በአማራ ክልል ዋግኽምራ ዞን የተፈናቀሉ 30 ሺሕ ሰዎች የመጠለያ ችግር ገጥሟቸዋል

0
610

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ጦርነቱ አለመቋጨቱን ተከትሎ በሕወሓት ጥቃት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ከ30 ሺሕ በላይ ሰዎች የመጠለያ ዕጥረት እንደገጠማቸው ተገለጸ።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ በመፈናቀል ላይ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ሠምታለች። በቂ የምግብ ዕርዳታ ካለመኖሩ በተጨማሪ፣ የመጠለያ ዕጥረት እንደገጠማቸው የዋግኽምራ ዞን የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መልካሙ ደስታ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት ከሆነ፣ ከየወረዳው ሠላም ወዳለበት አካባቢ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሺሕ በላይ ሆኗል። በአካባቢው ሠላም ሠፍኖ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ለማስተናገድ ፈታኝ የሆነው ነገር የመጠለያ ዕጥረት ነው የሚሉት መልካሙ፣ ተፈናቃዮቹ አሁን ያሉበት ቦታ መጠለያ ነው ለማለት ይከብዳል ሲሉ ነው ያስረዱት።

ለተፈናቃዮቹ ወደ ዘጠኝ መቶ ድንኳን እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ኃላፊው፣ አሁን ላይ እጃቸው ላይ ያለው ለመጠለያነት የሚያገለግል የድንኳን ብዛት ግን ከ10 የዘለለ እንዳልሆነ ነው ያስረዱት።
አሁን ላይ ከ30 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮቹ በፅፅቃ እና ሰቆጣ አካባቢ በመጠለያና በዘመድ ቤት ተጠግተው የሚገኙ ሲሆን፣ ነዋሪዎች መፈናቀል ከጀመሩም ከስድስት ወር በላይ እንደሆናቸውም ኃላፊው ተናግረዋል።

ሰቆጣ ውስጥ የሚገኙት በአባዎራ ደረጃ ስድስት ሺሕ፣ እንዲሁም ከነቤተሶቻቻው 23 ሺሕ የሚሆኑት ተፈናቃዮች በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ማለትም፣ አበርገሌ፤ ፃግብጅ፣ ሰቆጣ ዙሪያ፣ ዛታ፣ ኮረም፣ ወፍላ፣ እንዲሁም በከፊል ከአላማጣ አካባቢ የተፈናቀሉ መሆናቸውን መልካሙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ አንድ ሺሕ 624 አባዎራዎችና በአጠቃላይ ዘጠኝ ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች ከዝቋላ ወረዳ ከስድስት ቀበሌዎች ብቻ እንደተፈናቀሉ አብራርተዋል።

አሁንም ድረስ መፈናቀሉ ስላልቆመ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል የሚሉት መልካሙ፣ ባለፈው የካቲት 8/2014 እንኳ በአንድ ቀን ውስጥ ከተለያዩ ወረዳዎች ኹለት ሺሕ 500 ተፈናቃዮች ገብተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በኩል ብርድ ልብስ፣ ብረት ድስት፣ የውኃ ኩባያ፣ ጆግ፣ ፍራሽ፣ የመሳሰሉት ድጋፍ ቢደረጉም የተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ለማከፋፈል በቂ አለመሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
አያይዘውም ስንዴ፣ ፋፋና ማካሮኒ ተከፋፍሏል ያሉ ሲሆን፣ 30 ሺሕና ከዚያ በላይ ከሚሆኑት ተፈናቃዮች ውስጥ የስንዴ ድጋፍ ያደረጉት ለስምንት ሺሕ 509 ሰዎች ብቻ መሆኑንም አልደበቁም።

መልካሙ አክለውም አረጋውያን፣ ነፍሰጡር፣ የሚያጠቡ፣ እንዲሁም የስኳር፣ የኤች አይ ቪ፣ የደም ግፊት መድኃኒት የሚጠቀሙ ሕሙማን ከተፈናቃዮች መካከል ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፣ ከመደበኛው ድጋፍና ክትትል በተለየ ልዩ ትኩረት ቢያስፈልጋቸውም የድጋፍ ዕጥረት እንደገጠማቸው ነው ያብራሩት።
የፃግብጅ ወረዳ አስተዳዳር ነጋሽ በበኩላቸው፣ በዚሁ ወረዳ በሚገኙት 02 እና 03 ቀበሌዎች የሕወሓት ታጣቂዎች መዝረፋቸውንና ጥቃት መፈጸማቸውን ስላላቆሙ፣ ከዚህ በፊት አራት ሺሕ ብቻ የነበረው የተፈናቃይ ቁጥር ሠሞኑን ወደ 11 ሺሕ 176 ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።

ታኅሣሥ 15/2014 የሕወሓት ቡድን ወደ ፃግብጅ የሚወስደውን ድልድይ በቦንብ እንደሠበረው የመሠከሩት ሔኖክ፣ ይህን ተከትሎ አካባቢው ሠላም ባለመሆኑ የተፈናቃዮች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል ነው ያሉት።
በታኅሣሥ 18/2014 ከፃግብጅ ወረዳ መቶ ተፈናቃዮች ብቻ እንደነበሩና ከሠሞኑ ደግሞ ወደ 11 ሺሕ 176 እንደደረሱ ተናግረዋል።

በርካታ ተፈናቃዮች በወረዳው ቢኖሩም፣ የተዘጋጀው መጠለያ ሦስት እንደሆነና ከ180 ሰዎች በላይ ማስጠለል እንደማይችል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አክለውም፣ ቀሪዎቹ ተፈናቃዮች በዘመድ ቤት የተጠለሉ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ ቁጥራቸው ብዙ ስለሆነና ቦታ ባለመኖሩ በረንዳ ሥር ታጭቀው ነው የሚኖሩት ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከአረጋውያንና ዓቅመ-ደካሞች በተጨማሪ፣ በመንገድ ላይ ለመውለድ የተገደዱና ከወሊድ በኋላ እንክብካቤ ያላገኙ እናቶች አሉ ሲሉ የጠቆሙት የወረዳ አስተዳደሩ፣ ከክልሉ መንግሥትና ከዞኑ ጋር በመነጋገር መጠለያ ለመጨመር በሒደት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here