በመንግሥትና በትግራይ አመራሮች መካከል ንግግር መቀጠሉን ተመድ አስታወቀ

0
718

ሐሙስ የካቲት 3 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ አመራሮች መካከል ንግግር መቀጠሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

ይህን የተናገሩት በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ ናቸው።

ምክትል ዋና ፀሐፊዋ አዲስ አበባ ውስጥ ትናንት ረቡዕ የካቲት 02 ቀን 2014 ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በአማራ፣ በትግራይ እና በአፋር ክልሎች ጉብኝት ማድረጋቸውን እና ከክልሉ አመራሮች ጋርም መገናኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ጦርነቱ የተጎዱትን የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎችን ከጎበኙ በኋላ ለሰላም ተስፋ እንዳለ የገለጹ ሲሆን “በእርግጥከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው አንፃር አነስተኛ ግጭቶች ናቸው የሚታዩት” ብለዋል።

አክለውም “በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ” በማለት አስረድተዋል።

ከትግራይ አመራሮች፣ ከአማራ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ያደረጉት አሚና መሐመድ ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ዋና ፀሐፊዋ በክልሎቹ ከሴቶችና ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሲባዊ እንዲሁም ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንደማይታገስ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች አጋርነታቸውን የገለጹት አሚና፣ በጦርነቱ ሳቢያ በሴቶች ላይ የደረሰውን ግፍና በደል እንዲሁም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለማቃለል ድርጅታቸው መፍትሄ በማፈላለግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ሴቶች ካለባቸው ህመም እንዲፈወሱ በተሃድሶ እና በመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ውስጥ እንዲካተቱም አመራሮቹን አሳስበዋል። በተጨማሪም ተመድ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሰላም ጥረትም ይደግፋል ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች በቅርቡ ለሰላም ያሳዩትን እርምጃ በበጎ እንደሚያዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከቀናት በፊትም መግለጻቸው ይታወሳል።

ሰላም ለማስፈን ግጭቱን እንዲሁም ተኩስ ማቆም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ የተናገሩት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተፋላሚ ወገኖች ይህንን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here