ሐሙስ የካቲት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ ከተማ ሽጉጥና የክላሽንኮቭ ጥይቶችን ይዞ ሊሄድ ሲል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተከሳሽ በ9 ዓመት ፅኑ እስራትና በ80 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አንዲቀጣ ተወስኖበታል።
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አበበ ቦጋለ የተባለው ተከሳሽ የጦር መሳርያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀፅ 4/1 እና 22/3 ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ መጋቢት 22/2013 ከቀኑ 4:00 ሰዓት ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ ውስጥ ወደ ወልቂጤ ከተማ ለመጓዝ ቅጥቅጥ አውቶብስ ላይ ተሳፍሮ እያለ፤ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ተጠራጥረው ድንገት ሲፈትሹት ይዞት በነበረው ሻንጣ ውስጥ “ሪታይ ፍልከን” የተባለ ሽጉጥ ከመሰል 4 ጥይቶች እና ብዛታቸው 300 (ሶስት መቶ ) የሆኑ የክላሽንኮቭ ጠመንጃ ጥይቶች ይዞ እጅ ከፍንጅ በመገኘቱ በፈፀመው የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳርያ መያዝና ማዘዋወር ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶበት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቧል።
ተከሳሹ በተመሰረተበት ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃሉን ተጠይቆ ወንጀሉን መፈፀሙን ሙሉ በሙሉ ባለማመን ክዶ የተከራከረ ሲሆን፤ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዳሉ ያላቸውን ዝርዝር የሰው፣ የሰነድና በክሱ ላይ የተጠቀሰው የጦር መሳርያ በኢግዚቪት ማስረጃነት አቅርቦ አሰምቷል።
ይህንንም ተከትሎ ፍርድ ቤት ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሹ ማስተባበል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽን ጥፋተኛ ነህ ሲል ፍርድ በመስጠት ተከሳሽን ያርማል መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል ያለውን በ9 ዓመት ፅኑ እስራትና በ80 ሺህ ብር የገንዘብ እንዲቀጣ እንደወሰነበት ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



