‹‹ኦነግ ጫካ ካለው ሸኔ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት አለው›› የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን

Views: 4514

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሰላማዊ መልኩ ለምርጫ እወዳደራለሁ የሚለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በበረሃ ሆኖ የትጥቅ ትግል እያካሄደ ካለው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት አለው ሲል ወቀሰ።

‹‹ኦነግ በአንድ በኩል ሰላማዊ የሆነ ምርጫ ላይ እሳተፋለሁ ብሎ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃ ካስቀመጠው የታጠቀ ሃይል ጋር እጅግ በጣም ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ በመመሳጠር በየቀኑ ትንኮሳዎች፣ ግድያ፣ ዘረፋ እና ከግዜ ወደ ግዜ እየሰፋ የመጣ እንቅሳቃሴ አለ›› ሲል ምክትል ኮሚሽነሩ የሰጡትና በኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ላይ የተላለፈው ገለፃ ያስረዳል።

ከፓርቲው ውጪም ከፍተኛ የሆነ በጀት ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በማሰባሰብ ለዚህ ሃይል ፍጆታ፣ የትጥቅ መግዣ እንዲሁም የሬሺን አቅርቦት ላይ የተሳተፉትን ኮሚሽኑ መለየቱን የተናገሩት ግርማ ‹‹ፖሊስ አሁን ላይ የወሰደው እርምጃ ከሌላው ግዜ ለየት ያለ እርምጃ ነው›› ብለዋል። ስለ እርምጃው ዝርዝር ባይገለጽም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ብቻ የሚደረግ ነው ሲሉም አክለዋል።

በወለጋ አራቱም ዞኖች ራሱን ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጥቃት እያደረሰ ነው ሲሉም ኮሚሽሩ ገልፀዋል።

የክልሉ ፖሊስ እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም እርምጃ እየወሰደ ቢመጣም እስካሁን የወሰደው እርምጃ ግን ከችገሩ ስፋት አንፃር ተመጣጣኝ አይደለም የሚል ግምገማ ላይ መደረሱንም አስታውቀዋል። ‹‹ይህንን ለማስቆም እና ህብረተሰቡ ሰላማዊ የሆነ ኑሮ እዲኖር እነኚህ በየቦታው በግዲያ ወንጀል ላይ ተሰማርተው ያሉ ሰዎችን የመመንጠር እና ለህግ የማቅረብ ስራ ፖሊስ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ልገልፅላችሁ እወዳለሁ›› ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።

በተገባደደው ሳምንትም ፓርቲው በአዲስ አበባ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ላይ በአባላቶቼ እና በአመራሮቼ ላይ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰብኝ ነው ማለቱ ይታወሳል። አዲስ ማለዳም ማምሻውን ወደ ፓርቲው ሊቀ መንበር፣ ቃል አቀባይ እንዲሁም ነባር አባላት የስልክ ጥሪ ብታደርግም ስልካቸው ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ለግዜው ማካተት አልቻለችም።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com