• ኮሚሽኑ እርዳታን በደብዳቤ ጠይቆ የተከለከለ ክልል የለም ብሏል
“በብሔር ትግራዋይ በመሆናቸው ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተፈናቀሉ 77 ሺሕ የትግራይ ተወላጆች አሰቸኳይ ድጋፍ ቢፈልጉም፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ ዜጎቼ ብሎ አላያቸውም፤ መልሶ ለማቋቋምም እየሠራ አይደለም›› ሲል የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወቀሰ፡፡
የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሊያ ካሳ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ “ትግራዋይ በመሆናቸው ብቻ ከተለያዩ አካባቢዎች በሚሰነዘርባቸው ብሔር ተኮር ጥቃት ተፈናቅለው በክልሉ የሚገኙት 77 ሺሕ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብና መጠለያ ድጋፍ የሚፈልጉ ቢሆንም የፌደራሉ መንግሥት የዕለት ደራሽ እርዳታ በማቅረብም ይሁን በዘላቂነት በማቋቋም አላገዘንም” ብለዋል፡፡
የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ምክንያት ከአማራ፣ ኦሮሚያና የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ወደ ትግራይ የሔዱ እንዳሉ የሚናገሩት ኃላፊዋ “እነዚህን ተፈናቃዮች እንደክልል መንግሥት ለማቋቋም እየተሠራ እንጂ እንደማዕከላዊ መንግሥት ተፈናቃዮቹ የእኔ ዜጋ ናቸው ብሎ ድጋፍ የሚያደረግበትና እነሱን ለማቋቋም የሚሠራበት ሥራ የለም” ሲሉ የክልሉ መንግሥት ቅሬታ እንዳደረበት ገልፀዋል፡፡ ድጋፍ ለማድረግ እየሠሩ ያሉት የክልሉ መንግሥት፣ የተለያዩ ተቋማትና ባለሀብቶች መሆናቸውንም በመጥቀስ የፌደራሉ መንግሥት “እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አለማድረጉን” አክለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ በብሔር ትግራዋይ ይሁኑ እንጂ በዜግነት ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ማዕከላዊው መንግሥት ዜጎቼ ሊላቸው ይገባል ለሚሉት ሊያ አስቸኳይ ድግፍ ለማድረግ በፌደራል ደረጃ ለተዋቀረው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጥያቄውን አቅርበው እንደሆነና ከፌደራል መንግሥት ጋር ስላላቸው ትብብር አዲስ ማለዳ ጥያቄ ሰንዝራለች፡፡ ቢሮ ኃላፊዋ “ይታወቃል፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ ላይ ምን ያህል ተፈናቃይ እንዳለ መረጃው አለው” ያሉ ሲሆን ለማገዝ አለመሠራቱን በመግለፅ ይተቻሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የኅዳር 21/2011 መግለጫ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ኹለት ነጥብ አራት ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የተፈናቀሉት የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን እንጂ ትግራዋይ ብቻ ናቸው ወይ ለሚለው ጥያቄ ሊያ ትግራዋይ ብቻ ተፈናቅለዋል ብለው እንደማያምኑ በመግለፅ የትግራይ ተወላጆች ግን በተለየ መልኩ ዘመቻ እንዲከፈትባቸው እየተደረገ የተፈናቀሉ ናቸው ሲሉ መልሰዋል፡፡ “የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ እንዲፈናቀሉና እንዲጨፈጨፉ በተለያዩ ሚዲያዎች ሳይቀር እየተቀሰቀሰ ነው፡፡ ትግራይ ላይ እንዲዘመት በግልፅ ታውጇል” የሚሉት የቢሮ ኃላፊዋ “ኢትዮጵያዊያን ግን አስተዋይና አርቆ አሳቢዎች በመሆናቸው በተቻለ መጠን የትግራይ ሕዝብ እንዳይጠቃ አቃፊ ሲሆን ነበር” ሲሉም አክለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ሆኖም በአብዛኛው ግን እንዲፈናቀሉ ተደርጓል ይህም የብሔር ጥቃት ነው” ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከሦስት ዓመታት ወዲህ በኦሮሚያና ሱማሌ፣ በደቡብና ኦሮሚያ፣ በአማራና ቤንሻንጉል አካባቢዎች በሚነሱ ብሔር ተኮር ግጭቶች በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስለመፈናቀላቸው አስታውሰው የትግራይ ተወላጆችን የሚለየው “ሕዝቡ እንደተፈለገው አላደረገውም እንጂ በዶክመንታሪ ፊልም ሳይቀር ትግርኛ ተናጋሪዎች እንደበደሉ በመግለፅ በግልፅ በትግራይ ተወላጆች ላይ እንዲዘመት መሠራቱ እንደሆነ” ያክላሉ፡፡
ለተፈናቃዮች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎችን የማድረሱ ኃላፊነት የተሰጠው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ከክልሎች በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት ድጋፍ ከማድረግ አለመቆጠቡን ገልጿል፡፡ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖች እርዳታ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የፌደራሉ መንግሥት እርዳታ የሚሰጠው ክልሎች ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አሳውቀው በሚጠይቁት ደብዳቤና የተረጅዎች ቁጥር መሰረት እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
“ክልል ጠይቆ ፌደራል እምቢ የሚልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም” ያሉት ደበበ ከምንም በላይ ለሰው ቅድሚያ ስለሚሰጥ መጠባበቂያ ክምችት ባይኖር እንኳን ተበድረው እንደሚረዱ አክለዋል፡፡
የኮሚሽኑ አንዱ መጋዘን መቀሌ እንደሚገኝ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በትግራይ ክልል ለሚገኙ 74 ሺሕ ተፈናቃዮች በቀረበው ጥያቄ መሰረት የምግብ እርዳታ እንዲደርሳቸው መደረጉንም ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ምን ያህል ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የጠየቅናቸው የሕዝ ግንኑነት ኃላፊው ቁጥሩ ስለሚቀያየር ይህን ያህል ነው ለማለት ያስቸግራል ብሏል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011