የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተመድ ለክልሉ ሕዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ

0
1003

ረቡዕ የካቲት 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በየጊዜው ጦርነት እየተከፈተበት የሚገኘውን የአፋር ሕዝብ እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ።

በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ከርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና ከተለያዩ የጎሳ መሪዎች ጋር ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ በተመለከተ ውይይት አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ህወሃት የክልሉን ድንበር ተሻግሮ በአሁኑ ወቅት በአምስት ወረዳዎች ላይ ጦርነት መክፈቱን ገልፀዋል።

ጦርነት ከተከፈተባቸው ወረዳዎች ሦስቱ ጦር ያልሰፈረባቸው የንፁሀን መኖሪያ መንደሮች መሆናቸውን እና ጥቃቱም ንፁሀን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አፋር ክልል መጥተው ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል ስለሚደርስበት መንገድ ከመነጋገር ባሻገር ወረራ የተፈፀመበትን የአፋር ሕዝብ ስለመርዳት እንዲያስቡም ጠይቀዋል።

አፋር ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ እንዲሄድ መንገድ ከማመቻቸት ጀምሮ ማከማቻ መጋዘኖች እንዲኖሩ ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የትግራይ ሕዝብም ጠላት የሆነው ህወሃት ግን የተከፈቱ መንገዶች ላይም ጦርነት እንደከፈተ ገልጸዋል።

ተመድ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ሄደው ያልተመለሱ መኪኖቹ ምን እየሠሩ እንደሆነ እና ዕርዳታዎችም ለጦርነት ዓላማ ሳይሆን ለንፁሀን ዜጎች ስለመድረሳቸው ሊያጣራ ይገባልም ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአፋር ክልል ለአገር ትልቅ ዋጋ እየከፈለ ያለ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ማለታቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ በበኩላቸው፣ ጦርነቱ በሚቆምበት እና ሰላማዊ ውይይቶች በሚኖሩበት ሁኔታ ላይ ይሠራል ብለዋል።

ሰብዓዊ ድጋፎች ጦርነት ባለበት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ንፁሀን እንዲደርስ እንሠራለን ሲሉም አክለዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here