የስታትስቲክስ ዐዋጅ እየተሻሻለ መሆኑ ተገለጸ

0
765

የተሻሻለው ረቂቅ ዐዋጅ ክልሎችን ይቆጣጠራል

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የስታትስቲክስ ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ ዐዋጅ ማዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ረቂቅ ማሻሻያ ዐዋጁ የተዘጋጀበት ዋናው ምክንያትም የአገሪቱ ስታትስቲክስ በሥርዓት የሚመራበትና ጠንካራ አገራዊ የስታትስቲክስ ሥርዓት እንዲኖር ነው ተብሏል። ረቂቁ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገበት አገልግሎቱ አስታውቋል።
ከዚህ በፊት ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ ያለው ዐዋጅ ክፍተቶች ስላሉበት መሻሻል እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳፊ ገመቺ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ሕጎች በየጊዜው መሻሻል አለባቸው ያሉት ኃላፊው፣ ረቂቁ ከመዘጋጀቱ በፊት በነበረው ዐዋጅ ክልሎችን መቆጣጠር አይቻልም ነበር ብለዋል። ከዚህ ቀደም ክልሎች በራሳቸው ፈቃድ የስታትስቲክስ ቢሮ የማቋቋም አዝማሚያ ያሳዩ ነበር ያሉት ኃላፊው፣ የመረጃ ጉዳይ ደግሞ ወጥ በሆነ አንድ አካል መተዳደር ስላለበት መሰል ችግሮችን ለማጥራት ታስቦ የማሻሻያ ረቂቁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም፣ በሥራ ላይ ያለው ዐዋጅ ተቋሙ የአገሪቱን የስታትስቲክስ ሥርዓት እንዲያደራጅ፣ እንዲያስተባብርና የአቅም ግንባታ እንዲሰጥ ቢፈቅድም ለማስፈጸም ግን የሕግ ክፍተትና ውሱንነት እንዳለበት አመላክተዋል።

በኹሉም ተቋማት ተመሳሳይ የሆነ የመረጃ መናበብ እንዲፈጠር፣ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ተጠቃሚዎች እንዳይደናገሩ ለማድረግ እና ለአገር የሚበጅ ወጥ የሆነ የስታሥስቲክስ ሥርዓት መፍጠር በማስፈለጉም የማሻሻያ ረቂቁ እንደተዘጋጀ አክለው ገልጸዋል።

የማኅበረሰቡ ፍላጎት ጨምሯል፤ የአገሪቱ የፖለቲካ ዕሳቤና ፍላጎት አድጓል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስታትስቲክስ አንጻር የተቀየሩ ብዙ ነገሮች አሉ ያሉት ኃላፊው፣ ቴክኖሎጅም በመኖሩ እነዚህን ኹሉ በአግባቡ ለመጠቀም የስታትስቲክስ ሕጉ ያን በሚያስተዳድር ሁኔታ መሻሻል እንዳለበት ተናግረዋል።

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የዘላቂ ልማት ግቦችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለመሰብሰብና ለማደራጀት ያለው ዝግጁነት እና ቀልጣፋነት ለመገምገም የ2012/13 የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ጥር 23/2014 ባደረገው ስብሰባ፣ የአገሪቱ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት የተቆራረጠ እና ወጥነት የሌለው መሆኑን አመላክቷል።

በዚህም፣ በተለይ የዘላቂ ልማት ግቦችን ትግበራ የሚያመላክቱ መረጃዎችን ከኃምሳ ተቋማት ለማግኘት ተፈልጎ ከአምስት ተቋማት ብቻ እንደተገኘ እና አርባ አምስቱ ተቋማት ስለሚሠሩት ሥራ መረጃ በአግባቡ እንደማይሰበስቡና የመረጃ ቋትም የሌላቸው መሆኑ ተገልጿል።
የመረጃ ቋት ያላቸው ተቋማትም በአንድ ይዘት ላይ የሚያወጡት መረጃ ተዛማጅነት እንደሌለውና ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጋርም የአሠራርና የመረጃ ቅንጅት እንደሌላቸው ተጠቅሷል።

ተጠያቂነት ባለመኖሩም ከመረጃ ጋር ተያይዞ ተቋማት የፈቃደኝነት ማነስ ስለሚያሳዩ የሚሻሻለው ረቂቅ ዐዋጅ መረጃ የማያስቀምጡ እና የተሳሳተ መረጃ የሚያቀርቡ ተቋማትን ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው፣ ብሎም ስለሚወጡ መረጃዎች በኹሉም ዘንድ መናበብ እንዲፈጠር ያደርጋል ነው የተባለው።

እስካሁን የነበረው የሕግ አሠራርም የመንግሥት ተቋማትን ብቻ የሚያካትት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተሸሻለው ረቂቅ ዐዋጅ ላይ ግን የግል ተቋማትም መረጃ ማስቀመጥና ማቅረብ እንዳለባቸው ለማካተት መታሰቡ ተመላክቷል።

መረጃ የአንድን ተቋምና አገር ቁመና ለማወቅና ለመተንተን ያለው ሚና የላቀ ቢሆንም፣ ተቋማት ይህን ሲያደርጉ ባለመታየታቸው እና አገሪቱም ጠንካራ የመረጃ ማዕከል ስለሌላት፣ በ2030 እደርስበታለሁ ብላ ካስቀመጠቻቸው የዘላቂ ልማት ግቦች ላትደርስ እንደምትችልም ጥቆማዎች ተሠንዝረዋል።

የተዘጋጀው ረቂቅ ዐዋጅ በተፈጠረው የመንግሥት ተቋማት አዲስ አደረጃጀት ምክንያት የሥያሜ ለውጥ፣ እንዲሁም ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር የኃላፊነት መጋራት በመፍጠሩ የይዘት ማስተካከያዎች ካሉ ተጨምረውበት በሚመለከተው አካል አቅጣጫ ሲሠጥ ለዐቃቤ ሕግ ቀርቦ በፓርላማ እንዲጸድቅ ይደረጋል ሲሉ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here