“መንግሥት የሠራተኞቼን ደኅንነት አላስጠበቀልኝም” የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍልና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሠራተኞቹ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት በሚወጡበት ወቅት መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ እያደረገላቸው አለመሆኑን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አስታወቀ።

የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊ እንግዳ ማንደፍሮ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ባለፈው ወር በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ጉዳት ለደርሠባቸው በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና በዋግ ኽምራ ዞን፣ እንዲሁም በአፋር ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

አቶ እንግዳ አያይዘውም፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና እና ባሌ ዞን፣ በሱማሌ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ምግብነክ የሆኑ ነጭ ዱቄት ፣ዘይትና የስንዴ ምርቶች ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም ከ 27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማውጣቱን ነው ማኅበሩ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

አቶ እንግዳ አክለውም፣ ተቋሙ የተቋቋመበት ዓላማ የተፈጥሮና ሠው ሠራሽ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ጉዳት ለደርሰባቸው የሕብረተሠብ ክፍሎች የቻለውን ኹሉ የሠብዓዊ ዕርዳታ ማድረግ ነው ብለዋል።

በዚህ መሠረት፣ ዜጎች ጉዳት በሚደርስባቸውና ዕርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ፣ ከዕለት ዕርዳታ እስከ መልሶ ማቋቋም ሥራ በመሥራት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበርና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበሩ ጦርነት ባለባቸው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመንቀሳቀስ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለቆሠሉ የሠራዊት አባላት የመጀመሪያ የሕክምና ዕርዳታ በመሥጠትና ወደ ጤና ተቋማት በማድረስ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ማስቻሉን ገልጿል።
ተቋሙ፣ በኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተጠፋፉ ሠዎችን በስልክ ከማገናኘት በተጨማሪ መልዕክቶቻቸውን በማድረስ እየሠራሁ እገኛለሁም ነው ያለው።

ከአንድ ሳምንት በፊት የማኅበሩ የቄለም ወለጋ ቅርንጫፍ ንብረት የሆኑና ፣ለሠብዓዊ ድጋፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አምቡላንሶች በውል በማይታወቁ አካላት መዘረፋቸው ቢጠቀስም፣ ዝርፊያውን የፈፀሙ አካላት እስካሁን እንዳልታወቁና ወንጀለኞቹን ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑ ነው የተገለፀው።

የሚመለከታቸው አካላት አምቡላንሶቹ ተመልሰው የተለመደውን የሠብዓዊ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲያደርጉና ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን ለሕግ አሳልፈው በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማኅበሩ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በጎ ፍቃደኛና መደበኛ ሠራተኞቹ በኦሮሚያ፣ በአማራና በአፋር ክልል ለሥራ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በፀጥታ ችግሮችና ሕግን በማያከብሩ ማንነታቸው በግልፅ በማይታወቅ አካላት ችግሮች እየገጠሟቸው በመሆኑ፣ መንግሥት ጥበቃ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ዋና ጸሐፊው ጠይቀዋል።

እንግዳ አክለውም፣ በቀጣይ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን የተለመደ የሠብዓዊ ድጋፍና የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ዕርዳታ የሚሰጥ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ስለ ማኅበሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሠጥ ነው የተናገሩት።


ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here