ማክሰኞ የካቲት 22 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ሌ/ጀነራል ጻድቃን ገ/ተንሳይን ጨምሮ 74 የህወሃት ወታደራዊ ቡድን አመራሮችና አባላት ላይ የተመሰረተውን ክስ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በንባብ አሰማ።
አጠቃላይ ክስ ከቀረበባቸው 74 ተከሳሾች ውስጥ ጀነራል ታደሰ ወረደ ሌ/ጀ ጻድቃን ገ/ተንሳይን ጨምሮ 54 ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ናቸው።
እነዚህ 54 ተከሳሾች በጋዜጣ ጥሪ ተደርጓላቸው አለመቅረባቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በሌሉበት መዝገቡ እንዲቀጥል ብይን መስጠቱ ይታወሳል።
ነገር ግን ቀሪዎቹ ኮነሬል መሐመድ ኑር፣ ኮነሬል ባህሩ ታጀበን ጨምሮ 20 ተከሳሾች ግን ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ናቸው።
ዓቃቢህግ የወንጀል ህግ አንቀጽ 321/2 አንቀጽ 33:35:38 እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁ 1176/2012 አንቀጽ 3/2 ድንጋጌን በመተላለፍ የመሰረተውን ክስ ፍርድ ቤቱ በንባብ አሰምቷል።
በዚህ በንባብ በተሰማው ክስ ላይ ተከሳሾቹ ከህወሃት የሽብር ቡድን ተልኮ በመቀበል ወታደራዊ ቡድን በማቋቋምና በመምራት በመከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ጥቃት ማድረስ ወንጀል እንደተሳትፎ ደረጃ መከሰሳቸውን ፍርድ ቤቱ አብራርቷል።
ክሱ ከተነበበ በኋላ የተከሳሾች ጠበቃ ዘራይ ወ/ሰንበት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያና ህገመንግስታዊ ትርጉም ጥያቄዎችን በጽሁፍ ለችሎቱ አቅርቧል።
ጠበቃ ዘራይ በጽሁፍ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ክሱን አይቶ ለመወሰን የሚያስችል በህግ የተሰጠ የስረ ነገርም ሆነ የሥፍራ የዳኝነት ስልጣን የሌለው ስለመሆኑ የተጠቀሰበት እና ሌሎች የመቃወሚያ ነጥቦች የተካተቱበት 26 ገጽ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያን ነው።
በተጨማሪም ጠበቃው የወንጀል ክሱ በህገመንግስት ትርጉም የሚያስፈልገው መሆንን በዝርዝር ተጠቅሶ 17 ገጽ የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄም አያይዞ በጽሁፍ ማቅረቡን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።
ፍርድ ቤቱም በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ የዓቃቢህግ ምላሽ ውጤት ለመጠባበቅ ለመጋቢት 23 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





