በአዲስ አበባ በ280.4 ሚሊዮን ብር የመገጣጠሚያ መንገዶች ማሻሻያ ሊሠራ ነው

0
1016

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በከተማዋ በተለይም በሥራ መውጪያ እና መግቢያ ሠዓት በመጋጠሚያ ሥፍራዎች የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ እና የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ 26 ቦታዎችን በጥናት በመለየት የመንገድ ደኅንነት ማሻሻያ ሥራዎችን ሊሠራ መሆኑን አስታወቀ።

በ208 ሚሊዮን 452 ሺሕ 330 ብር ጨረታውን ካሸነፉ ከሦስት የተለያዩ ተቋራጮች ማለትም፣ ታደሰ ወንድወሰን ጠቅላላ ተቋራጭ፣ ሔዛኔር ኢንጂነሪንግ፣ ቴዎድሮስ ስሜነህ አለማየሁ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ጋር ኤጀንሲው ውል ማሠሩ ታውቋል።

ውል ያሠሩ ተቋራጮች የሚረከቡት ፕሮጀክት በተለያዩ ሦስት ‹ሎቶች› የተከፋፈለ የትራፊክ ሲግናል ኢንስታሌሽን እና የእግረኛ ደኅንነት ማሻሻያ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ዓላማ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚስተዋለውን የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ እና የትራፊክ ግጭት አደጋን ለመቀነስ ያለመ ነው።

የማሻሻያ ሥራው ዋና ዋና ተግባራት ከፍሰት እና ከደኅንነት አንፃር የሚከናወኑ ሲሆን፣ የምልክት እና ማመላከቻዎች ተከላ፣ ቀለም ቅብ፣ የመንገድ አካፋይ ብረት፣ የእግረኞች መሔጃ የመንገድ ንጣፍ እና የእግረኞች መከለያ አጥር እና መሠል ሥራዎች እንደሚተገበሩ ለማወቅ ተችሏል።

የመንገድ ደኅንነት ማሻሻያ የሚደረግባቸው 26 ሥፍራዎች መሆናቸው የታወቅ ሲሆን፣ ከነዚሀም መካከል ገርጂ መብራት ኃይል፣ ሚናሮል ሕንፃ፣ ሲኤምሲ ሳፋሪ፣ ቦሌ መድኃኒዓለም፣ አስኮ መናኽሪያ፣ ልደታ ኮንደሚኒየም፣ ሰባተኛ፣ ሰሜን ማዘጋጀ፣ ጎፋ መብራት ኃይል፣ ቤተል አደባባይ፣ ጨርቆስ እና ሳሪስ አደይ አበባ የሚገኙበት ሲሆን፣ የ26ቱንም መጋጠሚያ ሥፍራዎች ሥራ ለማጠናቀቅ ስምንት ወራት እንደተያዘለት በሥምምነቱ ተጠቅሷል።

በውል ሥምምነቱ ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ኤጀንሲው የሚጠበቅበትን ቅድመ ዝግጅት እንዳደረገ እና በቀጣይም ከኤጀንሲው የሚጠበቀውን ኹሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀው፣ ፕሮጀክቱ በተቀመጠው ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሠጥ ውል ተቀባዮቹ ተቋራጮች ሥራውን በፍጥነት እና በጥራት ለመሥራት የበኩላቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ሥራው የሚከናወንባቸው ሥፍራዎች የትራፊክ ፍሰታቸው በቀላሉ የሚታወክ በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያካሒዱ እና በሥራው ወቅት ለባለሙያዎች አስፈላጊ የሆኑ የደኅንነት (የሴፍቲ ቱል) ግብዓቶችን በማማሏት ፕሮጀክቱን እንዲያከናውኑም ጭምር አሳስበዋል።

ኤጀንሲው ከዚህ በፊትም ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ምክንያት የሆኑ እና የእግረኞችን ደኅንነት የበለጠ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አራት አደባባዮች ላይ ማሻሻያ አድርጎ ወደ ትራፊክ መብራት በመቀየሩ በአካባቢዎቹ ላይ ሠላማዊ እና ተቀባይነት ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ ማረጋገጥ መቻሉም ይታወሳል።

ከዚሀ በተጭማሪ ከ159 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት በተለያዩ አካባቢዎች የእግረኛ መንገዶች ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ለማወቅ ተችሏል ።

የእግረኛ መንገድ የመልሶ ግንባታና ጥገና ሥራ እየተከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ ከሜክስኮ – ትንባሆ ሞኖፖል፣ ከአፍሪካ ኅብረት – ኦርቢስ፣ ከቀይ መስቀል – ኢትዮ ቴሌኮም ዋና መሥሪያ ቤት፣ ከፖስታ ቤት – ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር – ጨፌ ሜዳ፣ ከውኃ ልማት – አትላስ – ሩዋንዳ፣ ከጉርድ ሾላ – 49 ማዞሪያ፣ ከጐሮ – አይ.ሲ.ቲ ፖርክ የሚጠቀሱ ናቸው። አሁን ላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ እና በመገንባት ላይ ያሉ የእግረኛ መንገዶች በአጠቃላይ 9.6 ኪ.ሜ ርዝመት እና በአማካይ 3.5 ሜትር የጐን ስፋት አላቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here