ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ስደተኛ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተገለፀ

0
825

👉በጥቃቱ የአንድ ሠው ህይወት ሲያልፍ፣ ሁለት ሠዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ሶስት ህፃናት ታፍነው መወሰዳቸውም ተገልጿል

ሐሙስ የካቲት 3 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው በመግባት በዲማ ስደተኛ ካምፕና በጎግ ወረዳ ጥቃት ማድረሳቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡገቱ አዲንግ፥ በጥቃቱ የአንድ ሠው ህይወት ሲያልፍ ሁለት ሠዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና ሶስት ህፃናት ታፍነው ተወስደዋል ሲሉ ገልፀዋል።

ክልሉን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያጋራው ድንበር ሰፊና ክፍት ስለሆነ ታጣቂዎች በተለያየ ጊዜ ተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪም በጎግ ወረዳ ከፑኝዶ ከተማ ወደ ቴዶ ቀበሌ በሚንቀሳቀስ ሞተር ሳይክል ላይ ባደረሱት ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንም ገልፀዋል።

በቅርቡ መነሻውን ከጋምቤላ ከተማ አድርጎ ወደ ኑዌር ዞን በመጓዝ ላይ ባለ የጭነት መኪና ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ባደረሱት ጥቃት የመኪናው አሽከርካሪ እና ረዳቱ ህይወታቸው እንዳለፈም ተናግረዋል።

ጥቃት ያደረሱትን ግለሰቦች የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች ተከታትለው አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ጠንካራ ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ህብረተሰቡም ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግስት በአሁኑ ሰዓት ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመጠቀም ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ሥራውን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በየቦታው ሾልከው ሊገቡ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here