ጎራ መርጦ ከመሰለፍ እንቆጠብ!

0
584

ዓለማችን በርካታ የተቀዛቀዙ ጦርነቶችን አልፋ አሁን ላይ የተሟሟቀ ጦርነት ውስጥ የገባችበት ጊዜ ላይ እንኛለን። ቀዝቃዛው ጦርነት ይባል የነበረውና ድሃ አገሮች በኃያላኑ አስታጣቂነት ጎራ ለይተው በስፋት ይጋደሉ የነበረበት ሒደት አሁንም ከመጋረጃ ጀርባ ቢቀጥልም፣ በይፋ እንደቀደመው ጊዜ ስለማያደርጉት ያን ያህል የሕዝቡን ትኩረት አይስብም። የኃያላኑ ዜጎች ሳይገደሉም ሆነ ሳይገዳደሉ የሚያስታጥቋቸው ጎረቤታማቾች ሆኑ ወንድማማቾች ምርኮ እየተመላለሱ ይተላለቁ ነበር።

የዓለማችንን ነባራዊ ኹኔታ የቀየረው የቻይና መምጣት ቢሆንም፣ ለቀዝቃው ጦርነት መቆም ምክንያት የሆነው የምሥራቁ ጎራ ድክመት በቅርቡ ስለቀረ አሁንም ተመልሶ ቀዝቃዛው ጦርነት እሳት ላይ የተጣደ ይመስላል። በዚህ የብረት ምጣድ ላይ ለመብሰልም ሆነ ለማረር የሚጣዱ አገራት መኖራቸው የማይቀር ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን እሳቱ አግኝቷት እንዳትበስልም ሆነ እንዳታር ከሌሎቹ በእሳቱ ከከሰሉ ዜጎቿ ልንማር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ራሺያ ዩክሬንን ወረረች እየተባለ ጉዳዩን ሲያጦዙት መመልከት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሆነ ቀናት ተቆጥረዋል። ለምን ወረረች? ምን አድርጋት ነው? ከማለት ይልቅ፣ ከመሬት ተነስታ እንደወረረች በማስመሰል የምዕራቡ ጎራ ደጋፊና ኮናኝ ፍለጋ ሲማትር ይታያል። አድርባይ እንደሚባሉ የአገራችን ካድሬዎች አንዳንድ አገራት በበሉበት ሲጮሁም መስማት አዲስ ነገር አይደለም።

በእንዲህ ዓይነት ዋልታ በሚረገጥበት ጉዳይ ፖለቲከኞች ዙሪያቸውን በጥሞና ዓይተው የድጋፍም ሆነ የነቀፌታ አስተያየቶችን ከመስጠት ተቆጥበው መታየት ይኖርባቸዋል። እነሱ ገለልተኛ በመሆናቸው አገር ትጠቀማለች። ደርሶ ለማንም አጫፋሪ በመሆን የሚያመጡት ጉዳት የከፋ ነው የሚሆነው። ማጭድ የማይዋሰው ሆድ ለባሰው ብቻ ሳይሆን ሆድ ላስባሰም ጭምር መሆኑን ወቅታዊውን ኹኔታ በመረዳት ፖለቲከኞቻችን ሊያስተውሉት ግድ ይላል።

ዓለም ጎራ ለይቶ ሊጠፋፋ ጫፍ ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ በኹለቱም ወገን የሚናቅ አካል ደርሶ የአንደኛው ደጋፊ ነኝ ብሎ ሌላውን ለመጉዳት መሞከሩ፣ ለሌላው ማስፈራሪያ እንዲሆን የመጀመሪያው የጥፋት ገፈት ቀማሽ ያደርገዋል እንጂ፣ ከጥቅም ተጋሪ እንደማያደርገው በኹለቱም የዓለም ጦርነቶች ከኹለቱም ጎራ ተሰልፈው መከራን በራሳቸው ላይ ካመጡት ድሃ የአፍሪካ አገራት መማር ይቻላል።

ኃያላኑ በጥቅም ተጣሉ እንጂ ለድሃና ለተበደለ እንቁም ብለው ፉክክር የገቡ ባለመሆናቸው፣ እኛን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት ሊያስቡበት በተገባ ነበር። አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ አንዳንድ አገራት አንዱን ወገን ለመኮነን የተጣደፉበት ፍጥነት ከዚህ ቀደም አንዲህ ዓይነት በጉልበት የተደረገ ነገር ያልነበረ አስመስለውታል። ኢትዮጵያ በነፈሰበት ነፍሳ መድረሻው ከማይታወቅበት መሬት ላይ ከማረፍ አስቀድማ የትም ከማያላትማት አለት ጋር ተጣብቃ መቆየት እንደሚገባት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች። ከባለፉት የዓለም ጦርነቶችም ሆነ ከቀዝቃዛው ጦርነት የምንማረው ነገር ቢኖር የጉልበተኞች ፍትጊያ የሚጎዳው መሬት ያለውን ነው።

ሰርቢያዎች ይደጋግሙታል ከሚባል ብሒል፣ እኛ የእነሱ ዓይነት አዘቅት ውስጥ ከመግባታችን በፊት ልንማርበት ይገባል። ከብዙ ዓመታት ጦርነት በኋላ የተረዱት ነገር ቢኖር ከጦርነት በፊት የአንድ አገር ዜጎች የሚኖራቸውን የውጊያ ተሳትፎ ነው። እኛም አገር በግላጭ እንዳየነው ዜጎች ከጦርነት በፊት እንደየደረጃቸው የተለያየ ተግባርን ያከናውናሉ።

ፖለቲከኞች “ዝመቱ፣ አገር አድኑ” እያሉ ሥልጣናቸውን አድነው ገዢነታቸውን ለማስቀጠል ሕዝብ በሚከፍለው ዕዳም ሆነ በልመና ያገኙትን የጦር መሣሪያ ተማጽነውም ጭምር እየጎተጎቱ ድሃውን ያስታጥቃሉ። እነሱ አቅሙ ስለማይኖራቸውም ባለሃብቱ ድሎቱ እንዳይቀንስበት ንብረቱንም እንዳያጣ አስፈራርተውም ሆነ አግባብተው፣ ስንቅ ከቻሉም ትጥቅ ለድሃው እንዲያቀብልና በአገር ሥም ሀብቱን እንዲያስጠብቅ ያስደርጉታል። እነዚህ ኹለቱ በአንዳንድ አገራት ቦታ እየተቀያየሩም ሆነ እየተፈራረቁ በመተጋገዝ ድሃውን ይጠቀማሉ። አማራጭ የሌለውና ለአገር ነው ሲባል አምኖ ሕይወቱን ለመስጠት ከጥንትም የማያመነታው ድሃው ግን፣ ጦር ሜዳ ዘምቶ፣ ውድ የምትባል ግን ለገዢዎቹ እንደርካሽ የምትታይ ፣ሕይወቱን እንዲሰጥ ይጋበዛል ወይም ይገደዳል።

ጦርነቱ ካበቃ ወይም ውጊያው ከቆመ በኋላ ግን ነገሮች ይቀያራሉ። ፖለቲከኞች ላተረፋቸው ለድሃው የሽንገላ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ያስታጠቁት መሣሪያ አፈሙዙ ወደእነሱ እንዳይዞር ብለው በግድ መሰብሰብ ይጀምራሉ። ባለሀብቱም እንደወትሮው አጋዥ በመሆን በሀብቱ ላይ ሀብት ለመጨመር ከጎናቸው ይሰለፋል። ሕይወቱን የሠጠው ድሃው ግን ዞር ብሎ የሚያየው አንደሌለ ተረድቶ፣ አስከሬኑ ያረፈበትን ፍለጋ ቤተሰቡ ያለረዳት እንደሚለፉም በንጽጽር በማስቀመጥ ልዩነቱን ከጊዜው መለዋወጥ ጋር እያፈራረቁ ቁልጭ አድርገው ገሀዱን ዓለም ያሳዩታል።

ይህ በእኛም አገር በተካሄደው ጦርነት የታየ ቢሆንም፣ ከጭብጣችን ጋር የሚገናኘው እኛም የሀብታም አገራት ጥይት ማብረጃ ሆነን የወደቅንበትን ፍለጋ እንዳንማስን ለማስገንዘብ ነው። ምዕራባውያኑ የምሥራቁን ጎራ ያልኮነነ ጠላት እንደሆነ በመንገር እያንዳንዱ ዜጋቸው በያለበት ለማሳመን እየጣረ እንደሆነ የሚታይ ሐቅ ነው። በስፖርታዊም ሆነ በሥነ-ጥበቡ ዘርፍ ያሉ ታዋቂ ሠዎችን ጭምር ያሳተፈ የመፈራረጅና የማግለል ፖለቲካም ከጀመሩ ሠንብተዋል።

ጥቁሮች እንደሠው ሳይቆጠሩ የመጨረሻ ደረጃ ተሠጥቷቸው ከሞት እንዳያመልጡ እየተደረጉ እያየ፣ አድራጊዎቹን ደግፎ ለመወዳጀት የሚሞክር አፍሪካ አገርን እንደማየት የሚያሳፍር ነገር የለም። አጀማመሩ ጥሩ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ምሳሌ የነፃነትም ተምሳሌት እንደመሆኗ፣ እንዲህ ዓይነት ቅሌት ውስጥ ፖለቲከኞቿ እንዳይከቷት አዲስ ማለዳ ታስጠነቅቃለች። “ጥቁር ነህ” ተብሎ ዜጋው ፍዳን አንዲጋፈጥ የተደረገበት አገር መንግሥት፣ በዳዩን መኮነን ሲገባው ሕሊና ለሌለው ባለሕሊና ለመምሰል መሞከሩ ያስንቀዋል እንጂ አያስከብረውም፤ አይጠቅመውምም።

በሌላ በኩል፣ አፍሪካውያን ኑና ያለምንም መስፈርት ተቀላቀሉን የሚለው የምሥራቁ ጎራም ጥሪ ዝም ተብሎ በአድናቆት መታየት የለበትም። በጭንቁ ሰዓት ብቻ የሚያስታውስ ወዳጅ ነው ሊባል ስለማይችል፣ ለምን ለአፍሪካ ብቻ የሞት ግብዣ ይቀርባል ተብሎ መጠየቅ አለበት። ሉዓላዊነትም ሆነ ክብር አቻ ለአቻ ሲሆን እንጂ፣ በገንዘብ ቢለካማ በአድዋም ጦርነት ባልተካፈልን ለድልም ባልበቃን።

ከአፄ ምኒልክ ታሪክ የአሁኖቹ ገዢዎች መማር ያለባቸው አንድ ዋና ጉዳይ እንዳለ አዲስ ማለዳ ማሳወቅ ትፈልጋለች። ለወራሻቸው ለልጅ ኢያሱ ቃል እንዳስገቡት የሚነገረው ይህ ጉዳይ ማንን ወዳጅ ማድረግ እንደሚገባና ማንን ማቅረብ እንደማይጠቅም ያሳወቁበትንና ለክብር ያበቃቸውን መንገድ ነው። የቅኝ ገዢ መንፈስ ያለባቸውን መስፋፋትም ሆነ ሥነ-ልቦናቸውን በሌላ ላይ ለመጫን ከሚፈልጉ፣ በተለይ በቅኝ ግዛታቸው ከተጎራበቱን ጋር መቀራረብ እንደማይጠቅም ተናግረዋል ይባላል። እኩል ፊት እያሳዩዋቸው፣ አንዱ ከአንዱ በእሳቸው ፊት የበለጠ ሞገስን ለማግኝት ሲል ኹል ጊዜ አገርን እንዲጠቅም ማስደረግ እንጂ፣ ወደ አንዱ ጎራ መጠቃለል የሌላው ጠላት መሆን ብቻ ሳይሆን ብቸኛ ወዳጁ ያደረገን ወገንም “የትም አይሄዱም” በሚል ዕሳቤ መጥቀም ሳይሆን መጠቀሚያ ያደርገናል በሚል ነው።

እያስተያዩ የጋራ ጠላቶችን እርስ በርስ ማጣላቱን ፈጣሪ ባይወደውም፣ ወዳጅ ማድረግ ያለብን ገለልተኛ ሆነው መኖርን ከሚመርጡ ጋር እንደሆነ ከአማካሪ አመራረጣቸው መማር እንችላለን። ከእሳቸው ለመማር ባለመቻሉ ግን ጠላቶቻችን ጎራ አስለይተው ለማጋደል ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። የሰገሌውንም ሆነ የቅርቦቹን የእርስ በርስ ጦርነቶችን አንስተን ማን ማንን ያስታጥቅ እንደነበር መመልከቱ ይበቃል።

ኢትዮጵያ የቃልኪዳን አገር ናት እየተባለ ቢነገርም አብዛኞቻችን ነገሥታቱ ከፈጣሪ ጋር የገቡት ኪዳን ምን እንደሆነም ሆነ፣ ከፈረሰ ምን እንደሚከተል አናውቅም። ለኢትዮጵያ ተብሎ የተነገረ ነገር የለም ብሎ አብዛኛው በሚያምንበት በዚህ ዘመን፣ ይህንን ለኃይማኖተኞቹ እንተወውና እንደዜጋ ምን ይጠበቅብናል? መንግስትስ ምን ማድረግ አለበት? በሚለው ላይ ማተኮሩ ያስፈልጋል።

ሌባ የሠረቀውን ለመካፈል ሲጣላ፣ ተሠራቂው መጥቶ ሊያስማማቸው እንደማይችል ልንረዳ ይገባል። ፀባቸውን ሰምቶ ፖሊስ ቢደርስም ለአንዱ ለተሠራቂውም ቢሆን መወገን ስለማይጠበቅበት፣ ዕቃውን ማስመለስ ሳይሆን ለሌላውም መማሪያ እንዲሆን ወደ ፈራጅ መውሰድ ግዴታው ይሆናል። ስለዚህም፣ መንግሥት ልዕልናቸውን ከሌላው ነጥቀው ለመብለጥ የሚፈልጉ አካላትን መርጦ መደገፉ ጸቡን ከማራገብና ሌላውም ተጨምሮበት እንዲስፋፋ ስለሚያደርገው በዝምታው ቢገፋበት ይሻላል። እንደአዲስ ማለዳ ዕምነት ኃያላኑ እርስበርስ እየተዋወቁ እኛ ደርሰን ማስተዋወቁ ስለማይጠቅመን ገለልተኛ ኾኖ መቆየቱ ከጥፋትም ይጠብቀናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here