በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች አንድ ሊትር የምግብ ዘይት እስከ 170 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል።
የዋጋ ጭማሪው ከጥር ወር መግቢያ ጀምሮ የተከሠተ መሆኑን አዲስ ማለዳ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውራ ያነጋገረቻቸው የምግብ ዘይት ሻጮች ተናግረዋል። ከውጭ ገበያ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ከሱፍ የሚመረተው አንድ ሊትር የምግብ ዘይት በተለያዩ መሸጫ ቦታዎች የተለያዬ ዋጋ ያለው ሲሆን፣ በመገናኛ አካባቢ ከ150 እስከ 160 ብር ሲሸጥ፣ በአየር ጤና አካባቢ ደግሞ ከ150 እስከ 170 ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
በሜክሲኮና አካባቢውም ከውጭ የገባ አንድ ሊትር የምግብ ዘይት “ፎር ኦል” የሚባለው ከ150 እስከ 165 ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ ባለአምስት ሊትሩ ድግሞ በ690 ብር በመሸጥ ላይ ነው። በዚሁ አካባቢም ከሱፍ ፍሬ የሚዘጋጀው የምግብ ዘይት ባለአምስት ሊትሩ 715 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
እንዲሁም፣ ከውጭ የሚገቡ ኹሉም የምግብ ዘይት ዓይነቶች በብዙ ቦታዎች ዝቅተኛ መሸጫ ዋጋቸው 150 ብር ሲሆን፣170 ብር የሚሸጠው አንድ ሊትር የምግብ ዘይት ከጥር ወር በፊት ቀድሞ ይሸጥ ከነበረበት 140 ብር ከፍተኛ ዋጋ፣ የሰላሳ ብር ጭማሪ አሳይቷል። የዚሁ ዘይት ባለ አምስት ሊትርም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ከ630 ብር እስከ 715 ብር ሲሸጥ፣ ባለሦስት ሊትሩም ከ420 እስከ 430 ብር በመሸጥ ላይ ነው።
የአገር ውስጥ ባለ አንድ ሊትር ዘይት እንዲሁ በ130 ብር የሚሸጥ ቢሆንም፣ ለሸማቹ ያለው የአቅርቦት መጠን ግን ዝቅተኛ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መስከረም ባህሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በዘይት ዋጋ ላይ ተደረገ ስለሚባለው የዋጋ ጭማሪ መረጃው አለን፣ ሆኖም ግን ወርደን የምናረጋግጥ ይሆናል በማለት፣ ከዚያ ቀጥሎ የሚወሰደው ዕርምጃ በቀጣይ ይገለጻል ብለዋል።
ቀደም ብሎም የተወሠነ ጭማሪ እንደነበር ዳይሬክተሯ ጠቁመው፣ የሠሞኑ የተጋነነ ጭማሪ የመጣው በአጭር ቀናት ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል። ውጭ ገበያው ላይ የምግብ ዘይት ዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ያነሱት መስከረም፣ ዕጥረቱን ለማስተካከልና ዋጋውን ለማረጋጋትም የአገር ውስጥ አምራቾች ከስረውም ቢሆን በተመሳሳይ ዋጋ እንዲያስረክቡ ውሳኔ ተላልፏል ነው ያሉት።
ከቀረጥ ነጻ በሚገቡት ላይም አሠራር እያስቀመጥን ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በአስመጭዎች የሚቀርበው ዘይት መጠን በገበያ ላይ ትልቁን ድርሻ ስለሚወስድ በቅርቡ ከአስመጭዎች ጋር የጋራ መድረክ ይኖረናል ሲሉ አክለዋል።
የምግብ ዘይት የሚያመርቱ የአገር ውስጥ አምራቾችም ከነጻ ገበያ ሥርዓት ውጭ ስለሆኑ፣ ምርታቸውንም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በኮታ የሚወስዱት በመሆኑ ከዚያ መስመር ውጭ ምርታቸው ገበያ ላይ ላይገኝ ይችላል ሲሉ ጠቁመዋል።
በዚህም፣ የበላይነህ ክንዴ የዘይት ማምረቻ 16.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት፣ እንዲሁም ኹለት የዘይት ማምረቻ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ባለበት ዋጋ እንዲሸጡ ተወስኗል ብለዋል።
ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንም 12.5 ሚሊዮን ሊትር ያለቀለት የምግብ ዘይት፣ አንድ ሊትር በአማካይ በ77 ብር ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከውጭ ገበያ በማስገባት ሒደት ላይ መሆኑን አውስተዋል።
የዋጋ ንረቱ የተፈጠረው በምንዛሬ ዕጥረት ከውጭ የሚገባው ዘይት ቀንሶ ይሆን ለሚለው ጥያቄም ዳይሬክተሯ ምላሽ ሲሰጡ፣ ድፍድፍ ለሚያስገቡ ለአገር ውስጥ አምራቾችና ያለቀለት የምግብ ዘይት ለሚያስገቡ ለንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በበጀት ዓመቱ የተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሬ እየተሠጣቸው እንደሆነና ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2014 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት፣ ከባለፈው ሐምሌ 1/2013 ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ 30 ድረስ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ፣ 90 ሺሕ 741 ቶን የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ መመረቱን ገልጿል። እንዲሁም 679 ሺሕ 416 ቶን የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ገበያ እንደገባም ነው ኢንስቲትዩቱ ያመላከተው።
ብዙ ሸማቾች የምግብ ዘይት ዕጥረት መኖሩን በመግለጽ፣ የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት እንደሔደ እና ይህም በማኅበረሠቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ሲገልጹ ይሠማል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014



