የኦነግ ሠራዊት አባላት ወደ ካምፕ እየገቡ ነው ተባለ

0
602

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከመንግሥት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ከአንድ ሺህ በላይ የሠራዊት አባላትን ወደ ካምፕ ማስገባቱ ተገለፀ። ይህ ተግባር እስከ የካቲት 14 እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ቤት መግባቱን ተከትሎ ከሠራዊት ትጥቅ መፍታት ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ከመከሰታቸውም ባለፈ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ የሰው ሕይወትን የቀጠፉ ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደነበሩ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ሰላምና እርቅ ለማውረድ በሚል ኮሚቴ ተዋቅሮ የማስታረቅ ሥራውን ከጀመረም ሰንብቷል። ሐሙስ ጥር 17 በመንግሥትና ኦነግ መካከል ሰላም መውረዱ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሲበሰር ከተቀመጡ ስምምነቶች መካከል አንዱ ኦነግ ሠራዊቱን በ20 ቀናት ወደ ካምፕ እንዲያስገባ የሚል ነበር። ይህን ተከትሎ ነው የግንባሩ የሠራዊት አባላት ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ መግባት የጀመሩት ተብሏል።

በኦነግና በመንግሥት መካከል የወረደውን እርቅ በበላይነት ሲያስተባር የነበረው ኮሚቴ የኦነግ ሠራዊት አባላትን ወደ ካምፕ ለማስገባት ወደ 12 ዞኖችና 22 የተመረጡ ወረዳዎች ስምሪት መጀመሩን አስታውቋል። ከእነዚህም መካከል ወለጋ፣ ጉጂ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ከረዩ ይገኙበታል ተብሏል። በአማራ ክልል ከሚሴ የሚገኙትን በተመለከተ በቀጣይ ከአማራ ክልል ጋር እየተነጋገሩ እንደሚሰሩም የኮሚቴው አመራሮች ተናግረዋል።

የታጠቁት የኦነግ አባላት ከረቡዕ የካቲት 6 ጀምሮ ወደ ካምፕ እንዲገቡ ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ ከየካቲት 12 እስከ 14/2011 ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ሠራዊቱን አጠቃልሎ ወደ ካምፕ ለማስገባት እቅድ መያዙ ታውቋል። ይህም ቀድሞ በነበረው የአምቦው እርቅ ከተያዘው የ20 ቀናት እቅድ የተወሰነ ጊዜ ጭማሪ ማስፈለጉን ተከትሎ የተጨመረ ቀን ስለመኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሠራዊቱ ወደ ካምፕ ሲገባ ትጥቅ እየፈታ መሆኑንና ትጥቁ መልሶ በሕግ አግባብ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚሰጥ እንደሚሆንና ወደ ካዝና እንደማይገባ ስምምነት መኖሩን የኮሚቴው ሰብሳቢ አባ ገዳ ሰንበቶ ገልፀዋል። ታጣቂዎቹ ሲገቡ ትጥቃቸውን ለአባገዳዎች እያስረከቡ እንደሚገቡም ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here