀረበው ከ4445 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ፣ በባህላዊ ወርቅ አውጪዎች የቀረበው 2996 ኪሎ ግራም በመሆን ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ በአጠቃላይ ለተገኘው 272 ሚሊዮን ዶላር ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል።

የማዕድን ሚኒስቴር የ2014 ግማሽ በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጽም ጥር 26/2014 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለማዕድን እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት የማዕድን ዘርፉ በጸጥታ ችግር ከፍተኛ ችግር እየገጠመው መሆኑን የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ ማግኘት የምትችለውን ያክል እያገኘች አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ባለፈው ስድስት ወራት የጸጥታ ችግር ለዘርፉ ከፍተኛ ፈተና መሆኑ ተነግሯል።

በሰሜኑ ጦርነት እና የማዕድን ምርት በሚገኝባቸው የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ችግር በማጋጠሙ በማዕድን አውጭዎች ላይ እንቅፋት መፍጠሩ ተገልጿል። የጸጥታ ችግሩ የምርት ሥራ የጀመሩ ማዕድን አውጭዎችን ሥራ ከማስተጓጎሉ በተጨማሪ፣ ወደ ሥራ ለመግባት የተዘጋጁ ኩባንያዎች ወደ ምርት ሥራ እንዳይገቡ እና አዳዲስ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከፍተኛ ፈተና መሆኑን ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።

በተለያዩ የማዕድን ክምችት ባለባቸው አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር ፈተና እንደሆነበት ለቋሚ ኮሚቴው ያስረዳው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ለችግሩ መፍትሔ ካልተፈለገለት ወደፊትም በማዕድን ምርት ላይ ከፍተኛ ችግር ሆኖ እንደሚቀጥል አመላክቷል። በሰሜኑ ጦርነት የኢትዮጵያ ሠላም እንደታወከ በውጭ ሚዲያዎች የሚሰሙ ዜናዎች በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ባደረባቸው ሥጋት ባለፉት ስድስት ወራት ፍላጎት አለማሳየታቸው ተጠቁሟል።

የተለያዩ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች ላይ የፀጥታ ሥጋት ባለፉተ ዓመታት የተስተዋለ ሲሆን፣ በተለይም በቤኒሻንጉል ክልል የሚገኙ የድንጋይ ከሰል፣ የዕምነበረድ አምራቾችን ምረት ማምረት እስክማስቆም የደረሰ ነው። በሌሎችም አካባቢዎች ለአብነትም በዋግኽምራ ዞን የብረት ማዕድን በማወጣት ሥራ ተሰማርቶ የነበረው ሰቆጣ ማይኒንግ ሥራውን ማቆሙ የሚታወስ ነው። በኦሮሚያ ክልል በወለጋ አካባቢ የተሠማሩ የማዕድን አውጭዎችም በጸጥታ ችግር የምርት ሥራቸው ሲስተጓገል እንደነበር ይታወሳል።

በማዕድናት ማምረቻ ቦታዎች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል። የተለያዩ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች ላይ የሚስተዋለዉን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የደኅንነት መረብ ኤጀንሲ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንሲ ኃላፈዎች ጋር ዉይይት በማድረግ የማዕድን ፖሊሲ ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ ተገብቷል ተብሏል። ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ ባሉ ቦታዎች ላይ የየክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጸጥታ በማስፈን ተሠማርተው አምራቾችን በከፊል ወደ ሥራ መመለሳቸው ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here