“ዲና” የጉዞ ማስታወሻ

0
861

በጌራ ጌታቸው የተፃፈው ይህ የጉዞ ማስታወሻ መቼቱን ከአዲስ አበባ እስከ ሀዋሳ በሚደረግ የአውቶብስ ጉዞ ላይ ዘርግቶ የአንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪን ቅንጭብ የአፍላነት የ‘ፍቅር’ ሕይወት በጨረፍታ በማሳየት የማኅበረሰባችን ጉድለትም አብሮ ያመላክታል።

በጌራ ጌታቸው የተፃፈው ይህ አጭር ልብ ወለድ ድርሰት መቼቱን ከአዲስ አበባ እስከ ሀዋሳ በሚደረግ የአውቶብስ ጉዞ ላይ ዘርግቶ የአንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪን ቅንጭብ የአፍላነት የ‘ፍቅር’ ሕይወት በጨረፍታ በማሳየት የማኅበረሰባችን ጉድለትም አብሮ ያመላክታል።

ዕለተ ሰኞ፣ ቀን ስድስት ሰዓት ተኩል ላይ ነው። መስቀል አደባባይ ላይ አንገታም አውቶቡሶች ፊታቸውን ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አዙረው ኩንቢያቸውን እንደ ዝሆን ግንባራቸው ላይ ቀስረው የሚጋልባቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

አንዳንድ ተሳፋሪዎች በስፍራው ካሉ ጀብሎዎች(ሱቅ በደረቴዎች) እንደማስቲካ፣ ሞባይል ካርድ፣ውሃና ለስላሳ መጠጦችን እየሸማመቱ አውቶቡሶቹ የሚንቀሳቀሱበትን 7፡00 ሰዓት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። እኔም ከተሳፈሪዎቹ አንዱ ነበርኩና ለጉዞ የሚሆነኝን ነገር እየሸማመትኩና አካባቢውን እየታዘብኩ እጠባበቅ ነበር። ወቅቱ የዓለማየሁ ገላጋይ “ታለ በስም” የተሰኘው መፅሐፍ ገበያ ላይ የዋለበት ስለነበር መፅሐፉን ገዝቼ ለማንበብ ጓጉቻለሁ።

በቆምኩበት ዘወር ዘወር እያልኩ ስመለከት ዓይኔ አንድ ነገር ላይ አረፈ። በተለምዶ ኢንጅነር ስመኘው የሞተበት ለመባል በበቃው ቦታ አካባቢ ጥግ ላይ ጥንዶች አንገት ለአንገት ገጥመው አየሁ። ድንገት ባዩት ነገር አይኞቼ ተማርከው ቀሩ። እውነት ነው ሁኔታው የተለየ በመሆኑ ማፍጠጤን ወደድኩት።

ዝቅ ባለ ድንጋይ ላይ የተቀመጠች ልጅ በደረጃው ላይ የተቀመጠን አንድ ወጣት ተንጠራርታ በቀኝ እጇ አንገቱን ጨምድዳ ተለጥፋበታለች። ልጅቱ ልጁን አንቃ ለመግደል የምትተናነቅ መስሎኝ ደነገጥኩ። ቦታው የወንድ ልጅ ደም የቀመሰ በመሆኑ ጥርጣሬዬ ከዚህ የመነጨ ነበር። መስቀል አደባባይ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ጀግና የውሃ ሽታ ካደረገ በኋላ የሚያምነው ጠፍቷል፤ ታድያ እንዴት አልጠረጥር?

ነገሩ ግን ሌላ ነበር። ለካ ከንፈሮቹን በከንፈሮቿ ይዛ ነው መጠምጠሟ። በቅፅበት ከድንጋጤ ስሜት ወጣሁ። እሱ አይኑን ወደኛ ላክ እያደረገ በ“ሴት የላከው ወንድ አይፈራም” ብሂል ከንፈሩን ሰጥቷታል። እርሷም ጀርባዋን ለኛ ሰጥታ እየተስገበገበች ትስመዋለች። ከመንጠራራቷ ብዛት የለበሰችው ቲ-ሸርት ወደ ላይ እየተሰበሰበ በታይት ሱሪዋና በቲ-ሸርቷ መካከል ቀይ ገላዋ ሲያበራ ይታያል።

ልጅቱ የልጁን ከንፈር አንድም ነገር ሳታስቀር ወደምትሔድበት አገር ይዛ ለመሔድ ያሰበች ይመስል ከሥሩ ለመነቀል እስከሚቃጣው ድረስ ተስገብግባ ትስመዋለች።

ሁኔታው የማማ ማሚቴን ነገር አስታወሰኝ። ጎረቤታችን እማማ ማሚቴ የልጅ ልጃቸውን ቁርስ እያበሉ፣ ሲጨምሩ አይጠግብ፣ ሲጨምሩ አይጠግብ፣ እስከምሳው ያዘጋጁለትን በቁርሱ ሲጨርሰው ጊዜና ሌላም ቢጨምሩለት ለመብላት ያለውን ፍላጎት ባዩ ጊዜ “እንዴ! አንተ ልጅ እንደ ሕወሓት ባለሥልጣናት የቤቱን ሀብት ጥርግርግ አድርገህ የት ልትመሽግ አስበህ ነው?” በማለት ንግግራቸው በውል በማይገባው የ5 ዓመት የልጅ ልጃቸው ላይ አምባርቀውበት የመመገቢያ ሳህኑን አንስተው ወደ ጓዳ ጥለውት ገቡ። እኔም ይቺ ልጅ የሰው ከንፈር ጠራርጋ የት እንደምትመሸግ ለማወቅ ጉጉት አደረብኝ።

አውቶቡሱ ሞተሩን ማሞቅ ሲጀምር ወጣቶቹ በሞተሩ ድምፅ በመባነናቸው ከግብ ግብ ወጥተው ወደ አውቶቡሱ ተጠጉ። ሰዓቴን አየት ሳደርግ ስድስት ሰዓት ከ55 ደቂቃ ይላል። የቀረው 5 ደቂቃ በመሆኑ ወጣቶቹ የስሜት ስካራቸው አወላክፎ እንዳይጥላቸው በሚመስል ሁኔታ ተቃቅፈው እንደተደጋገፉ ወደ አውቶቡሱ ተጠጉ። እኔም የቴአትሩን ሌላ ክፍል ማብቃትና የአውቶቡሱን መንቀሳቀሻ ሰዓት መድረስ ተከትሎ ወደ አውቶቡሱ ገብቼ ወንበሬ ላይ ተቀመጥኩ።

ሁሉም ተሳፋሪ ገብቶ እሷ ብቻ ቀረች። ረዳቱ የቀረ አለ? የሚለውን ጥያቄውን ለተሳፋሪ ሲያቀርብ በድጋሚ የባነነችው ወጣቷ በጥድፊያ ከንፈሩን ስማው ያልጨረሱት ወሬ እንዳለ በሚመስል ቅር እያላት ፈጥና ገባች።

በአውቶቡሱ ውስጥም እኔና እሷ በተከታታይ ወንበር ላይ በመቀመጣችን ቀጣይ ትወናዋን ለመከታተል አላስቸገረኝም።

ገና አውቶቡሱ ሳይንቀሳቀስ ሞባይሏን አወጣችና አንድ ቁጥር ላይ ደወለች። በቅፅበት የተነሳላት ስልክ ላይ ማውራት ጀመረች። ልጅቱ በአብዛኛው በለሆሳስ ድምፅ የምታወራ በመሆኗ “ለሁሉም ነገር አመሰግናለሁ፤ ግን ገንዘቡን አብዝተኸዋል፤ በጣም እወድሃለሁ ማሬ” የሚሉት ንግግሮቿ ብቻ ጎልተው ተሰሙኝ። ትንሽ ካወራች በኋላ ስልኳን ዘግታ የወንበሩን ቀበቶ አስራ ተደላድላ ተቀመጠች።

የቦሌን መስመር ከታክሲዎችና ከቤት ተሽከርካሪዎች ጋር እየተጋፋ የሚያዘግመው አውቶቡስ ብራስ ድልድይን አልፎ የቦሌ ሚካኤልን ቀለበት መንገድ ሲይዝ ፍጥነቱን ጨመረ። ጉዞው ወደ ውቢቷ ሃዋሳ ከተማ ነበር። የከንፈር ዘራፊዋ ልጅም መመሸጊያ ይቺው ከተማ መሆኗን ተረዳሁ። እኔም የዓለማየሁ ገላጋይን አዲስ መፅሃፍ እየተስገበገብኩ ማንበቤን ተያይዜዋለሁ። የእርሷን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ሥራዬም አልተቋረጠም። ወጣቷ በጆሮዋ የዘፈን ማዳመጫዋን ሰክታ ሙዚቃ እያዳመጠች በሰመመን ውስጥ እንደሆነች አዲስ-አዳማ ፈጣን መንገድ ገባን።

ፈጣን መንገዱ ላይ ስንደርስ ብንን ያለችው ይቺ ወጣት የሙዚቃ ማዳመጫውን ከስልኩ ላይ ነቅላ አንድ ስልክ ላይ ደወለች። ገና ሄሎ! ሳትል የላይኛውና የታችኛው ከንፈሮቿ ወደ ዳር አፈገፈጉና ጥርሶቿ ለመሳቅ ወደ ፊት ብቅ አሉ። ወዲያው የተዳፈነ ፍቅር በሚቀሰቅስ ቀጭን ድምፅ ሄሎ አለች። ከስልኩ ማዶ ምን እንደሰማች ባላውቅም ወደ ላይ አንጋጣ ከትከት ብላ ሳቀች።

“ቤቢ በጣም ይቅርታ፣ ማዘር እኮ አልፋታሽ ብላኝ ነው። ልክ አውቶቡሱ እስክገባ ድረስ አብራኝ ነበረች፣ እንዴት ነህ?” ብላ በአራዳ ቋንቋና በመደበኛ ንግግር ስብጥር ከጠየቀችው በኋላ በተራዋ ማዳመጥ ጀመረች። ትንሽ ካዳመጠች በኋላ “ሃዋሳ እንዴት ነች? ክላስ ብዙ አመለጠኝ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ጠይቃ መልሳ ማዳመጥ ጀመረች። ከወዲያ የተሰጣትን ምላሽ ባላወቅም ተንከትክታ እየሳቀች “አንተኮ የኔ ባትሆን ምን ይውጠኝ ነበር? ስንት ቀን ፈረምክልኝ? ‘አይዲ’ ቁጥሬን አወከው?” ብላ ተከታታይ ጥያቄዎችን ጠይቃ መልሱን ማዳመጥ ጀመረች። ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ “ለነገሩ እንኳን ‘አይዲ’ ቁጥሬን ሌላውን ሚስጥር ቁጥሬን ታውቀው የለ” ብላ በድጋሜ ሌላ ከትከት ያለ ሳቅ በመሽኮርመም አከለች።

እኔም መፅሐፉ ላይ ካለው ታሪክ ይልቅ የማይደገመው የልጅቱ ታሪክ ስለጣመኝ የደረስኩበት ገፅ ላይ ምልክት አድርጌ ሁኔታውን መከታተል ጀመርኩ። በሳቅ፣ በጥያቄና በመሽኮርመም የተሞላው የወጣቷ የስልክ ወሬ ፈጣን መንገዱን ጨርሰን ሞጆ ስንገባ አቆመ። በቀጥታ ሙዚቃ ማዳመጫዋን ሰካች “እፎይ! እኔም ሥራ ቀለለልኝ” መፅሐፌን ማንበብ ቀጠልኩ።

ወጣቷ አንድ የተቆለመመ ትራስ አንገቷ ላይ አድርጋ ወንበሯን ወደ ኋላ ትንሽ ለጠጥ በማድረግ ተደላድላ ተኛች። ከሞጆ ጀምሮ እየነቃች፣ ተመልሳ እየተኛች፣ እኔም በመሃል ስትፈራገጥ ተነስታ ልትተውን እየመሰለኝ ቴአትሩ እንዳያመልጠኝ በጉጉት ስጠባበቅ ዳጎስ ያሉ ገጾችን አንብቤ ዝዋይ ደረስን።

ዝዋይ ላይ የነቃችው ወጣቷ በድጋሜ ስልኳን አውጥታ ደወለች። አሁን ሄሎ ከማለቷ በፊት ድብርቷን ለማባረር በሚመስል ዘለግ አድርጋ አዛጋች። ልክ ማዛጋቷን ሳትጨርስ አሁንም በሚስለመለም ድምጽ “ሄሎ” አለች።

“ወዬ አባቴ፣ ዝዋይ ደርሻለሁ፤ ብታይ ካንተ ከተለየሁ ጀምሮ ድብር ብሎኝ አዲስ አበባ የተኛሁ ገና አሁን ስልኬን አወጣሁት” ብላ ከሱ በመለየቷ ድብርትና ናፍቆት እንደተጫጫኗት ገለፀችለት። “አቤት ውሸት!” ብዬ በውስጤ ታዘብኳት። ይህ ሰው ያ ኢንጅነር ስመኘው አንገቱን እደፋበት ቦታ አንገቷን አስረዝሞ ሲስማት የነበረው የአዲስ አበባው ወዳጇ እንደሆነ ገባኝ። የኹለቱ የስልክ ወሬ ደርቶ አንድ ሞቅ ያለ ሳቅ ለተሳፋሪዎች ጋበዘችን። ከዚያም “ሙት በአደባባይ እንደዚያ መሆናችን ግን አይገርምም? እስክመለስ የሚበቃኝን ‘ቴክ አዌ’ ይዣለሁ፤ አንተስ?” ስትል ጠየቀችው። እሱ የሰጣትን ምላሽ ባላውቅም “አመሰግናለሁ” አለችው። ‘ቴክ አዌ’ ያለችው ግን የከንፈር ‘ቴክ አዌ’ እንደሆነ ገብቶኛል።

እውነቷን ነው የኢንጅነሩ በአደባባይ መሞት ያላስገረመው ማን አለ? በአደባባይ እንደዛ መሆናቸው ባይገርማት ነው የሚደንቀው። እንደዛ የሰው ከንፈር ዘርፋስ ባይበቃት ምንኛ ያስተዛዝበን ነበር። ግን የዘራፊ በቃኝ ባይ በሌለባት አገር በቃኝ በማለቷ፣ አመስጋኝ ዘራፊ በሌለበት በማመስገኗ እኔም በውስጤ ፈገግ ብዬ አመሰገንኳት። “ምንናለ የአገራችንን ሀብት ሙልጭ ያደረጉ ዘራፊዎች የጠበቃ የለንም፣ ቤት የለንም ወዘተ ከሚሉ በግልፅ በቂያችንን ዘርፈናል ብለው የዋሁን ሕዝባቸውን አመስግነው ቢመሽጉ?” ብዬ ራሴን ጠየኩ።

ስልኳ ሲቆም፤ እኔም ካቆምኩበት ጀምሬ መፅሐፌን ማንበብ ቀጠልኩ። መፅሃፉ በአንድ የፍልስፋና ተማሪና አስተማሪ ጓደኝነትና ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ስለነበረ ይቺ ልጅ የዩንቨርስቲ ተማሪ ብትሆንስ ብዬ አገናኘሁት። ቀደም ሲል ስለ ‘አይዲ’ ቁጥር፣ ስለ ‘አሳይንመንት’ ማውራቷ ደግሞ ይበልጥ አጠራጠረኝ።

ከዝዋይ ጀምሮ በአውቶቡሱ ውስጥ አንድ የአማርኛ ፊልም ስለተከፈተ ይቺን ወጣት ጨምሮ አብዛኛው ተሳፋሪ ትኩረቱን ፊልሙ ላይ አድርጓል። እኔም በብዛት መፅሐፌ ላይ አልፎ አልፎ ደግሞ ፊልሙ ላይ አተኩሬአለሁ። በገደምዳሜ ባየሁትም ቢሆን ፊልሙ አንድ የፖሊስ ፍቅረኛ የነበረች ቆንጆ ወጣት ሞባይሏን በሰረቃት ወጣት ፍቅር ስለመውደቋ የሚያሳይ ነበር።

እንዲህ እንዲህ እያልን ሻሸመኔ ስንደርስ ረዳቱ “ሻሸመኔ ወራጅ ካለ ተዘጋጁ!” የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈ። ከፊትም ከኋላም ለመወረድ የሚዘጋጁ ተሳፋሪዎች ስለነበሩ መንኮሻኮሹ ቀጥሏል። ግማሹ ሻንጣ ያወርዳል፣ ግማሹ ከጎኑ ካለው ሰው ስልክ ቁጥር ይቀበላል። የማይወርደው ለሚወርደው መንገድ እየከፈተ ብቻ በአውቶቡሱ ውስጥ ትርምስ የማይባል መጠነኛ እንቅስቃሴ ነበር።

ሻሸመኔ የሚወርዱ ተሳፋሪዎች እየወረዱ ባለበት ቅፅበት የጫጫታውን ጋብ ማለት ተጠቅሞ ረዳቱ እኛ ወደተቀመጥንበት ወንበር ጠጋ ብሎ ጮክ ባለ ድምፅ “ዲና ማነው? መልስ አልወሰደም” በማለት እጁ ላይ ያለውን ትኬት እያነበበ ጮክ ብሎ ጠየቀ። በረዳቱ ድምፅ ብንን ያለችው ወጣቷ “እኔ ነኝ፣ ይቅርታ ረስቼው ነበር፣ አመሰግናለው” ብላ መልሷንና ትኬቷን ተቀበለች። በዚህ አጋጣሚ ወጣቷ ዲና እንደምትባል ለመረዳት ቻልኩ። ለጉዞው የሚከፈለው 180 ብር በመሆኑ ዲና 200 ብር ሰጥታ እንደነበርም ተረዳሁ።

ዲና መልሷን ከተቀበለች በኋላ ስልኳን ወደ ጆሮዋ አስጠግታ “ሄሎ ቤቢ ሻሸመኔን እያለፍኩ ነው፤ ውጣልኝ” ብላ በደከመ ድምፅ አዘዘችው። እሱም እሺታውን ለግሷታል መሰለኝ፣ “ግን በር ላይ ሳይሆን መናኀሪያ ነው የምትጠብቀኝ” ብላ ሌላ ትዕዛዝ አከለች። እኔም መውረጃዬ እየደረሰ ስለሆነ መፅሀፌን አጣጥፌ ሙሉ የዕይታ ትኩረቴንና ከፊል የመስማት ፍላጎቴን ፊልሙ ላይ፣ ከፊል ጆሮየን ደግሞ ልጅቱ ወሬ ላይ አደረኩ።

በስልክ ልውውጣቸው ለምን መናኀሪያ ጠብቀኝ እንዳለችው የተደወለለት ወጣት ግራ ሳይገባው አይቀርም መሰል “ዛሬ ባክህ ዶርም አልገባም፣ ናፍቀኀኛል፤ አልጋ ይዘን እናድራለን፤ ከማዘር ገንዘብ ተቀብያለሁ እንዳታስብ” በማለት አስረዳችው። ቀጥሎም ወጣቱ ፈተና እንዳለበት ሳይገልፅላት አይቀርም “ባክህ የሚነበበውን ይዘህ ና!” በማለት ቀጭን ትዕዛዝ ካስተላላፈች በኋላ ስልኩን ዘጋችው።

ቴአትሩ ከአንድ ትዕይንት የዘለለ ክፍል እንደማይቀረው በመገመት ሙሉ ትኩረቴን ፊልሙ ላይ በማድረግ የፊልሙን መልዕክት ለመረዳት ሞከርኩ። ፊልሙ አንድ ቆንጆ የሀብታም ልጅ ከፖሊስ ጋር ፍቅር የጀመረችው ፖሊሱ የአባቷን የጠፉ ጠቃሚ ሰነዶች ማግኘቱን ተከትሎ በውለታ ተሸብባ እንደሆነ ያስረዳል። በሒደት በፖሊሱ ሥራና ባሕሪይ እየደበራት የመጣችው ይቺ ወጣት በድንገት አንድ ቀን ሞባይሏን ትሰረቃለች። ከተሰረቀች በኋላም በሞባይሏ ላይ ስትደውል ሌባው ያነሳና ያወራታል፣ በተደጋጋሚም ስትደውል ያወራታል፣ ሌባው ጨዋታ የሚችልና ድምፁ ማራኪ ስለነበር ልጅቱ ሳታስበው በፍቅሩ ትወድቃለች። ከዚያ በአጭሩ ፖሊሱን ከድታ ሌባውን አገባችው፤ ቤተሰቦቿም አመሉን ከረሳ ብለው ወደዱላት።

ፊልሙ ሀዋሳ ስንገባ አለቀ። የዲና ትወና ግን እንደሚቀጥል ተስፋ አድርጌ መናኀሪያ ደረስኩ። አውቶቡሱ ተሳፋሪዎችን ሲያራግፍ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሆኗል። እኔም ልጅቱን ተከትዬ ስወርድ አንድ ሪዙን በቀጭኑ የተስተካከለ፣ ጉልበቱ ላይ የተቀደደ ኦሞ መሳይ ቀለም ያለው ሱሪ የለበሰ፣ የከንፈር አካባቢ ፂሙን ደግሞ በእንግሊዘኛው ‘ኦ’ ቅርፅ የተሠራ፣ ባለ ሉጫ ፀጉር ጠይም ልጅ ፈገግ ብሎ አቀፋት፣ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ተሳሳሙ፣ በመጨረሻ ግን ከንፈር ለከንፈር ከተጋጩ በኋላ ሻንጣዋን አንጠልጥሎላት በቀኝ ባለው መታጠፊያ ወደ ውስጥ አመሩ። በዚያ አካባቢ ብዙ መኝታ ቤቶች አሉ። ኹለቱም ልጆች የዩንቨርስቲ ተማሪዎች መሆናቸውን አረጋገጥኩ። ባነበብኩት መፅሐፍ የፍልስፍና ተማሪው ከአንድ ቆሎ ተማሪ ባገኘው ግዕዝ የዩንቨርስቲ ጓደኞቹንና ጠቅላላ ተማሪውን “አደግ ወ ክበድ ሁላ ተሰባስቦ” እያለ እንደሚማረርባቸው ተረድቻለሁ።

‘አደግ ወ ክበድ’ ሲፈታም አህያና በቅሎ ማለት ሲሆን እሱ የፍልስፍና ተማሪና ሆዳም አንባቢ፤ በአጠቃላይ ከአዋቂዎች ቡድን የሚሰለፍ በመሆኑ ሌሎቹን እንደ አህያና በቅሎ ስብስብ እንደሚቆጥራቸው ለሁሉም ሰው ስለ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሲያወራ እነዚህ ‘አደግ ወ ክበድ ሁላ’ እያለ እንደሚሰድባቸው መፅሐፉ ያስረዳል። እነዚህ ተማሪዎችስ ‘አደግ ወ ክበድ ሊባሉ ይችሉ ይሆን? ልጅቱ ከአዲስ አበባው ጓደኛዋ የተቀበለችውን ገንዘብ የዩንቨርስቲ ፍቅረኛዋን ለማዝናናት ተጠቅማበታለች፤ በጨለማው ፈረቃ ወጣቱ ይዞት የመጣውን መፅሐፍ የሚያነብበት ጊዜ ይኖረው ይሆን? ግንኙነታቸውስ በጥንቃቄ ይሆን? ከዚህ አዳር በኋላስ ዲና አብራው በጓደኝነት ትዘልቅ ይሆን? ወይስ ደግሞ በከተማዋ ወዳሉ ጭፈራ ቤቶች ጎራ ብላ ችላ ትለው ይሆን?

በፊልሙ ላይ ያለችውስ ቆንጆ ሌባዋን አግብታ አርፋዋለች። ሌባን እየተባባረች በፖሊስ ጓደኛዋ ፍቅርና እንጀራ ላይ ተረማምዳለች። ሌባን ልጄ ብለው በጉያቸው የሚሸሽጉ ክልሎች ባሉባት አገር የፊልሙ ደራሲ ይሄንን ታሪክ መክተቡ አይደንቅም። የዩንቨርስቲዋ ወጣትም በአዲስ አበበባው ጓደኛዋ ፍቅር ላይ ተረማምዳ ከሌላ ጋር አድራለች፣ ገንዘቡንም ሌላ አዝናንታበታለች፣ ከዚህኛውስ ትራመድ ይሆን? ከተራመደችስ ወዴት?

በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘቧ በዘራፊዎች ድንበር እያቋረጠ ሌሎች አገራትን እየፈወሰ ባለባት አገር ውስጥ ከአንዱ ዘርፎ ሌላውን ማጥገብ አዲስ ነገር ባይሆንም የዲና ነገር ግን እየገረመኝ ወደ ቤቴ አቀናሁ።

ጌራ ጌታቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው geragetachew@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here