የቤት ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች በወቅቱ ባለመረከባችን የ500 ሺሕ ብር ጉዳት ደርሶብናል አሉ

0
822

በአዲስ አበባ ለሚኩራ ክፍለ ከተማወረዳ አራት ቦሌ በሻሌ በሚባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንደር፣ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣላቸው ሠዎች፣ ቤቶቹን በወቅቱ ባለመረከባቸው ከ500 ሺሕ ብር በላይ ጉዳት እንደደረሠባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡

ዕጣ የወጣልን የካቲት 27/2011 ሲሆን፣ በመጭው የካቲት 27/2014 ሦስት ዓመት ይሞላናል የሚሉት ሥሜ አይጠቀስ ያሉ ግለሰብ፣ ቤቱን በወቅቱ ባለመረከባችን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድ ሰውበወር አምስት ሺሕ ብር የቤት ከራይ እንኳ ከፍሏል ተብሎ ቢታሠብ፣ ከ180 ሺሕ ብር ያላነሰ ወጭ ለቤት ኪራይ አውጥተናል ነው ያሉት፡፡

ከቁጠባ ሒሳባችን ገንዘብ ተቀንሶ ወደ ቤቶች ልማት ገቢ በመሆኑም በባንክ ወለድ እናገኘው የነበረውን ገንዘብ አጥተናል ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፣ከባንክ ጋር የብድር ውል በመግባታችንም ለተበደርነው ገንዘብ በ12.5 በመቶ ወለድ ምጣኔ የ29 ወራት ብዙዕዳ አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የነበረው ለቤት ዕድሳትየሚያገለግል የግንባታ ዕቃ ዋጋ አሁን ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ፣በአጠቃላይ ቢያንስ ከ240 ሺሕ ብር በላይ አጥተናል ይላሉ፡፡ በዚህም፣ በአጠቃላይ በግንባታ መዘግየትና በወቅቱ ባለመረከባችን በትንሹ ከ500 ሺሕ ብር በላይ ከሥረናል በማለት ቅሬታ አቅራቢው አስረድተዋል፡፡

የደረሰብን ኪሳራ ሲጨመር የቤቱ ዋጋ መንግሥት ደጉሞ የሰጠን ሳይሆን፣ የሪል ስቴት ዋጋ ነው የሆነብን ሲሉም አክለዋል፡፡ሌላኛው የቤት ዕጣ የወጣላቸውናሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ ግለሰብ፣ የቤት ዕጣ ወጥቶላችኋል የተባልነው ከሦስት ዓመት በፊት ቢሆንም እስካሁን ባለመረከባችን ከፍተኛ ምሬት ውስጥ እንገኛለን ብለዋል፡፡

በዚህም፣ የባንክ ዕዳ እንድንከፍል በመገደዳችን በየወሩ አራት ሺሕ ብር ለባንክ ብድር ከነወለዱ፣ ስድስት ሺሕ 500 ብር ለቤት ኪራይ፣ እንዲሁም በየወሩ ከኹለት እስከ ሦስት ሺሕ ብር ከመሥሪያ ቤት ለተበደርኩት ብር እከፍላለሁ፡፡ይህ ደግሞ ከኑሮ ውድነቱ ጋር በጣም ነው የሚያማርረው፤ኹሉም ሰው ችግር ውስጥ ነው ያለው፤ለማን አቤት እንደምንል ግራ ገብቶናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ሔደን ስንጠይቅም የፋይናንስ ዕጥረት ስላለ ነው ይሉናል፡፡ ኮንትራክተሮችም እንዲሁ 100 ሚሊዮን ብር ለሠሩበት ያልተከፈላቸው መኖሩን ይነግሩናል በማለት ነው የገለጹት፡፡

ሌላ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብም እንዲሁ ቤቱን በወቅቱ ባለመረከባቸው ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸው፣ በኹነቱም መኪናቸውን ሽጠው የባንክ ዕዳቸውን የከፈሉና መንቀሳቀሻ ያጡ ሰዎችን አውቃለሁ ሲሉ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም የቦሌ በሻሌ የጋራ መኖሪያ ቤቶችማኅበር አቋቁመው ኮሚቴ በማዋቀር እየጠየቁ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ ቅንነቱ ካለም የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን በቶሎ መፍታት ይችላሉ ነው ያሉት፡፡

በ31 የጋራ መኖሪያ ቤት ሕንጻዎች ከ2300 በላይ ሠዎች ዕጣ የወጣላቸው ቢሆንም፣ ቤቶቹን ባለመረከባቸው አብዛኞቹ ከመማረራቸው የተነሳ የት ሔደን እንጩህ እስከማለትና ሰልፍም ለማድረግ እስከማሰብ እንደደረሱ ቅሬታቸውን በገለጹበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ለማግኘት ያደረገቸው ሙከራ አልተሳካም፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here