የ“ሰካራም ስንኞች” ግጥም መጽሐፍ ዳሰሳ

0
1144

ክፍል ኹለት

ባለፈው ሣምንት ዕትማችን ሰካራም ስንኞች የተሠኘውን የሣራ ሞገስ የግጥም መድብል ላይ ጸሐፊው ያላችውን ዕይታ ማጋራታቸው ይታወሳል። በአጠቃላይ ስለ መድብሉ፣ ሰለ ገፁ ሽፋን፣ ስለ ዳሰሰቻቸው ጉዳዮች በአብዛኛው መልካም ጎኗን አንስተዋል። ኹለተኛው የዳሰሳ ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው ቀርቧል:: መልካም ንባብ።

ሣራ ሞገስ በአጠቃላይ ስለ ተፈጥሮና ስለ ሰው ልጅ ባህርይ የራሷን ዕይታ ጀባ ብላናለች። ዕግረ መንገዷን የዘመኑን ፖለቲካም አልማረችም። ሣራ ለግጥሞቿ የተሳካ ኹነት [context]/situation/background] ወይም መንደርደርያ በመፍጠርና ያንንም በግሩም ስንኞቿ ስሜት በሚኮረኩርና በሚያጓጓ መንገድ ገልጻ ጽፋለች። በዚህ ዘርፍ እጅግ የተሳኩ ግጥሞችን በመድረስ ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩምን የሚያህለው የለም። እሷም በዚህ ዘርፍ ተሳክቶላታል ብንል አላጋነንንም። ለምሳሌ አምባገነን መሪ፣ የቡስካ ላይ ትዝብት፣ የደስታችን ፍሬ፣ በፍቅራችን እደሜ፣ ናፍቆትህ፣ እስቲ እንዴት ነሽ በለኝ፣ የወጥቶ አደሩ ሚስት፣ ውዳሴ ለፍቅሯ፣ አንተን ለመርሳትና እቀናለሁን መጥቀስ ይቻላል። በተለይ “እቀናለሁ” የተሠኘው ግጥም እንደ “አምባገነን መሪ” በተሳካ ኹነት ተሰንዷል ። ይህም ከኑሯችን ጋራ እያስተሳሰርን፣ ራሳችንንም ኹነቱን ባለመርሳት ቆፈን ውስጥ ከተን፣ ተመስጠን፣ እንዲሁም ተስበን እንድናነባት አድርጋለች። ይህንንም በሚከተሉት ምሳሌዎች ማብራራት ይቻላል።

ምሳሌ 1-“አምባገነን መሪ” በተሠኘው ግጥሟ ውስጥ አንድ አምባገነን ሾፌር ህልቆ የሰው መዓት አሳፍሮ፣ ከብዙዎች በተለየ በተጠቀሱ ሰባት ዓይነት /ሙያ/ ያላችው ሰዎች ታክሲው ውሰጥ ተሳፍረዋል። እነሱም ለበሽተኛው መድኃኒት የሚያዝና ሪፈር የሚጽፍ ሐኪም/ ሥራ ያጣ ግን ቅን የሆነ ሐኪምና ርህራሄው ከክብሩ፣ ሙያው የበለጠለት/ ፣ ለማጅ ጋዜጠኛ፣ በዛለ ጉልበት ላይ የቆሸሸ ቱታ የለበሰ ላብ አደር፣ ከባሏ ተጣልታ የተደበደበች ሚሰት፣ ጠባሳዋን በጋቢም ያይደለ በቁስል ማሸጊያም ያይደለ ግን በነጠላ የሸፈነች ‹ለሷ ቁስል ይሆን መድኃኒት ያዘዘው/ሪፈር የሚፅፈው ? ፣ ጠና ያሉ አዛውንት፣ ልፋቱን የሚቆጥርና የላቡን ክፍያ ያልበላ መምህር…ለስንዝር መንገድ ሙሉ የሚያስከፍል ረዳት፣…መጓዝ የምንሻ፣ ለውጥን የምንሻ እኛም አብረን ተሳፍረናል። ከነዚህ ኹሉ ሰዎች ግን ላባደሩ ብቻ ላለመክፈል ይከራከራል። ለምን ? ለዛች ስንዝር መንገድ እየቃመ የሙሉ የሚያስከፍል ረዳት ስለቆመ? እንጃ! ። ሌሎቹ ሰልችተዋል። ለምን? በሰለቹና በሚከራከሩ ሰዎች መሃል አዛውንቱ ያወራሉ። ሰሙም አልሰሙም ማውጋታቸውን አላቋረጡም። አዛውንት ሲያወራ የሚሰሙ ዘመነኛየ ዘመን ተጋሪ ዜጎቸ ታክሲውን ሞልተዋል። ሾፌሩም በአርምሞ ይነዳል።
“…ለውጥን የምትሻ አንተም ተሳፍረሃል፣
እኔም አብሬ አለሁ፣
ላልሄድንበት መንገድ ሙሉ ከፍያለሁ”
(ገጽ 11) እያልን፣

አማሬያዊ ትርጉሙ ለትራንስፖርት ይሁን እንጂ፣ ሊያውም አንድ ተጓዥ ካሰበበት ሳይደርስ የሚከፈል ክፍያ። በፍካሬያዊ ትርጉሙ “ሰለተሳፈርን ብቻ” ላልተገለገልንበት፣ መልስ ላላገኘንለት፣ ዋስትና ላላገኘንበት… በከንቱ ያጨበጨብንበትን ዘመን ያሰታውሳል። ስለዚህ ሣራ የዘመንን መንፈስ አላሰተጋባችምን? በርግጥ አምባገነን መሪ የተሰኘው ግጥም ኹነት ነፍሰ ሄር ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ወቅት [1996 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር አማካይነት በተደረገ ንግግርና ርዕይ 2020 በተሰኘ መጽሐፍ ከተጠቀሰው ] ንግግራችወ ጋራ ይመሳሰላል። አይበለውና ከአዲስ አበባ ድሬደዋ የሚጓዝ አንድ የአውቶብስ ተጓዥ ቀድሞ ይክፍልና በመንገድ የመኪና አደጋ ቢገጥመው [ ያው ኢትዮጵያ ውስጥ 70 ሰዎች ከ10,000 ተሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ ይሞታሉ ተብሎ ይታሰባል ] (ዳመን 2014፣ ፍሰሃና ስለሺ 2014፣ በያየህይራድ 2017 ገጽ 276 የተጠቀሰ] ቀብድ ከፍሎ ይሞታል ማለት ነው! ከፍሎ መሞት! የላይ ቤት ትራንስፖርት ክፍያ ይሆን? የሚገርመው ደግሞ ኹሉም ወደ ሥራ ለመሄድ አይደለም ታክሲ የሚሳፈሩት፣ ወደ ቤት ለመግባት እንጂ። ወደ ቤት፣ ወደ እናት ቤት፣ ወደ አገር ቤት፣ ወደ ራሳችን፣ ወደ ልጅነታችን፣ወደ በጎነታችን፣ወዳልተበላሸንበት ዘመን እንመለስ እያለችን ይሆን? ለዚያውም ሕልቆ ሆነን! ለምን? ለማረፍ፤ የሰበሰብነውን ጥሪት ከቤተሰቦቻችን ጋራ ለመጋራት፣ለመወያየት…። ነገር ግን ልፋቱን የሚቆጥርና የላቡን ክፍያ ያልበላ መምህር፣ ጠና ያሉ ዝም ብለው የሚያወሩ አዛውንት፣ ማከሚያ /ቦታ?/ አጥቶ ታክሲ ውስጥ ሪፈር የሚፅፍ ሐኪም፣ በዛለ ጉልበቱ ወደ ቤት የሚገባ ላብ-አደር፣ ተደብድባ ወደ ቤት የምትገባ ሚሰት፣ ሰለዚህ የተደበደበችው የት ነው ማለት ነው? ክብራችንን የምናጣው የት ነው? በአገራችን ወይስ በባዕድ አገር። ያም ሆነ ይህ ግን ሲመሽ ወደ ቤት እንከተታለን።ብዙ ዓይነትም ሰዎች ሆነን፤ ብዙ ዓይነትም ጉዳይ ገጠሞን፤ ከፍቶንም ደልቶንም… እንደማለት። ቤት በኢትዮጵያውያን ሥነ ልቡና ብዙ ነገር ማለት ነውና። እነኳን በሕይወት ከሞትንም በኋላ አስከሬናችን ቤት ገብቶ የፍቅር አንባ ፈሶለት በክብር ወደ ዘላለም ማረፊያው ይሸኛል።

“ኑሮ ኑሮ ከመሬት፣
ዞሮ ዞሮ ከቤት” አንደምንለው ማለት ነው።
ምሳሌ 2- ሣራ አካታች ናት፤ በግጥሞቿ። ሕዝብን ለቱሪዝም ስንል ምን ያህል እንደጎዳን በቡሰካ ላይ ትዝብት ግጥሟ በአንዲት የሐመር እናት ውሎ እነዲህ ትለናለች፡-
“.. ጉልቻ ሳትጎልት ጭሷን ሳታጫጭስ፣
ፍየሏን ሳትፈታ ቡሰካን ሳትቀሰቅስ ፣
ለጆቿን አስትላ ሴቲቱ ውጥታለች፣
ከማጀት የለችም
ከቱሪስት ካሜራ ሽርፍራፊ ሳንቲም፣
አምሰት ብር ልትለቅም…
ምን ተሰምቶሽ ይሆን ?
በራስሽ ሜዳ ላይ የልጆችሽ ክብር፣
በአምሰት አምሰት ብር ወጥቶ ሲቸረቸር!?” (ገጽ 14-15) በማለት ሙሾ ታወርዳለች።

ምሳሌ -3 እቀናለሁ ደግሞ በተለየ መንገድ፣ ማራኪ የሆነ ኹነት ተገልጦበታል። አንዲት አፍቃሪ ሚሰት በአራት ሴቶች ስትቀና ያስነብበናል። መቼም ምን አንላለን?። ቅናት ቤትና ውስጥ ከቤትም ውጪ ልቧን ሲቧጥጣት አንገረማለን። ቤት ውስጥ በቤት ሠራተኛዋ። በቤት ሰራተኛዋ እጅ “ ሽንኩርቱ ተልጦ፣ ተከትፎ፣ ተቁላላልቶ፣ከእንጀራ ከውኃ ፍርፍሩ ተሠርቶ” ቁርስ ላይ ሲበሉ የምትወደው ከንፈር በቀይ ቅባት ወዝቶ የተሠራና ከባለቤቷ ጋራ የምትቋደሰው ምግብ የቅናት ምንጭ ይሆናል። እሷም፡-

(1)
“እንብላ ስትለኝ፣
ከፍርፍሩ ጀርባ ከትፎ ያቁላላው እጅ
ጠላት መስሎ ታየኝ” እያለች በውስጧ ትብሰለሰላለች።

(2)
ከቤት ከወጣች በኋላ በሏ ናፍቋት ስልክ ስትደውልለት፣ “ሴት ዘፈን እንኳ ደፍራ የማትጋብዘው የቴሌዋ… የደወሉላቸው ደመበኛ መስመር ተይዟል” ስትላት፣

(3)
ከዚያም ሌላ አማራጭ ትወስዳለች። ይህም በቢሮ ስልክ መደወል ነው። ትደውላለች። የምታነሳው የባልየው ጸሐፊ /መቼም ወንድ ጸሐፊ የለም አይደል ? አሁንም ቅናት አናቷ ላይ ይወጣል፣
“ጸሃፊህ አነሳች፣
የፈረደባት ሴት እሷም ጥርሴ ገባች “ ፤ ከዚያም የመጨረሻ የምትለውን አማራጭ ትወስዳለች። ይህም በአሳቻ ሰዓት ቀጥሮ እሱን ማግኘት ይሆናል። ታደርገዋለች።

(4)
ድንገት ቀትር ላይ ናፍቆቷ ሲፀና፣ፍቅሯ ሲበረታ ቅጥራው፣ ምሳ አብራ ትበላለች። እሱ በተከፈለ ልብ እጆቿን ጨብጦ ፍቅሩን ያወጋታል፤ ‹ደራሲዋ ግን የምትረዳው እሱ በሥራና በሷ የፍቅር ምሳ መሃል እንደዋለለ ነው› ። በወንበራቸው ትይዩ ቆንጅየ ልጅ ተቀምጣለች። እዛ ምግብ ቤት ውስጥ ቆንጅየ ልጅ ብቻዋን? እሱ ቀጥሯት ይሆን ሚሰቱ በመሃል ናፍቀህኛል ብላ የተከሰተች? እሱም የዋዛ አይደለም፣ ፍቅርን የደልላል። ሚሰቱን ይሸነግላል። በኹለት ልብ ኹለት ሴቶች መሃል፣ ለተሻለ ነገ? የተሸለ ድራማ ይተውናል። አልተሳካለትም። ሚሰት ቀድሞ ገበቷታል። እሱ ቀድሞ በሀፍረትም፣በሽሽትም፣ ለሥራም ቀድሞ ክካፌው እብስ ይላል። በተከፈለ ልብ ነበርና ቁልፍ፣መነጽርና ባረኔጣ ይረሳል፤ ምናልባት በዚህ ቅጽበት ሚስትም ታውቅ ኖሮ ጨርሳ እነድትወጣ በነገራት ብርጭቆ ውስጥ ባለ ውሀ፣/ መጠጥ የመሆን ዕድል አለው /ቆንጅየዋ ልጅ ሸሚዝ ላይ ትደፋባታለች። ትበሰብሳለች። ለምን ሦሰት ነገር

/ምናልባታም ኹሉንም የያዘውን ዕቃ ብሙሉ/ ሊረሳ ቻለ? ስለተጨናነቀ ነዋ! ፣በሌላ በር ተመልሶ /ሚስቴ ከካፌው ወጥታለች በሚል ግምት/ ምናልባትም ቆንጅየዋን ልጅ ለማግኘት ይመለሳል። ባልም ይሄኔ የበሰበሰችውን ቆንጅየዋን ልጅና ሚሰቱን በዓይኑ በብሌኑ ይመለከታል፤ ሚሰትም ትነግረዋለች። ምንም አጸፋ አይመልስም። ሚስትም፡-
“የልጅቷ ሸሚዝ በሽብሾ ያየሀው፣
ጨርሼ እንድመጣ ያዘዝከኝ ብርጭቆም ባዶ የነበረው
ስዓቱን ነግራብኝ ከዓየኔ ስታርቅ ነው::”
(ገጽ 64-65) ብላ የቅናቷን ጥግና የፍቅሯን ልዕልና ትገልጣለች።

ሣራ ኮረኳሪ ግጥሞችን የሰጠችንን ያህል፣ አንዳንድ ከመጸሐፍ የማንጠበቃቸውን ስህተቶቸም ሠርታለች። ለምሳሌ ቀላሉን የቃላት እረማት አልተወጣችውም። ለምሳሌ ዝናም ለማለት ዝናብ ፣ረጅም ለማለት እረጅም። በአንድ ግጥም ውሰጥ የተደጋገሙ ቃላት መብዛት፣ ገላጭና በግጥሙ ውስጥ [body] የተጠቀሱ ሐረጎችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በርዕሶቿ መጠቀም። ለምሳሌ ገጽ 4-11፣14፣16፣17፣18፣1920፣21፣24፣26፣27፣28፣30፣37፣40፣42፣48፣60፣68። ይሄም አንባቢ ርዕሱን ብቻ በማንብብ ሊባል የተፈልገው ነገር ቀድሞ እነዲገባውና ቅኔውን በአቋራጭ አንዲረዳ ዕድል ይከፍታል። መበዛቱ እነጂ ቢያንሱ ችግር ባላስከተሉ ነበር። ሌላው ደግሞ ክዚህ ቀደም የተገጠሙና የተዘፈኑ ዘፈኖችን ሐሳብ በዚህ የግጥም መድብል ውስጥ በድጋሚ ማንበባችን ነው። ለምሳሌ የሚያስደሰት ስቃይ (ገጽ 16)፣ ረጅም ጥበቃ (ገጽ 18)፣ ቀን ሲጥል (ገጽ 20)፣ የኛ ዘመን ፍቅር (ገጽ 35) እና ፍቅር አግራችንን ወደ አፍቃሪ በራሱ ሲመራ። አንዳንድ የፍሰት ችግር ያለባችውንም አንብበናል። እጅግ የሚያናደው ደግሞ ከኹለት ሦስተኛ በላይ ግጥሞቿ በሳድስ ሁሄያት መድፋታቸው ነው። የሚቅጥሉ ሥራዎቿን በመናፍቅ ምናልባትም ስል ሴተነት/እናትነት በደረሰችውና ብቸኛ የኹለት መሰመር ግሩም ግጥም ዳሰሳችንን እንዝጋ። ቢተሰብ በምትሰበስብ እናት፣ወጣትንትን በትዳር አደብ ባሰገዙ ሚስቶች፣ ወንድ ካገቡ በኋላ ጥሪት እንዲያካብት ዕደሜ ለሰዉ ሴትነቶች በተቅኘችው፡-

“በዚህ ሁሉ ቃላት በዚህ ሁሉ ቅኔ፣
የምትፈታኝ አንተ የምቋጥር እኔ።” (ገጽ 36)
ሠላም!
የፅሁፉ አዘጋጅ የሆኑትብ በድሉ አበበን በ tatyetgaab@gmail.com ኢሜል አድርሻ ያገኙዋቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here