ከወለጋ ተፈናቅለው መተከል ዞን የተጠለሉ ሰዎች ለአንድ ወር ድጋፍ እንደተቋረጠባቸው ገለጹ

0
1072

ድጋፉ የተቋረጠው በጸጥታ ችግር ተሸከርካሪ ማለፍ ባለመቻሉ ነው

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ባምባሲ ወረዳ የሚገኙ ዜጎች በመንግስት በኩል የአንድ ወር ሰብአዊ ድጋፍ እንደተቋረጠባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ባምባሲ ወረዳ በኹለት የመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ በመንግስት በኩል የአንድ ወር 15 ኪሎ ስንዴና ግማሽ ሊትር ዘይት የሰብአዊ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጅ ለኹለት ወር የተሰጣቸውን ድጋፍ ከተጠቀሙ በኋላ ለአንድ ወር ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ጠቁመዋል፡፡

በባምባሲ ወረዳ በኹለት የመጠለያ ጣቢያዎች ከአምስት ሺሕ በላይ ዜጎች የሚገኙ ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣቢያው የህክምና ቁሳቁስና የመዲሀኒት እጥረት በመኖሩ ምክንያት ህፃናትና እናቶች ለበሽታ እየተጋለጡ መሆኑንና አገልግሎትም ማግኘት እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡

ተፈናቃይ ዜጎች አክለውም፣ ለክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ድምፃቸውን ቢያሰሙም፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ከመናገር በቀር ምንም ነገር ለአንድ ወር እንዳልተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡
የታህሳስና የጥር ማለትም ያለፉት ኹለት ወራት ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ስንዴና ግማሽ ሊትር ዘይት፣ ብረትድስት፣ ጀሪካን፣ አልባሳትና ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች በመንግስት በኩል ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተፈናቃይ ዜጎች አስታውሰዋል፡፡

ከምዕራብ ወለጋ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ በሚገኘው ኢንዚ መካነ ገነት መድሀኒያለም ቤተ ክርስቲያን ከ200 በላይ ህፃናት፣ አረጋውያን፣ ነብሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶችን ጨምሮ በራካታ አቅመ ደካሞች ተጠልለው የአካባቢው ህብረተሰብ በየወቅቱ ድጋፍ እያደረጉላቸው የነበረ ቢሆንም፣ የክልሉ መንግስት እራሱን የቻለ የመጠለያ ጣቢያ አዘጋጂቻለሁ ማለቱን ተከትሎ ተገደው መተከል ዞን ባምባሲ ወረዳ ወደሚገኘው የመጠለያ ጣቢያ ማቅናታቸው ይታወሳል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ከሚሽን ኮሚሽነር ታረቀኝ ተሲሳ በበኩላቸው፣ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች መኖራቸውን የገለፁ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ አከባቢ ያለው የፀጥታ ችግር ለዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እንዳናስገባ እንቅፋት ሁኖብናል ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ለምግብነት የሚውሉ እህሎችንና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብአዊ ድጋፎችን በተሽከርካሪ ጭነው ማለፍ ባለመቻላቸው ለተፈናቃይ ዜጎች የየካቲት ወር ሰብአዊ ድጋፍ እንዳልተደረገና ቅሬታ አቅራቢ ተፈናቃዮችም ያቀረቡት ጥያቄ እውነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለውም፣ የተፈናቃዮችን ቅሬታ ለመፍታትና ተገቢውን ወርሀዊ ድጋፊ ለማድረግ የክልሉ መንግስት፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት፣ ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን እንቅፋቱን ለመፍታት እየሰሩ እንደሚገኙና ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሰብአዊ ድጋፉ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያ በርካታ ዜጎች እንዳሉና የፀጥታ ችግር ካለባቸው ከኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ከሌሎች አከባቢዎች በየጊዜው ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የሚመጡ ሰዎች መጨመራቸውን ተከትሎ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ዲያስፖራዎች፣ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here