አዘዋዋሪዎቹ ወደ ትግራይ ከሚላከው ገንዘብ 50 በመቶውን ያስከፍላሉ
በትግራይ ክልል የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ የተፈጠረውን የጥሬ ብር ዕጥረት ተከትሎ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች አላማጣ ድረስ ጥሬ ብር ለመላክ የተደራጁ ግለሰቦች ከላኪዎች ወይም ከተቀባዮች ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈሉ ነው።
በክልሉ የተከሠተውን የጥሬ ብር ዕጥረት ተከትሎ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ የተደራጁ ግለሰቦች ገንዘቡን ከላኪው ወደ ተቀባዩ ለማድረስ ወይም ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ ሠዎች ትግራይ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለማድረስ መቀመጫቸውን አላማጣ አድርገው ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
መቀመጫቸውን አላማጣ ያደረጉት ጥሬ ገንዘብ አዘዋዋሪ ግለሰቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ አከማችተው፣ ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ የሚላክላቸው ሠዎች የማዘዋወሪያ እየከፈሉ እንዲወስዱ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ በርካታ ሠዎች ወደ አላማጣ እየተጓዙ ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እያስላኩ ነው። በክልሉ ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ ዕጥረት መከሠቱን አዲስ ማለዳ ከምንጮች የሠማች ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው በጥሬ ገንዘብ ወደ አዘዋዋሪ ግለሰቦቹ የሒሳብ ቁጥር ገንዘብ በማስላክ ከፍተኛ የአግልግሎት ክፍያ እየከፈሉ ከአዘዋዋሪዎች እየተቀበሉ ነው።
ትግራይ ክልል ውስጥ የባንክ አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ፣ ከክልሉ ውጭ የሚገኙ ነዋሪዎች ለቤተሰቦቻቸው ከሚልኩት ገንዘብ ከ40 እስከ 50 በመቶ ያክሉን ገንዘብ ለሚያዘዋወሩ አካላት እየከፈሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። አዘዋዋሪዎቹ የሚያስከፍሉት ገንዘብ ቀን በቀን እየጨመረ መምጣቱን አዲስ ማለዳ ከምንጮች የሠማች ሲሆን፣ መጀመሪያ የነበረው ክፍያ ከላይ ከተጠቀሰው ያነሰ ነበር ተብሏል። አንድ ከክልሉ ውጭ የሚገኝ ሠው ትግራይ ለሚገኝ ቤተሰቡ ገንዘብ መላክ ቢፈልግ በቅድሚያ ገንዘቡን በሚያዘዋውሩት አካላት የባንክ ሒሳብ ቁጥር ማስገባት አለበት። የላኪውን ገንዘብ የሚቀበለው አዘዋዋሪ አካል አላማጣ በሚገኙ ተወካዮቹ አማካይነት ለተላከለት ሠው ያስረክባል።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገችው ጥረት፣ አላማጣ የሚገኙ ጥሬ ብር አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ አከማችተው በሺሕ ለሚቆጠሩ ሠዎች በክፍያ እያዘዋወሩ ነው። ገንዘብ የተላከላቸው ሠዎች ገንዘቡን የሚወስዱት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አላማጣ ተጉዘው ሲሆን፣ ወደ ከተማው ለመጓዝ የተገደዱትም ከሌሎች አካባቢዎች ገንዘብ ለማስላክ የኔትዎርክ አገልግሎት የሚገኘው እና የጥሬ ገንዘብ ዝውውሩ የሚከናወነው አላማጣ በመሆኑ ነው።
የጥሬ ገንዘብ ዝውውሩ የተጀመረው በክልሉ የሚገኙ ሠዎች የኔትወርክ አግልግሎት ለማግኘት ወደ አላማጣ እየተጓዙ ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ከጀመሩ በኋላ ነው። ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከጥር 2013 እስከ ጥር 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ በትግራይ ክልል ከቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው ለተነጣጠሉ 41 ሺሕ 326 ሰዎች ነጻ የስልክ ማስደወል አገልግሎት መሥጠቱን በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል።
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014



