የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ80 ዓመት ጉዞ

0
2469

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ ፈር ቀዳጅ ሲሆን፣ በመንግሥት ባለቤትንት የሚተዳደር የፋይናንስ ተቋም በመሆን በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ነው። የ80 ዓመት ዕድሜ ያለው ባንኩ፣ ዕድሜ ጠገብ ከሆኑ የመንግሥት ድርጅቶች ተርታ የሚሰለፍ መሆኑን ከታሪኩ መረዳት ይቻላል።

በ1935 እንደተቋቋመ የሚነገርለት ንግድ ባንክ፣ በወቅቱ በአንድ ሚሊዮን ማርትሬዛ ካፒታል የተመሠረተው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ፣ የብሔራዊ ባንክን እና የንግድ ባንክን ሚና ሲወጣ ቆይቶ፣ በ1955 ለኹለት ተከፍሎ የኢትዮጵያ ገንዘብ ቁጥጥርና የማሳተም ኃላፊነት ለብሔራዊ ባንክ፣ የንግድ ሥራ ዘርፉ ደግሞ ለአሁኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሠጠቱን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ የባንክ ሥራ ከ117 ዓመት በላይ ማስቆጠሩ የሚነገር ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ የተቋቋመው በ1897 መሆኑ በታሪክ ይነገራል። በወቅቱ የነበረው የመጀመሪያው ባንክ “ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ” የሚባል ሲሆን፣ በወቅቱ ባንኩንም በበላይነት ይቆጣጠርና ይመራው የነበረው በወቅቱ የእንግሊዛውያን ንብረት የነበረው የግብጽ ብሔራዊ ባንክ እንደነበር ይነገራል። በ1924 አፄ ኃይለሥላሴ ባንኩን ከእንግሊዝ ማኅበር በመግዛት “የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ” ተብሎ እንዲሠየም ማደረጋቸው ይነገራል።

በወቅቱ በአንድ ሚሊዮን ማርትሬዛ የተመሠረተው የዛሬው ግዙፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአሁኑ ጊዜ 824 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ፣ 1.1 ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት፣ ከአንድ ሺሕ 800 በላይ ቅርንጫፎች፣ እንዲሁም ከ34 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አፍርቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በ1935 ሕጋዊ ሠውነት ካገኘ በኋላ ሥራውን ቀድሞ የኢትዮጵያ ባንክ እና አቢሲኒያ ባንክ ይሠሩበት በነበረው ሕንፃ ውስጥ በ1 ሚሊዮን የማርትሬዛ ብር ካፒታል ሲጀምር፣ 43 ሠራተኞችና ኹለት ቅርንጫፎችን በመክፈት እንደነበር ባንኩ ከሠሞኑ የ80ኛ ዓመት ክብር በዓሉን እና የአዲሱ ሕንፃ ምርቃት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

በወቅቱ ኹለት ዓይነት አገልግሎቶችን እንዲሠጥ የተደረገ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዋና የንግድ ባንክ ሆኖ መሥራት ሲሆን፣ በ1938 መንግሥት ለባንኩ ብቸኛ የገንዘብ ማተም ሥልጣን መስጠቱን ተጠቅሞ ገንዘቦችን ያትም ነበር። በኹተኛ ደረጃ ጠቅላይ ባንክ በመሆን የሚታተሙትን የብር ኖቶች እንዲቆጣጠር፣ የኢትዮጵያን የውጭ መጠባበቂያ ገንዘብ እንዲይዝና ከንግድ ባንክ ሥራዎቹ በተለይ የመንግሥት የገንዘብ ወኪል ሆኖ እንዲሠራ የማዕከላዊ ባንክ ተግባራትን አጣምሮ ይፈጽም ዘንድ ተልዕኮ ተሠጥቶት ነበር።

በዚህ መንገድ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ80 ዓመት በላይ በመሪነት የቆየ አገልግሎት ሰጪ ባንክ ለመሆን በቅቷል። በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በጀመሩባቸው በ1950ዎቹ ለተቋቋሙት ፋብሪካዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዋነኛ የብድር አቅራቢ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ሲሆን፣ የባንክ ኢንዱስትሪ 57 ከመቶ ድርሻ እንደያዘም ተነግሮለታል።

ባንኩ የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በአዲስ አበባ ያስገነባውን ሠማይ ጠቀስ ሕንፃሠ የካቲት 6 በማስመረቅ እንደሚያከብር አስታውቋል። የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃው ከአራት ሺሕ በላይ የባንኩን የዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች አጠቃሎ የመያዝ አቅም እንዳለው ተገልጿል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ “LEED” ሠርተፍኬት ማግኘቱን ባንኩ አስታውቋል። “LEED” ሠርተፍኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው የአረንጓዴ ግንባታ ሥርዓት ሲሆን፣ በዩናይትድ ስቴትስ አረንጓዴ ሕንፃ ካውንስል የሚሰጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ “LEED” የምስክር ወረቀት ብቃቱ የተመሰከረለትና ሠፊ ተቀባይነት ያለው የምዘና ደረጃ ነው።

ባለ 53 ወለሉ የባንኩ ሕንፃ 209.15 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ 4B+G+48 የወለል ብዛት ያለው ዋናው ሕንፃ፣ (G+6 floor) 2,000 ሰዎች የሚያስተናግድ የስብሰባ ማዕከል እና (G+8 floor) የንግድ ማዕከል ሕንፃዎችን የያዘ ነው። የሕንጻው ገፅታ የአፍሪካ አልማዝ ቅርፅ እንዲኖረው መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም ሕንፃዎቹ በተለየዩ የኪነ ጥበብ ውጤቶች እንዲታጀቡ መደረጉ ተገልጿል።

ከአፍሪካ ሠማይ ጠቀስ ሕንፃዎች አንዱና በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን (G+48) ሕንፃ ግንባታ አጠናቆ ለምረቃ አብቅቷል። የባንኩ ሕንፃ ግንባታ አምስት ዓመት ከ11 ወር የፈጀ ሲሆን፣ ግንባታውም 303.5 ሚሊዮን ዶላር በጀት ፈሰስ እንደተደረገበት ባንኩ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (AAiT) ጂኦፊዚካል እና ጂኦቴክኒካል ምርመራ እና መዋቅራዊ ዲዛይን የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርግ ኃላፊነት የነበረው ሲሆን፣ ለግንባታ ኢንዱስትሪ የእውቀት ሽግግር ለማድረግና ለማጠናከር ተጨማሪ የዲዛይን ክለሳዎችን እና ውል አስተዳደር እንዲያከናውን መደበኛ የቴክኒክ አማካሪ ኃላፊነት ለዩኒቨርስቲው መስጠቱን ባንኩ አስታውሷል።

የሕንፃው ግንባታ በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ከ8 አገራት የተውጣጡ 28 ታዋቂ የግንባታ ግብዓት አቅራቢዎች ተሳትፈዋል። ከነዚህም መካከል 9 የአሜሪካ፣ 11 የቻይና፣ 3 የጀርመን እና 3 የፈረንሳይ አቅራቢዎች ይገኙበታል። የሕንፃዎቹ ምድረ ግቢ ለኹሉም ሕብረተሰብ ክፍት ሆነው በቀላሉ የሚታዩ፣ የዋናው ታወር 48ኛ ወለል ለሕዝብ ክፍት የተደረገ ሲሆን፣ አዲስ አበባና አካባቢዋን መመልከቻ ከዘመናዊ የሬስቶራንት አገልግሎት ጋር ተዘጋጅቷል ተብሏል።

ባንኩ ለትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ዋነኛ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ድጋፍ አቅራቢ ነው። በተለይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ በርካታ የመስኖና ግድቦች፣ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የመኖሪያ ቤት ፕሮጅክቶች በባንኩ የፋይናንስ አቅርቦት የሚደገፉ ናቸው ተብሏል።

በወቅቱ ከፍተኛ በሚባል ኢንቨስትመንት፣ በ4 ሚሊዮን ብር የተገነባውና በ1958 በንጉሰ ነገስቱ ተመርቆ ለሥራ የበቃው ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ የሚገኘው ወርቃማ ሕንፃ፣ በባንኮች የቢሮ ሕንፃ ግንባታ ታሪክ የመጀመሪያውና ትልቁ እርምጃ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት በርካታ ሕንፃዎች የተገነቡ ሲሆን፣ በተለይ ለገሀር አካባቢ የተሠራው ክቡ ሕንፃ በመባል የሚታወቀው የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ተጠቃሽ ነው። በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የባንኩን አገልግሎት የሚያቀላጥፉና ለየከተሞቹ ውበት የሚሆኑ በቁጥር በርካታ ሕንፃዎችም በግንባታ ሒደት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here