ሠሞኑን ቅበላ ነው፤ በክርስትና ዕምነት ታላቅ የሚባለው የሁዳዴ ጾም መያዣ ነው። ታድያ ጾሙ ከመግባቱ በፊት የጾም መያዣ ምግቦች ሁሉ እረፍት አያገኙም። ሥጋ ቤቶችም ‹ጾም ከገባ በኋላ ብዙ እንቅስቃሴ ስለማይኖር ቶሎ ቶሎ እንሥራ› ብለው የኃምሳ አምስት ቀናት ሒሳባቸውን ከወዲሁ በቅበላ ለማካካስ በመስተንግዶ ሽር ጉድ የሚሉበት ሰሞን ነው።
ከዚህ ጋር ባልተያያዘ ሠሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ሠዉ በብዛት በሥጋ ቤቶች እየተገኘ መሆኑን ጠቀስ አድርገው ‹ኑሮ ተወደደ እያላችሁ ሥጋ ቤት ምን ትሠራላችሁ?› ዓይነት ነጥብ አንስተው ነበር። የሠዎች አመጋገብ ሥርዓትና የሚመገቡት የምግብ ዓይነት አንድ አገር ያለችበትን የምጣኔ ሀብት ደረጃ ለመበየን በቂ ነው? ብሎ መጠየቅ ያሻል። ይህንንም ነው ማኅበራዊ ሚድያው ከሠሞኑ ሲቀባበልና ሲያስተጋባ የነበረው።
ይህ ነገር ከዚህ ቀደምም በተለያየ ጊዜ የሚነሳ ጉዳይ እንደሆነ አንዳንዶች መለስ ብለው ሲያስታውሱ ነበር። ብራችን ዋጋ በነበረው በቀደመው ስርዓት፣ ‹ቢራ እየጠጣችሁ እንዴት ኑሮ ከበደን ትላላችሁ?› ተብሎ ሕዝቡ ተወቅሶ ያውቃል አሉ። ‹እንግዲህ መንግሥት ሆዳችንን እየገመተ ከሆነ የአገሩን ምጣኔ ሀብት የሚመዝነው፣ ደበቅ ብለን እንብላ ይሆን!› ተብሎ ተቀልዷል።
ይህን ሀሜት የሰሙ ሥጋ ቤቶችም፣ ‹እንደውም የደንበኛ ዕጥረት አለብን!› ሳይሉ አልቀሩም። መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያለባት አገር ላይ የእኛ ደንበኞች ብቻ ተቆጥረው ‹ኑሮ ቢወደድማ አርፋችሁ ሽሮና ምስራችሁን ትበሉ ነበር› መባላቸው ቅር አሰኝቶናል። ቅዳሜና እሁድ ብቻ ሳይሆን ከሰኞ እስከአርብ ሙሉ ቢሆኑልን በወደድን ነበር።› ብለዋልም አሉ፤ ብሶትን በቀልድ አዋህደው ተናጋሪዎቹ።
በእርግጥ ሽሮና ምስር፣ ጤፍና ስንዴስ ዋጋቸው መች የሚቀመስ ሆነ? ኢኮኖሚው በ‹ብዙ› የቅዳሜና የእሁድ ሥጋ በላተኛ ግራ ከተጋባ፣ እንግዲያው የሽሮና በርበሬ፣ የጤፍና የምስርን ዋጋ ልብ ብሎት ከሆነ በምን ተዓምር እየተኖረ እንደሆነ አይጠይቅም ብላችሁ ነው? ሽንኩርት እንኳ ከአቅሙ ‹ስፔሻል› ምግብ ሲታዘዝ ነው የሚጨመረው እስኪባልለት ድረስ ውድ ሆኖ፣ የሥጋው ስለምን ይደንቃል?
‹በአገር ውስጥ ምርት እንኩራ፣ የአገራችንን ምርት እንጠቀም እየተባለ፤ እኛ ጥሬ ሥጋ የምንወድ ሰዎች ለምን እንታማለን? ስለምን ሆዳችን በምጣኔ ሀብት ፊት ተሰጥቶ ይገመታል?› ያሉም አሉ ተብሏል።
ያሰኛልም! ሥጋ ስሙ ክቡድ መሰለ እንጂ፣ ምስሩም ቡናውም፤ ሽሮውና በርበሬውም አሁን ላይ ባለሀብቶች ብቻ የሚበሉት ያህል ውድ ሆኗል። ጉሊት በመደብ በጣት የሚቆጠሩ ድንችና ቃሪያዎችን ደርድራ የምትሸጥ ሴትም በ‹ኢኮኖሚው› ዐይን ከተቆጠረች፤ ኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን ግራ የሚያጋባው ራሱ ኢኮኖሚውም ግራ ሳይገባው አይቀርም።
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014



