የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እየተጋጋለ ተሳታፊዎችንም እያበዛ በመጣበት በዚህ ሠሞን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያን እናውግዝ የሚል ጥሪ አቅርቦ፣ የዓለም አገራትን በተወካዮቻቸው አማካይነት በአስቸኳይ እንዲወስኑ አሜሪካና ግብረአበሮቿ ጫና አሳድረው ነበር። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያን ለማግለል የተጠራውን ጉባዔ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላት ሩሲያ እንዳታስቀረው በማድረግ ነበር እሷን ለመኮነን የተሠየመው። ውጤቱ ግን ጠሪዎቹ እንደጠበቁት ሳይሆን ቀርቷል።
ከተባበሩት መንግሥታት አባልነት ሩሲያን ከነጭራሹ ለማስወጣት ይሞከራል በሚል ተነዝቶ የነበረው ቅስቀሳ ላይ አገሪቱ ቁርጥ ያለ አቋሟን በማሳወቋ ጠላቶቿ ወደ ማግለሉ ነበር ያመሩት። ይህም ግን እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ካላሰቡት አገራት ተቃውሞና ድምፀ ተዓቅቦ ገጥሟቸዋል።
ሩሲያን የመኮነንና የማግለል ሒደቱን የተቃወሙት ጥቂት አገራት ሩሲያ፣ ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያና ኤርትራ ናቸው። የአብዛኞቹ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ የኤርትራ ማምረር ግን ብዙዎችን አስደንቋል። ከአፍሪካ ብቸኛ አገር ሆና መቃወሟ ድፍረቷን ያሳያል በሚል ብዙዎች ሲያሞካሹዋትም ተደምጧል። የኤርትራ መቃወም ያልገረማቸው አንዳንዶች ለዘመናት ከአሜሪካ ይደርስባት የነበረን ጫና የተበቀለችበት እንጂ፣ ያን ያህል የሩሲያን ዕርምጃ ደግፋ አይደለም በሚል አስተያየታቸውን ሠንዝረዋል።
በሌላ በኩል፣ ድምፀ ተዓቅቦ ያደረጉት በሙሉ ማለት ይቻላል ልባቸው ከሩሲያ ጋር የሆነ ነገር ግን ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸው በኹለት ቢላ መብላት የፈለጉ አገራትን ናቸው በማለት ቻይናን በምሳሌነት የሚጠቅሱ አሉ። ጭልጥ ብለው ምዕራባውያኑን ከደገፉት በርካቶች ይልቅ፣ በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ለዘመናት በመፈንቅለ መንግሥት ሲታመሱና ሲጨቆኑ የኖሩ የአፍሪካና የደቡብ አሜሪካ አገራት ትኩረትን ስበዋል። ከአጠቃላይ 193 አገራት 5 ተቃውሞ፣ 141 ድጋፍ፣ 35 ተዓቅቦ የተመዘገበ ሲሆን፣ 13 አገራት ከነጭራሹ ድምፅ አልሠጡም።
ኢትዮጵያና ጥቂት አገራት ጭራሽ አቋማቸውን ለማሳወቅ በውሳኔው አለመሳተፋቸው ብዙ ዜጎቻቸውን ያስደሰተ እንደነበር ለመታዘብ ይቻላል። ወገን መያዙን አጥብቀው የሚቃወሙ ሒደቱ የተመቻቸው ሲሆን፣ በዚሁ ገለልተኝነት አቋም መዘለቅ እንዳለበት መክረዋል።
ምዕራባውያን የሚባሉት በሙሉ ሩሲያን የኮነኑና ማግለሉን የደገፉ ሲሆን፣ ከእነሱ ይልቅ ሩሲያውያንን ያስቆጣውና እንዲዝቱ ያደረጋቸው የአንዳንድ አፍሪካውያን መሪዎች አቋም እንደሆነ ተወርቷል። ኹሉም ቀጥሎ የሚሆነውን ለማወቅ አሰፍስፎ በሚጠብቅበት በዚህ ወቅት ብዙዎችን የአገራቱ አሰላለፍ እያነጋገራቸው ይገኛል።
በሩሲያ ዕርምጃ አንዳንዶች የቃላት ፍጥጫ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ የአድዋ ድል ብለን ወራሪን የምንቃወም ሰዎች እንዴት ሩሲያን እንደግፋለን ሲሉ የሩሲያን ዕርምጃ እንደቅኝ ግዛት አድርገው ሲያቀርቡት ተደምጠዋል። ሌሎች ሲመልሱ፣ አጼ ኃይለሥላሴ በጉልበት የተወሰደውን የኤርትራን ግዛት ወደ ኢትዮጵያ ለመቀላቀል የሔዱበትን ጥግ የሚደግፍ ሰው፣ ሩሲያ የቀደመ ግዛቷ የጠላቶቿ መንደርደሪያ እንዳይሆን የወሠደችውን ዕርምጃ መቃወም የለበትም ሲሉ አስተያየታቸውን ሠጥተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014



