አገር በቀል የፍትሕ ስርዓት በ‘ኮቱ-ዱፌ

0
1048

በአገራችን የሕግ የበላይነትን እና ፍትሕን ለማስፈን ካልተቻለባቸው ምክንያቶች መካከል ሕጎቻችን እና የፍትሕ ስርዓቱ የምዕራባውያን አገራት ቀጥተኛ ቅጂ መሆኑ ነው በማለት የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው። በዚህ ረገድ አገር በቀል የዳኝነት ስርዓቶች ምን እንደሚመስሉ ከሚያሳዩ መጽሐፍት አንዱ በውብሸት ጌታሁን የተጻፈወው ‘ኮቱ-ዱፌ’ ነው። ቶፊቅ ተማም ይህንን መጽሐፍ አንብበው ቅምሻ ያስነብቡናል።

 

በኦሮሞ ገዳ ስርዓት ተግባራዊ የአገር በቀል ጥበብ ላይ የሚያተኩረው የደራሲ ውብሸት ጌታሁን ‘ኮቱ-ዱፌ’ የተሰኘው መጽሐፍ በቅርቡ ገበያ ላይ የዋለ ሲሆን፥ መጽሐፉም የኦሮሞን የዕርቅ፣ የዳኝነት ባሕል እና የፍትሕ ስርዓት በጥልቀት ሲዳስስ ‘ኮቱ-ዱፌ’ በጥሬ ትርጉም ደረጃ ‘ኮቱ’ ና ማለት ሲሆን፥ ‘ዱፌ’ ደግሞ መጣሁ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ‘በላ-ልበልሃ’ ከሚለው ባሕላዊ የፍትሕ አሰጣጥ ስርዓት ጋር ቢመሳሰልም፥ በሚያቅፈው ጉዳይ፣ ወሰን እና ጥልቀት ግን እንደሚለይ በመጽሐፉ ተገልጿል።

የመጽሐፉ መነሻ ጥናት ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በፊት መሆኑን የሚገልጹት ደራሲው፥ ለመጽሐፉ መነሻ ምክንያትም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የአካባቢ ንብረት እንክብካቤ ጉዳዮች ሲሆኑ፥ እንደሚታወቀው በአብዛኛው የዓለም ክፍል የአካባቢ ግጭት ዋነኛ ምክንያት የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብትና አጠቃቀም ነው። ይህንን ግጭት ለመፍታት የኦሮሞ ልኂቃን ይጠቀሙበት የነበረውን የ‘ኮቱ-ዱፌ’ የፍትሕ ስርዓት በጥልቀት ይፈትሻል።

አገር በቀል የፍትሕ አስተዳደር ስርዓት መገንባትና ማጎልበት፣ እንዲሁም የአገር በቀል ዕውቀት እና ጥበብ መሠረት ተደርገው የተገነቡ የፖለቲካ ባሕሎች ዘላቂ መሆናቸውን ሲያስረዱ፣ በማከልም የማሕበራዊ ፍትሕ መሣሪያ የሆነው የኦሮሞ ‘ኮቱ-ዱፌ’ የስብሰባ ስርዓት በሰነድ ተዘጋጅቶ መዳበርና ለብዙ ሰው መዳረስ በየዕለቱ በግጭት ለምትናጠው አገራችንና ዓለማችን እጅግ ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በመጽሐፉ የተዳሰሱ አንኳር ጉዳዮች እንደሚከተለው ለመዳሰስ ተሞክሯል።
‘ኮቱ-ዱፌ’ የኦሮሞ ልኂቃን አባቶች የሚጠቀሙበት የግልግል ዳኝነት ስርዓት ነው ማለት ይቻላል። በኦሮሞ ባሕል አባቶች ተራ ንግግር ካልሆነ በስተቀር ከኹለት ሰዎች በላይ የሚደረግ የሐሳብ ልውውጦችና ውይይትን ጨምሮ ማንኛውም ንግግሮች የሚካሔደው በስብሰባ መልክ ነው። ይህም ለስብሰባ የሚሰጡትን የላቀ ሥፍራ ያስገነዝበናል።

የአገር በቀል ዕውቀት ስርዓት የሆነው ‘ኮቱ-ዱፌ’ የተለያዩ ስርዓቶች አሉት። ከነዚህም ስርዓቶች አንዱ ‘ሸነቸ’ (የአምስት ስርዓት) ይጠቀሳል፤ ይህንንም አስመልክቶ ጸሐፊው ይህን ይላሉ፦ “የሸነቸ (የአምስቶች ስርዓት) በሽምግልና፣ የግልግል ዳኝነት፣ የማስታረቅ እና ጥቁር ደም የማድረቅ ሒደት፣ የጉማ ባሳ ስርዓት፣ የማስማማት ቃል የማስገባት፣ ቃል እንዳይፈርስ የማስማል (የማስገዘት) ወይም መገንታ ሒደት ሁሉ የሚስተናገድበት አሠራር ስለሆነ በማኅበረሰቡ የማኅበራዊ ግንኙነት እና የዕለት ከዕለት መስተጋብር ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነ የሰላምና ደኅንነት ማስከበሪያ መሣሪያ ነው።”

በ‘ኮቱ-ዱፌ’ ስርዓት መሠረት የሚደረጉ ስብሰባዎች በሙሉ እንደ ሌሎች ስብሰባዎች የጋራ የሆነ የስብሰባ መሪ በጸሐፊው አባባል ሙሴ አልባ የሆነ የስብሰባ ስርዓት ሲሆን፥ ሊቀ መንበር የማያሻው ሁሉም ነገሮች በሚደረስበት የእልባት ነጥብ እና ሥምምነት መፈታት ስለሚችል ነው።

ሌላው በመጽሐፉ የተጠቀሰው ጉዳይ የአባ ገዳ መዋቅርና አሠራር ማሳያ ሲሆን፥ በገዳ ስርዓት ያለው የይግባኝ ሰሚ አካላት መዋቅር በዝርዝር ቀርቧል። ከዚህ በተጨማሪም የኦሮሞ ገዳ የአስተዳደር ስርዓት የመዋቅር አባላት እና በገዳ ስርዓት አስተዳዳደሪ ለመሆን የሚያስችሉ መሥፈርቶች የተገለጹ ሲሆን፥ ከዚህ በተጨማሪ የኹለቱን ታላላቅ የገዳ መሪዎች አበርክቶ፣ ማለትም የአባ ገዳ ወላቡ ጀሉ እንዲሁም የአባ ገዳ መኮ ቢሊ አበርክቶዎች በዝርዝር ቀርበዋል።በአባ ገዳ መኮ ቢሊ የተዘጋጀው ባለ 65 ገጽ የገዳ ሕግጋትና መመሪያ ሰነድ በመጽሐፉ በአባሪነት ተያይዟል።

የ‘ኮቱ-ዱፌ’ የስብሰባ ስርዓት በሐሳብ አሰጣጥ ላይ የራሱ ሕግጋት ያሉት ሲሆን፥ እነዚህም የአነጋገር፣ የአለባበስ፣ የአቀማመጥ፣ የአለንጋ አያያዝና አቀማመጥ ስርዓት ምን እንደሚመስል በዝርዝር በመጽሐፉ ተዳሷል።

በገዳ ስርዓት መሠረት በብቃት አስተዳደር ኃላፊነትን በቅጡ ለመሸከም፣ እንዲሁም የሥራ ድርሻን በአግባቡ ለመወጣት ከልጅነት ጀምሮ በልምምድ፣ በዕውቀት፣ በዕድሜ ተሞክሮና በስርዓት ታንፆ ማደግ የግድ ነው። የገዳ ስርዓት የዕድሜ እርከንና ሥልጠናን በተመለከተ ዘርዘር ባለ መልኩ በመጽሐፉ ሰፍሯል።

በገዳ ስርዓት የሚገኙ የተለያዩ የዕርቅ ተቋማትም በመጽሐፉ ተገልጸዋል። እነዚህ ተቋማት ችግር አስቀድሞ እንዳይፈጠር መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ናቸው። ድንገት እንኳን ችግር ቢፈጠር በግልግል እና ዳኝነት በማስታረቅ ለኅብረተሰቡ ወርቃማ የሆነ የዕርቅ ስርዓት መዘርጋት እንዲቻል በር ከፍቷል። ከእነዚህ የዕርቅ ተቋማት መካከል ዋና ዋናዎቹ በመጽሐፉ ተገልጸዋል። እነሱም የጉማ ጫቹና ከለቻ (ሲቄ) የሴቶች መብት ማስከበሪያ፣ ለቦኩ (የቃሉ መንፈሳዊ መሪ ቤተሰቦች) የወረ አያና ቤተሰቦች፣ ጃርሱማ የሽምግልና ስርዓት እና ሸነቸ በዋቢነት ይጠቀሳሉ።

በ‘ኮቱዱፌ’ ስርዓት በውይይት ወቅት ካሉ ስርዓቶች መካካል ‘ሀብልቱ’ እና ‘ሂፈታ’ ይጠቀሳሉ። በሀብልቱ (በይደር) የሚጠየቀው በብዙ ምንክንያቶች ነው። ከነዚህ ምክንያች መካከል የተቀጣጠለ ሐሳብ ቀዝቅዞ እንዲቀርብ፣ የተረሳ ሐሳብ በሚኖርበት ጊዜ ለማስታወስና ከዚህ ባለፈም ተጨማሪ የውይይት ኃይል ለመጨመር ስለሚያሻ ነው። ጸሐፊው ይህንን ስርዓት በማስረጃ በማስደገፍ ሲያቀርቡ፥ የአርሲ አካባቢ ሽማግሎች ሀብለቱ ዱቢን (ነገር በይደር) የሚሉባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ተጠቅሰዋል።

የመርማሪ ወገን ኃይል ለመጨመር ሲፈልግና ሲያስፈልገው (ሂፈታ) እንዲቻል፥ በወቅቱ ለተደራዳሪዎች ያልመጣላቸው ሐሳብ እያደር በትውስታና እርጋታ ሐሳብን ለማሰባሰብ እንዲቻል፣ በወቅቱ ግሎ ተጋግሎ በኃይል ፈንቅሎ ወጥቶ ከእውነት መሥመር የሚያፈናቅለን የንዴት ሥሜት በጊዜ ርዝመት ለመቀነስ፣ ብሎም ለማብረድ እንዲቻል ማሰብ እንዲችሉ ታሶቦ ይደረጋል። የሂፈታ (የኃይል መጨመር) ስርዓት ደግሞ ጉዳዩን እያስታመሙ በማዋዛትና በትግስት እንዲቆይ በማድረግ እውነት ትወጣ እና ፍትሕ ይሰፍን ዘንድ አቅም የሚገነባበትን መላ ለመዘየድ ያስችላል።

በ‘ኮቱ-ዱፌ’ የስብሰባ ስርዓት የተቃውሞ ድምፅ የማሰማት ሒደት እንደሌሎች የስብሰባ ስርዓቶች አሉት። ይህም ስርዓት በመጽሐፉ እንዲህ ተገልጿል፦ “(ናጉምጉማሲስ) ማስተካከያ ተቀበለኝ ይሉና ይጠይቃሉ፤ ‘ሙርቲ’ (ውሳኔ) አሰሚው ከተቀበለው ‘ጉንጉሜ ከጉንጉሜ ሮቡ ዋቃ’ (አስተካክል ብየሀለሁ አስገምግም የሚዘንብ ሰማይ ነው) በማለት ይተርትና ማስተካከያውን ያቀርባል። ውሳኔ አሰሚው ማስተካከያውን በመቀበል፣ የሚስተካከሉትን በማስተካከል፣ የማይስተካከለውን ማብራሪያ እንዲሰጥ ውሳኔውን አሰምቶ ይጨርሳል።”

በ‘ኮቱ-ዱፌ’ ስብሰባ ውስጥ ለመሳተፍ የሚችለው ቢያንስ ዕድሜው 32 ከሆነ ነው። ከዚህ በመለስ ከ16 እስከ 24 ዓመት የደረሰ ልጅ ከወላጅ ጋር በመሆን ማዳመጥ ይችላል። ከ24 እስከ 31 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ደግሞ ሐሳብ መስጠት ይችላሉ፤ ውሳኔ ግን አይሰጡም።

በኦሮሞ ባሕል ከተራ ጫወታና ተራ ንግግር በስተቀር ማንኛውም የሐሳብ ልውውጥ በኮቱ ዱፌ ደንብና ስርዓት ተከትሎ የሚካሔድ ሲሆን የግዴታ በኮቱ ዱፌ የስብሰባ ስርዓት የሚያልፉ ጉዳዮች የሚከተለት ናቸው። ዳኝነት ሲታይ፣ ሕግ ሲደነገግ (ሴረ ቱማ)፣ የሠርግ ሥነ ስርዓት (ፉዳ ሄማ)፣ በለቅሶ ስርዓት፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር በሚያሻበት ሁኔታ ሲያጋጥም፣ ‘ኮቱ-ዱፌ’ እንደሚተገበር በመጽሐፉ ተገልጿል። በ‘ኮቱ-ዱፌ’ ስርዓት ውስጥ የግል ወይም ቡድን ሥራ አስፈፃሚ ዓይነት ስብሰባ የለም የ‘ኮቱ-ዱፌ’ ሥልጣን የአባላት ሁሉ ድምር ሥልጣን (Collective Power) እንጂ የሌላ እንዳልሆነ ተገልጿል፤ የፈላጭ ቆራጭነት አባዜ በ‘ኮቱ-ዱፌ’ ስርዓት ውስጠ ቦታ የለውም።

በ‘ኮቱ ዱፌ’ ትውፊታዊ የዳኝነት ስርዓት ውስጥ አንድ ውሳኔ ሲወሰን አንድ በአንድ በስብሰባው ውስጥ ያሉት አባላት በሙሉ መሥማማት አለባቸው፤ አንድም ተከራካሪ ካለ ስብሰባው በውሳኔ አይደመደምም። በ‘ኮቱ-ዱፌ’ ስርዓት የአብላጫው አመራር፣ የአናሳው መብቶች መከበር (majority rule, minority rights) የሚለው ብሒል ቦታ የለውም።

ጸሐፊው በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ የጎንዮሽ ጉዳት ማሳያ በማለት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን በዋቢነት ይጠቅሳሉ። የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ግጭት ጦርነት በተከሰተበት ወቅት ከኢትዮጵያ በኩል ጦርነቱን ለመጀመር ውሳኔ ስለሚያስፈልገው ጉዳዩ ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀርቦ ነበር። በወቅቱ የድርጅቱ ሊቀመንበር የጦርነቱን መካሔድ ተቃውመው እንደነበር ይነገራል። ቢሆንም ጉዳዩ በአብላጫ ድምፅ ስለተወሰነ ጦርነቱን ለማስፈፀም ተገድደዋል። በወቅቱ የፓርላማ አሠራር ስርዓት ባይኖር እና የገዳ ስርዓት ‘ኮቱ-ዱፌ’ የስብሰባ ስርዓት ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ፥ የተለየ እና የተሻለ ውጤት ያስገኝ ነበር ሲሉ ይሞግታሉ።

በ‘ኮቱ-ዱፌ’ የድምፅ አሰጣጥ እጅ በመቀሰር የሚሰጥ ድምፅ የለም። የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ በሁርሳ (በቃል ንግግር) በማድረግ የሚሰጥ ሐሳብ ነው እንደ ድምፅ የሚቆጠረው። ንግግሩ ደግሞ በገምናዎች (በብልሕና አስተዋይ ሰዎች) ይገመገምና ለውሳኔ መብቃት አለመብቃቱ ይወሰናል። የማጠቃለያው ሐሳብ የሚሰጠው ታኣው (ሁሉም ተሰብሳቢ) ሲቀበለው እንጂ በገምናዎች ውሳኔ ብቻ አይሆንም። በመሆኑም የ‘ኮቱ-ዱፌ’ የድምፅ አሰጣጥ ሙሉ ድምፅ (ያለ ተአቅቦ፣ ያለ ተቃውሞ) ሆኖ ነው የሚሰጠው። በድምፅ አሰጣጡ ውስጥ የድምፀ ተአቅቦ ወይም ተቃውሞ ከተገኘበት ስብሰባው እንደገና አብስሎ ይወያይበታል እንጂ ውሳኔ ሆኖ አያልፍም።

በ‘ኮቱ-ዱፌ’ የስብሰባ ስርዓት ምርመራ ሊደረግባቸው የሚገቡ የጠብ፣ የቅያሜ፣ ግጭት መነሻዎች በመጽሐፉ ተገልጸዋል። እነሱም ‘ሆሪ’ – በሀብትና ንብረት የተነሳ ቅያሜ፣ ‘ሙፊ’ – ኩርፊያ፣ ‘ገልቴ’ – የዕለት ግጭት፣ ‘ሸምቴ’ የተከማቸ ቂም በቀል፣ ‘ላፌ’ – ከፍተኛ ግጭት ሲፈጠር፣ እንዲሁም ‘ጉማ’ – ከፍተኛ ደረጃ ወንጀል ናቸው።

ለማጠቃለል ያህል ይህን የመሰለ አገር በቀል የዕርቅ፣ የዳኝነት እና የገዳ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያለ መልካም አስተዳዳር ለምን በኦሮሚያ ደረጃ እንኳን አልሰፈነም ሲሉ የሚጠይቁት ደራሲው፣ የምዕራባውያንና የአውሮፓዊያን የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገልበጥና ለማምጣት ከመባዘን ባለፈ “ሰነፍ እረኛ ከቅርብ ትቶ ከሩቅ ይመልሳል” እንዳይሆን አገር በቀል የዕርቅ፣ የዳኝነት እና የፍትሕ አስተዳደር ስርዓትን ከዘመኑ ጋር በማሰናሰል ተግበራዊ ማድረግ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

ቶፊቅ ተማም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው  tofick1970@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here