አርብ የካቲት 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ያለመ በቀጣይነት በየወሩ በባለድርሻ አካላት የሚካሄድ የዉይይት መድረክ ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት በተሰኘ ድርጅት ተጀመረ።
“ልዩ ምልከታ” በተለያያ የትምህርት መስክ የሰለጠኑ ምሁራንና ባለሞያዎችን አንድ ላይ በማምጣት የሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚያካሂድ ሲሆን፣ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች፣ የክልል መንግስታት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የምርምርና አካዳሚክ ተቋማት፣ የወጣቶችና የሴቶች ቡድኖች የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የመጀመሪያው “የልዩ ምልከታ” ፎረም የሥራ ዕድል ፈጠራ ልማት በኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ተግዳሮት እና መልካም አጋጣሚዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ዛሬ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
“ልዩ ምልከታ” የወጣቶች ሥራ-ፈጠራንና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት፣ ባለ-ድርሻ አካላት በቅርበት በመወያየት፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለማሻሻል፣ ተቋማዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ፣ ሽርክናና አጋርነትን ለማበረታታት እንዲሁም የፋይናንስ ተደራሽነትን እና ከፍተኛ ጥራት ያለው የንግድ ልማት አገልግሎትን ለመስጠት የተቋቋመ የውይይት መድረክ ነው።
መድረኩ የወጣቶች የፋይናንስ ተደራሽነት በማስፋት ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት የሚያስችል አገልግሎት እንዲኖር፤ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ መላ ሥራዎቻቸውን ለማበልፀግ እንዲችሉ መድረኩ የበኩሉን አስተዋፅዖ ያደርጋል ተብሏል።
ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ጥናትና ምርምር፣ ሥልጠናዎችንና የንግድ ልማት አገልግሎት የሚያከናውን የአማካሪዎች ተቋም ነው።
ተቋሙ የሥራ ፈጠራና ወጣቶች ልማት ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከነዚህ ጥረቶች ውስጥ አንዱ የሥራ ዕድልና የሥራ ፈጠራን ለማበረታታት ባለ ድርሻ አካላት በቅርበት በመወያየት የተሻለ ከባቢ እንዲፈጠር “ልዩ ምልከታ” የተባለ ወርሃዊ መድረክ ማዘጋጀቱን በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



