ፋብሪካው በመዘጋቱ የአንድ ሺሕ ሠራተኞች ዕጣፈንታ አደጋ ላይ ወድቋል

0
503

ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን ላለፉት 15 ወራት ሥራ በማቆሙ የተነሳ ከ354 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበትና ድርጅቱም ደምወዝ መክፈያ ገንዘብ በመቸገሩ ከ1 ሺሕ በላይ ሠራተኞቹ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።
የድርጅቱን 90 በመቶ በላይ ገቢ የሚሸፍነው ከአዲስ አበባ 550 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የቀንጢቻ ፋብሪካዎች በመዘጋታቸው ድርጀቱ ከታንታለም ምርት ማግኘት የነበረበትን ወደ ስምንት ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማጣቷን ማወቅ ተችሏል።

በተለይም ከማዕድን የውጭ ንግድ ከሦስት ዓመታት በፊት ያስገኝ የነበረው ዓመታዊ ገቢ ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ የነበረ ቢሆንም ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ በ10 ዕጥፍ ዝቅ በማለቱ የአገሪቷን የማዕድን ኢንዱስትሪ የበለጠ ችግር ውስጥ እንዳይከተው ተሰግቷል።›

በታኅሣሥ 2010 በኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ በተፃፈ ደብዳቤ መሰረት የተዘጋው የታንታለም ማምረቻው፤ ዝቃጭ ማስወገጃ ግድቡ መሙላቱ ሰው ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ለመዘጋቱ እንደ ምክንያት ተነስቶ ነበር።

በየወሩ ወደ 10 ቶን ታንታለም የሚያመርተው ድርጅቱ፤ ፋብሪካው ከተዘጋ አንስቶ ምንም ዓይነት ገቢ ባለማግኘቱ ንግድ ፍቃድ እስካሁን እንዳልታደሰ ማወቅ ተችሏል። ኮርፖሬሽኑ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በጉጂ ዞን ሰባቦሮ ወረዳ በ5 ነጥብ 3 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን የምርት ፈቃድ ክልል ውስጥ ለ28 ዓመታት የታንታለም ምርት በማምረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ የመንግሥት ልማት ድርጀቶች አንዱ ነው።

ይሁን እንጂ ድርጅቱ በከፊል ከዚህ ቀደም በ2001 እንዳጋጠመው ወደ ዝቃጭ ማጠራቀሚያው የሚገባው አሸዋ እና አፈር መሙላት የተነሳ ወሃ ወደ ውጭ በመፍሰስ አካባቢ እንዳይበክል በመስጋት በመዘጋቱ ሥራ ለማቆም መገደዱ መገለጹ አይዘነጋም።

በተጨማሪም ማስተካከያ እርምጃዎችና ማስፋፊያ ለማድረግ በፓርላማ 208 ሚሊየን ብር ቢፈቀድለትም ባለመጠቀሙ ተመላሽ መሆኑን ምንጮች ገልፀዋል። የኮርፖሬሽኑ ማዕድን ይዞታ ለባለፉት 15 ወራት በሕገ ወጥ ማዕድን ቆፋሪዎች በመዘረፉ በእንዲህ ዓይነቱ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለአደገኛ ጨረር መጋለጣቸውን ማወቅ ተችሏል።

የድርጀቱ የታንታለም ፋብሪካዎች ሕገ ወጥ በሆኑ ኃይሎች ዘረፋ ከመፈፀሙም በላይ የፋብሪካውን የመነቃቀልና የመሰባበር ተግባራቶች መፈፀማቸው ታውቋል። ከዚያ ባሻገር ኮርፖሬሽኑ የታንታምና ሊትየም ማዕድናትን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጨረታ በማውጣት አጋር ድርጀቶች ፍለጋ ላይ ቢሆንም፤ የማዕድን ይዞታው በሕገ ወጥ የማዕድን ቆፋሪዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመዘረፉ አንዳንዶችም በድርጅቱ ይዞታ ላይ ተደራቢ ፈቃድ ይዘው በመቅረባቸው ዕቅዱን ለማሳካት እየተቸገረ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።

የተፈጠረው ችግር ሥራ ሳይቋረጥ ለመፍታትና በሠራተኛው የሥራ ዋስትና አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የኮርፖሬሽኑ አመራሮች ከመንግሥት ልማት ድርጀቶች ኤጀንሲና ከማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ጋር ውይይት ቢያደርጉም ምንም መፍትሔ ሊገኝ አልቻለም።

ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጠይባ ሃሰን በተገኙበት በተደረገ ውይይት ችግሩን በጥናት ለመፍታት እንዲሁም ድርጅቱ በአፋጣኝ ወደ ሥራ የሚገባበበት መንገድ እንዲፈለግ አቅጣጫ ቢቀመጥም የዞኑም ሆነ የወረዳ አስተዳደሮች ተፈፃሚ አላደረጉም።

ኮርፖሬሽኑም ችግሩን በመረዳት ጥገናዊ ለውጥ ለማድረግ ጥያቄ ቢያቀርብም በአካባቢው ገብቶ ሥራ ለማከናወን የዞኑ አስተዳደሮች ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሊፈፀም አለመቻሉን አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ምክትል ኃላፊ ቦና ያዴሳ ግን ኮርፖሬሽኑ ተጨማሪ ጥናት አቅርብ ቢባልም ስላላቀረበ እንደተዘጋ ገልጸዋል። ነገር ግን በማዕድን ማምረቻ ውስጥም ሆነ ግድቡ ላይ ያሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የኅብረተሰቡ ጤና ላይ ሊያደርሱት የሚችሉት የጤና ችግሮች በመጥቀስ ለፀጥታ ኃላፊዎች ቢያሳውቁም፤ በሚገባ አለመፈፀሙን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል፤ በአሁኑ ወቅት በጉጂ ዞን ያሉት የድርጅቱ ሁለት ፋብሪካዎች ከፍተኛ አመራሮች እየደረሰባቸው ባለው ዛቻና ጥቃት በቦታው መቆየት ባለመቻላቸው ሸሽተው በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት እንደሚገኙ ማወቅ ተችሏል። በቦታው ያለው ፀጥታ ኃይልም ችግሩ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ለድርጅቱም ሆነ ለሠራተኞች ጥበቃ ማድረግ አለመቻሉን ማወቅ ተችሏል። ይህንን ችግሮች በተመለከተ በተደጋጋሚ በሲሲ ቲቪ ካሜራ በመቅረፅ በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ ኮርፖሬሽኑ ለፌዴራል ፖሊስ ማቅረብ ቢችልም ሊፈታ አልቻለም።

ሆኖም ግን በፌዴራል የመከላከያ አባላት በተወጣጡ ኃይሎች በተደረገ ኦፕሬሽን የፀጥታና ንብረት ማውደሙ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱን ምንጮች ገልፀዋል።
ከወቅታዊ ችግር ባሻገር ነዋሪዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በአካባቢው የሚገኙ ማኅበረሰቦች የአክሲዮን ባለቤት እንዲሆኑ በአዳማ በተደረገው ውይይት ስምምነት ላይ ቢደረስም ተፈፃሚ ሊሆን አለመቻሉ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ከታንታለም ፋብሪካው በተጨማሪ፤ ኦሮሚያ ክልል አናሶራ ወረዳ የካኦሊን ፋብሪካው በአካባቢ ኅብረተሰብ በተነሳ ተቃውሞ የተነሳ መዘጋቱ ታውቋል።
ለውሃ ማጣሪያነት የሚውል አልሙኒየም ሰልፌት ለማምረት የሚያገለግለው ካኦሊን የሚያመርተው ፋብሪካው ሥራ በማቆሙ የተነሳ የአዋሽ መልካሳ ምርት መቀነሱ ባደረግነው ማጣራት ማወቅ ተችሏል።

በድርጅቱ የተመረተ ወደ 263 ቶን ካኦሊን ለገበያ መቅረብና ለፋብሪካዎች መከፋፈል ቢኖርበትም የአካባቢው ፀጥታ ኃይል ሰላም ማስከበር ባለመቻሉ ምርቱን አውጥቶ ማከፈፋፈል አልተቻለም። በዚህም የተነሳ ፋብሪካው ኪሳራ ውስጥ መግባቱን ምንጮች ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here