ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹ ቁጥር ከ60 ሚሊየን ማለፋን አስታወቀ

0
1101

ሰኞ የካቲት 21 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮ- ቴሌኮም የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ዛሬ የካቲት 21 2014 በሂልተን ሆቴል በገንዘብ ሚኒስቴርና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በተገመገመበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የድርጅታቸው አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 60 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አንዳሉት በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ድርጅቱ 28 ቢሊየን ብር ግቢ ማገኘቱን ተናገረው፤ 74 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከስምንት ወር በፊት ሥራ ላይ ባዋለው የቴሌ ብር አገልግሎት 13 ነጥብ 1 ሚሊየን ደንበኞችን በማፍራት 16 ነጥብ 6 ሚሊየን ክፍያዎች በመተግበሪያው አማካኝነት መደረጉንና በገንዘብ ረገድም የ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ልውውጦች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ወጪውን ለመቀነስ እንዲያስችለው ‹‹ዱቱሴቭ›› አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ ማስቀረት ችያለሁ ያለው ድርጅቱ፣ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለዕዳ ክፍያ ማዋሉን፣ እንዲሁም 12 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የታክስ ክፍያ መፈፀሙንም ገልጿል፡፡

ከግማሽ ዓመቱ ዕቅዴ 86 በመቶውን ነው ያሳካሁት ያለው ድርጅቱ የፀጥታ ችግር፣ የመስረተ ልማትና ንብረት ጉዳት፣ በክልሎች አግባብ ያልሆነ ካሳ ጥየቃና የባንክ ሂሳብ መዘጋት ለሥራዬ ዋና ዕንቅፋት ነበሩ ሲልም አስታውቋል፡፡

የግምገማ መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር አህመድ ሽዴ እንዳሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ባለፋት 6 ወራት ውስጥ አገልግሎቱን በማስፋፋት፣ የአግልግሎቱን ጥራት በማሻሻል፣ የገጠሙትን ፈተናዎች ለማለፍና በተለይ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ጠንክራ ሥራ ሰርቷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያው ይበልጥ ትርፋማ እንዳይሆን ምክንያት የነበሩ ደንቦችና አሰራሮችን መንግስት ለማሻሻል መስራቱን የተናገሩት አህመድ፤ ወደፊትም ለሚገጥሙት ችግሮች በጋራ መፍትሔ ለመስጠት ይሰራል ማለታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በወጪ ቅነሳ በኩል ኩባንያው ጥሩ መሻሻል አሳይቷል ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት አህመድ ሽዴ በቀጣይ ኩባንያው ራሱን ለውድድር በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እንዳለበትም አሳስበዋል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here