የእለት ዜና

ለለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ አዲስ የትግበራ እቅድ ተዘጋጀ

ሥራ አቁሞ የሚገኘው የለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ማውጫን ወደ ሥራ የሚመልስ እቅድ በጥናት እንዲሁም በድርድር ተደግፎ መዘጋጀቱን ሜድሮክ ጎልድ ይፋ አደረገ።
ሜድሮክ ጎልድ ይህን ያስታወቀው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ለአልሚዎች እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በማስወገድ አዲስ ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ ለመተግበር የካቲት 6/2012 ኢሊሌ ሆቴል ባለሀብቶችን ባወያየበት ወቅት ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት በዚህ መርሃ ግብር በመድረኩ ላይ ስለ ጥናቱ ውጤት በዝርዝር አልቀረበም።

የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ማምረቻ፣ ከማምረቻው የሚወጡ ኬሚካሎች በአካባቢው በሚኖር ማኅበረሰብ ላይ ባደረሰው የጤና ቀውስ ምክንያት ከግንቦት 1/2010 ጀምሮ ላለፉት ኹለት ዓመታት ታግዶ ቆይቷል።

ይህ የሥራ እቅድ እንዲተገበር የጠየቀው ሜድሮክ ጎልድ ያቀረበው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኹለት ጥናቶች ተካሂደዋል።

የእነዚህ ጥናቶችን አስተያየቶች እና ውጤቶች መሰረት በማድረግ የማዕድን፣ ነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና በድርጅቱ የትግበራ ዕቅድ መዘጋጀቱን እና የመንግሥትን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ጥናቱንም መሰረት በማድረግ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እና ድርጅቱን እንዲሁም መንግሥትን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የትግበራ ዕቅድ መሆኑን ያስረዳው ሜድሮክ ጎልድ፣ ይህ በፍጥነት ተተግብሮ ወደ ሥራ ለመግባትም ጠይቋል።

ሜድሮክ ጎልድ የትግበራ እቅዱ የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች በሚመልስ መልኩ የተሰናዳ ሲሆን፣ ይህም ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ መክፈልን ያጠቃልላል፤ እንደ ወረቀቱ ከሆነ።
የማዕድን ማውጫዎቹ ወደ ሥራ የሚገቡ ከሆነ በፈረንጆቹ 2025 ለአንድ ሺሕ 567 ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ያስታወቀ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል እስከ 11 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንደሚያደርግም ገልጿል።

የማዕድን፣ ነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ጥናቱ በመከናወን ላይ መሆኑን ያነሳ ሲሆን፣ ከጥናቱ የሚገኘው ውጤት ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ገና መሆኑን አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኪሮስ ዓለማየሁ፣ ጥናቱ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ማምረቻው ፍቃዱ ይመለስለት አይመለስለት የሚለውን ለመወሰን ግን ጊዜው አሁን አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ድርጅቱ በአካባቢው የወርቅ እና የነሐስ ማዕድናትን ያመርት የነበረ ሲሆን፣ ከማምረቻው በሚወጡ ኬሚካሎች ምክንያት በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት መድረሱን ምክንያት በማድረግ የማዕድን፣ የነዳጅ እና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የማዕድን ማውጫ ፕሮጀክቱ እንዲታገድ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

በስፍራው ለ20 ዓመታት ማዕድን ሲያወጣ የቆየው ሜድሮክ ጎልድ፣ ከኹለት ዓመታት በፊት ፈቃዱ ለቀጣይ 10 ዓመታት መታደሱን ተከትሎ በአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ተቃውሞ ከፋብሪካው የሚወጡ ኬሚካሎች በሰዎች፣ በእንስሳት፣ እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ ተፋሰሶች ላይ ብክለት አስከትሏል የሚል ነበር። በብክለቱ ምክንያትም አዲስ የሚወለዱ ሕጻናት ለአካል ጉዳት እንዲዳረጉ ሆነዋል የሚሉት ተጠቃሽ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች ነበሩ።

በወቅቱ የፈቃድ እድሳቱ ከመደረጉ በፊት ጥናቶች ተደረገው የነበረ ቢሆንም፣ ጥናቶቹ በቂ ባለመሆናቸው እና ትክክለኛ ያልሆነ ውጤትን ያመላከቱ እና ጥልቀት የሌላቸው በመሆናቸው ፍቃዱ ለጊዜው ታግዶ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግበት መወሰኑን በወቅቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።
ሚኒስቴሩ የማኅበረሰቡ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን ተገንዝበናል፣ ማምረቻው በአካባቢው ላይ ስላሳደረው ተፅዕኖ ጥናት ሊደረግ ይገባል በሚል ፈቃዱ ለጊዜው እንዲታገድ ማድረጉ አይዘነጋም።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!