ዓባይ ለገጠሩ ብርሃን ያመጣ ይሆን?

0
856

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታው የተጀመረው መጋቢት 24/2003 ሲሆን፣ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በመንግሥትም ሆነ በግል ሥራ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ከገቢያቸው ቀንሰው ቦንድ በመግዛት ለተከታታይ ለ11 ዓመት የበኩላቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡
ግድቡን ለመገንባት ከታሰበበት ወቅት ጀምር አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ብዙ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ያለው ዓባይ፣ በየካቲት ወር 2014 ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ዋጋ የከፈሉ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ በደስታ እያስፈነደቀ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭበትን ቀን ተስፋ ሠንቀው ለዓመታት ሲጠብቁት የነበረው ዓባይ 13 ተርባይኖች ያሉት ሲሆን፣ ኃይል ማመንጨት የጀመረው በአንድ ተርባይን እንደሆነና በዚህም 375 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለው ተመላክቷል፡፡
በአንድ ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረው ዓባይ ግንባታው ሲጠናቀቅ በ13ቱ ተርባይኖች አምስት ሺሕ 150 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይቻለዋል፡፡
240 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል የተባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እስካሁን ከ10 ሺሕ በላይ ኢትዮያዊያን ሠራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡

በአራቱም አቅጣጫዎች የሚፈሱት የበለስ፣ ጫሞጋ፣ ደቡሳ፣ ዴዴሳ፣ ፊንጫ፣ ጉደር፣ ሙገር፣ በሻሎ፣ ወኝጭትና ሌሎች ገባሮች ማረፊያ በመሆኑ በብዛት የውኃ ክምችቱ የሚታወቀውና በ80 ቢሊዮን ብር ይገነባል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የዓባይ ግድብ፤ አሁን ካለበት ደረጃ እስከሚደርስ 163 ቢሊዮን ብር ወጪ ስለመጨረሱ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሠጠው መግለጫ ያመላክታል፡፡

ላለፈው 11 ዓመት ስለዓባይ ግድብ ያልተወሳባቸው ወቅቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከግብጽና ከሱዳን ጋር ብዙ ውዝግቦች ተስተውለዋል፡፡ የግድቡን የውኃ ሙሌት አስመልክቶ ግብጽና ሱዳን የተለያዩ ውዝግቦችን ማንሳታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውዝግቡን በውይይት ለመፍታት ባደረገችው ድርድር በ2012 እና በ2013 የክረምት ወራት የውኃ ሙሌቱ መሳካት ችሏል።

ግብጽና ሱዳን ግድብ እንዳይገነባ ቅናት በሚመስል መልክ ያላቀዱት የማሰነካከያ አጀንዳ አልነበረም፡፡ ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያዊያን ከግብጽና ከሱዳን ጋር በተደጋጋሚ ድርድር ሲያደርጉ ቆተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን የግድቡ ኃይል ማመንጨት የግብጽና ሱዳንን ዐይን ማቅላቱ እየተነገረ ነው፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት የግድቡ ተደራዳሪዎች ግብጽና ሱዳንን በመጡበት አውድ ለመመለስ የተለመደው ድርድር መቀጠል እንዳለበት አቋማቸውን እየገለጹ ነው፡፡
መንግሥትን ጨምሮ ከታች እስከ ላይ ድረስ ያለው የማኅበረሠብ ክፍል ቦንድ በመግዛት፣ የዘርፉ ምሁራን ሙያዊ አስተያየታቸውን በመስጠት ለግድቡ የበኩላቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡

የሕዳሴ ግድቡ ኃይል ማመንጨቱን ተከትሎ መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይልን ለውጭ አገር ለመሸጥ እንዳሰበ መግለጫ ሠጥቷል፡፡ ይህን በተመለከተም በርካቶች ለምን የሚል ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ፡፡ ቅሬታቸው ኃይል ተሽጦ ለምን ገቢ ይገኛል ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ በተለይም የገጠሩ ማኅበረሠብ ችግር ተፈትቶ ኃይል ቢተርፍ እንኳ የተለያዩ ፋብሪካዎችን በማስፋፋት የሥራ ዕድል መፍጠር እንጅ መሸጡ እምብዛም አዋጭ አይደለም በሚል ሐሳብ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ ምሁራን ልጆች ቢኖሯትም እንደ አለመታደል ሆኖ አገራቸውን በማገልገል ፈንታ ወደ ውጭ ስለሚሄዱ በተግባር የሚገለጸው የዕውቀታቸው ውጤት ለውጭ አገር ሲሳይ እንደሆነ ሁሌም የሚወሳ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ የሚሆንበት ምክንያትም የተሻለ ዕውቀት አላቸው የሚባሉ ኢትዮጵያዊያን በአገር ውስጥ ሠርተው ከሚያገኙት ገቢ ይልቅ፣ በውጭ አገር ሠርተው የሚያገኙት የበለጠ ስለሚሆንና በአገር ውስጥ አዲስ ነገር ለመፍጠር የኢኮኖሚ አቅሙም ስለማይኖር መሆኑን በተለያዩ ጊዚያት ሲተነተን የቆየ ጉዳይ ነው፡፡

በቴክኖሎጅ ዕድገት ጫፍ ደረሱ የሚባሉት የዓለም አገራት ዋነኛ መሠረታቸው ኤሌክትሪክ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ የበለጸገች ሆና ሳለ ይህን ሀብቷን በትክክል ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ሕዝቦቿ ተመጽዋች ከሆኑ ሰንበትበት ብለዋል፡፡
የሆነው ሆነና ብዙዎች የሚሠነዝሩት አስተያየት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ችግር ሙሉ ለሙሉ ቀርፎ የሚተርፍ የኤሌክትሪክ ኃል ቢኖር እንኳ ወደ ውጭ ከመሸጥ ይልቅ፣ ከአደጉ አገሮች የተለያዩ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በሥራ አጥነት የተማረረውን ወጣት የሥራ ዕድል እንዲፈጥረበት ማድረግ የተሻለ መሆኑን ነው፡፡

ኃይል መሸጥ ለምን?
መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ እንደሚሸጥ መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም በርካቶች የኢትዮጵያዊያን የመብራት ችግር ቢቀረፍ እንኳ ከመሸጥ ይልቅ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ጥቅም ማዋሉ የተሻለ እንደሚሆን አስተያታቸውን ሲሰጡ ተሠምተዋል፡፡
ዐቢይ አሕመድ (ጠ/ሚ) የሕዳሴ ግድቡ ኃይል ማመንጨቱን ለማብሰር በጉባ ላይ በተሳተፉበት መርሃ ግብር “ምዕራባውያን ከተለመደው የውኃ ፖለቲካ ተላቀው በአዲስ የትብብር መንፈስ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሠሩ” ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዓባይ ኃይል አመነጨ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ በርካቶች የሚያንሸራሽሩት የተስፋ ንግግር በጨለማ ውስጥ ያለው የማኅበረሠብ ክፍል ብርሃንን ከመለገስ በዘለለ የተለያዩ ፋብሪካዎችንም ለማስጀመር እንደሚያስችል ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግል አማካሪው ፈካነት ነጋሽ በበኩላቸው፣ በመጀመሪያ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ችግር ሳይቀረፍ ሽያጭ የሚታሰብ አይመስለኝም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኃይል መሸጡ አዋጭ የሚሆነው በአንድ ወቅት ብዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ቢቻልና ያን የምንጠቀምበት ጊዜ ባይኖር ከሚባክን ሸጦ ገቢ ማግኘቱ የተሻለ ከመሆኑ አንጻር እንጅ፣ ኃይል ይሸጣል ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ችግር ሳይፈታና የሥራ ዕድል ሳይፈጠር ኃይል መሸጡ እንደሌለበት ፈካነት አብራርተዋል፡፡

ማንኛውም የኃይል ማመንጫ በቅድሚያ ለፍጆታ መዋል ያለበት በአገር ውስጥ ነው የሚሉት ፈካነት፣ ይህ ሳይደረግ ወደ ውጭ መሸጥ ግን አግባብ እንደማይሆን ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፡፡

አያይዘውም፣ በቅድሚያ ለዘመናት በጨለማ ውስጥ ያለውን የማኅበረሠብ ክፍል ብርሃን እንዲያገንኝ ማድረግ ተገቢ መሆኑንና ከዚህም በዘለለለ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ችግር መቅረፍ የኤሌክትሪክ ኃይሉ ወደ ውጭ ተሽጦ ከሚገኘው ገቢ የበለጠ ጠቃሚ እንደሚሆን ነው ያብራሩት፡፡

ፈካነት አክለውም፣ አገር ውስጥ ያለው ችግር ሳይቀረፍ ኃይል ወደ ውጭ መሸጥ አዋጭ አይመስለኝም ያሉ ሲሆን፣ አዋጭ አይሆንም ላሉበት ምክንያት የሰጡት ማብራሪያ ደግሞ ወደ ውጭ ተሸጦ ከሚገኘው ዶላር ይልቅ በአገር ውስጥ የሚቀረፈው ችግር ሚዛን የደፋ እንደሚሆን ነው፡፡

የግል አማካሪው እነደሚሉት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሸጦ ዶላር ከማምጣት ከሚገኘው ትርፍ ይልቅ በአገር ውስጥ ያለውን ችግር መቅረፉ የዜጎች ችግር ከማቃለልም በዘለለ ሌላ የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ አኳያ ጥቅሙ የጎላ መሆኑን ነው፡፡

ስለ ዓባይ በተለያዩ ወቅቶች በመደራደር የሚታወቁት ያዕቆብ አስፋው (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ በተጀመረው መሠረት መብራ እያመነጩ የገጠሩም የከተማውንም አካባቢ ከሸፈኑ በኋላ፤ በሌላ ጎን ደግሞ የተረፈውን በመጠኑ ወደ ጎረቤት አገሮችና ደንበኞች በመሸጥ ገንዘብ የማግኘት ጉዳይ እንጅ፣ አገሩን ትቶ ኃይል ወደ ውጭ የመሸጥ ተግባር ሊኖር እንደማይችል ነው የግል አስተያታቸውን የሠጡት፡፡

ዓባይ ለገጠሩ ነዋሪ
በኢትዮጵያ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው የማኅበረሠብ ክፍል በጨለማ ውስጥ እንደሚኖር ይነገራል፡፡ በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩ የማኅበረሠብ ክፍሎችን መለስ ብለን ብንመለከት ለመብራት አገልግሎት የሚጠቀሙት ኩራዝ፣ እንጨት ከዚያ አለፍ ካለም ምናልባት የእጅ ባትሪ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፣ ውኃ የሚያገኙት ወደ ወንዝ በመውረድ ወንዶች በትካሻቸው ሴቶች በጀርባቸው ተሸክመው ብዙ ርቀትን በመጓዝ መሆኑ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡
ታዲያ ዓባይ ኃይል ሲያመነጭ ችግራቸው እንደሚቀረፍ ለዘመናት በተስፋ ከመጠበቃቸውም በላይ፣ ከገቢያቸው ቀንሰው ቦንድ በመግዛት የበኩላቸውን ለተወጡት ዜጎች ተስፋቸው እውን ይሆን የሚለው ጉዳይ የብዙኃኑ ጥያቄ ነው፡፡

ኃይል ማመንጨት የጀመረው ዓባይ በተለይም ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በገጠሩ አካባቢ ለሚኖሩ የማኅበረሠብ ክፍሎች የመብራት አገልግሎት ያስገኛል የሚል ተስፋ ተስንቆበት ኖሯል፡፡
እንደ ዱባይ፣ ሳዑዲ አረቢያ ባሉ አገራት የሚኖር እያንዳንዱ ማኅበረሠብ የመብራት አቅርቦት የተሟላለት ሲሆን፣ ከዚህም አልፎ ጫካው ሁሉ በኤሌክትሪክ መብራት የፈካ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በውኃ ሃብቷ የምትታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳ አብዛኛው የማኅበረሠብ ክፍል የመብራት አገልግሎት እንደማያገኝ የዘርፉ ምሁራን የተናገሩ ሲሆን፣ አሁን ግን ዓባይ የገጠሩን ጨለማ ያበራል እያሉ ነው፡፡
ያዕቆብ አስፋው (ፕ/ር) በበኩላቸው የዓባይ ኃይል ማመንጨት በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ዜጎችን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ባለው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆነው የማኅበረሠብ ክፍል የመብራት አገልግሎት እንደማያገኝ ሲነገር ኑሯል የሚሉት ያዕቆብ፣ አሁን ደግሞ ዓባይ ላይ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከቀድሞው በመጨመር ለገጠሩና ለከተማው በተሻለ ሁኔታ መብራት እንደሚዳረስ በመንግሥት በኩልም ተወስቷል ነው ያሉት፡፡

ፈካነት በበኩላቸው፣ የገጠሩ ማኅበረሠብ ሆስፒታል፣ ወፍጮ፣ ውኃ እና ሌሎች ነገሮችም ያሥፈልጉታል ያሉ ሲሆን፣ በግንባር ቀደም እነዚህን ችግሮች መፍታት ለአገር ዕድገትም ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
በጨለማ ውስጥ ያለው የሕብረተሠብ ክፍል ከዓባይ ኃይል ማግኘት የሚችልበት ኹለት ዓይነት አማራጮች አሉ የሚሉት ፈካነት፣ የመጀመሪያው ጋዝን የሚተካ የኃይል አገልሎት ማግኘት ነው ብለዋል፡፡

ይህም ማኅበረሠብ ከከተማ ርቆ ስለሚገኝ በአቅርቦት ዕጥረት ከተማረረበት፣ ከፍተኛ ወጭ ከሚጠይቀው፣ እንዲሁም ከቤት ውስጥ ሲበራ ጭሱ ለዐይን ጤንነት ጉዳት ከሚያስከትለው ከኩራዝ መብራት ወደ ኤሌክትሪክ ብርሃን ለመሸጋገር የሚያስችል መሆኑን ፈካነት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

በገጠሩ አካባቢ የሠፈረው ማኅበረሠብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲያገኝ የሚጠቀመው ለመብራት ብቻ ሳይሆን፣ እንጀራ ለመጋገር እንጨት ወይም ኩበት ሲጠቀሙ እንዲሁም ኩራዝን ሲያበሩ ጭሱ በአይናቸው ላይ የሚያስከትለውን ችግርም ስለሚያስወገድ ጤንነታዊ ፋይዳ እንዳለው ፈካነት አብራርተዋል፡፡

ፈካነት አያይዘውም፣ የጋዝና የኩበት ጭሱ የማኅበረሠቡን ጤንነት ከማወኩም በተጨማሪ፣ የአካባቢውን አየር ስለሚበክል የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ አየር ብክለትን ከመቀነስም ባሻገር፣ ለማገዶነት የሚወድሙ ዛፎችም ስለማይኖሩ በተዘዋዋሪ ደረጃ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ከፍ እንዲል ይረዳል ነው ያሉት፡፡

የዓባይ ኃይል ማመንጨት ለከተሜው ከሚሠጠው ጥቅም ይልቅ፣ ብዙ መፍትሔ በሚሹ ችግሮች ለዘመናት ለተሰቃየው ለገጠሩ ማኅበረሠብ የሚኖረው አገልግሎት ሚዛን የደፋ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ከእነዚህም ችግሮች መካከል ከጨለማ ሕይወት መውጣት መቻል አንዱ ሲሆን፣ የወፍጮ አገልግሎት ማግኘትም ሌላኛው ከችግር ሊያወጣ የሚያስችል ተግባር መሆኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ኤሌክትሪክ ይቅርና የነዳጅ ወፍጮ እንኳ በሌለበት ቦታ የሚኖሩ እናቶቻችን ዴቄት የሚያገኙት ወገብ ሠባሪና ለጤንነት ጠንቅ በሆነው የድንጋይ ወፍጮ እየፈጩ ነው የሚሉት ፈካነት፣ የዓባይ ኃይል ማመንጨት ማኅበረሠቡ የኤሌክትሪክ ወፍጮ እንዲያገኝ ይረዳዋል ነው ያሉት፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here