ዕረቡ የካቲት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የማህበር ቤት ፈላጊዎች ምዝገባቸውን ዳግም በአካል እንዲያረጋግጡ ጠይቋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ፍላጎት ያላቸውን ነባር የ20/80 እና የ40/60 የማህበር ቤት ፈላጊዎችን በህብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ በኦንላይን ምዝገባ ማካሄዱን አስታውሷል።
ቢሮው ካሉት አማራጭ የቤት አቅርቦት ውስጥ አንዱ የሆነውን የማህበር ቤት ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻልበትን የዲዛይን ዝግጅት ፣ የመሬት ዝግጅት እና የአበዳሪ ባንኮችን የመለየት ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ማህበራቱ ተደራጅተው ወደ ተግባር የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን ገልጿል፡፡
በመሆኑም ከዚህ በፊት በኦንላይን የተመዘገቡ የማህበር ቤቱ ፈላጊዎች ሁሉ ከየካቲት 16 እስከ መጋቢት 16 / 2014 ድረስ በኦንላይን የተደረገውን ምዝገባ በአካል እንዲያረጋግጡ ቢሮው ጠይቋል፡፡
ለዚህም “በአዲስ አበባ ከተማ ክልል በራሳችሁም ሆነ በትዳር አጋራችሁ ሥም ቤት ወይም ቤት መስሪያ ቦታ የሌላችሁ ወይም ኖሯችሁ ከ1997 ወዲህ በስጦታ ወይም በሽያጭ ያላስተላለፋችሁ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ” የሚገልፅ ቅፅ ከምትኖሩበት ወረዳ ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት በመውሰድ ምዝገባውን በተጠቀሰው ጊዜ ብቻ መፈፀም እንደሚችሉ ገልጿል።
ቢሮው ሁሉም ተመዝጋቢዎች ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲስተናገድና፤ ጊዜውን አሳልፈው ለሚመጡ ኃላፊነት እንደማይወስድ ያሳሰበ ሲሆን፤ ተመዝጋቢዎች የበለጠ መረጃን ከሚኖሩበት ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት ማግኘት የሚችሉ መሆኑንም አስታውቋል።




