በዜጎች መፈናቀል ጉዳይ ላይ የሰፈነው ዝምታ

0
548

የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ መረጃ ከባለሥልጣናት ወደ ሕዝቡ የሚቀርብበት መንገድ አደጋውን ለመቆጣጠር ሁነኛ መንገድ እንደሆነ የሚናገሩት ቤተልሔም ነጋሽ በዚህ መጣጥፋቸው በጎንደር ግጭት ወቅት የተፈናቃዮች ዜና የተነገረበትን ዐውድ እንደምሳሌ አቅርበውታል።

 

 

በጎንደር ደንቢያ ወረዳ በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ በተፈጠረ ግጭት 465 ቤቶች ወድመው 6040 ሰዎች ሲፈናቀሉ ነው በቅርብ የሚባለው ቀውስ የመጣው። በበኩሌ ስለ ክስተቱ ዝርዝር መረጃ ሊኖረኝ የቻለው ለኹለት ዐሥርት ዓመታት ያህል ከትምህርት ቤት ጀምሮ የማውቀው፣ በመልካም ምግባሩና በጥረቱ ከሰሜን ጎንደር ገጠር ከተማ ወጥቶ ከፍተኛው የትምህርት ደረጃ ላይ ደርሶ በዩናይትድ ኪንግደም የዩኒቨርሲቲ ሥራ ላይ ያለው፣ በዘርፉም በዓለም ከሚጠቀሱ ምሁራን አንዱ የሆነው ወዳጄ ቤተሰብ፣ በዕድሜ የገፉ እናትና አባት እንደዋዛ ቤታቸው አመድ ሲሆን ጥለውት ሲወጡ፣ አሮጊት እናቱ ከሐዘን ብዛት ከዝምታ ውጪ መናገር አለመቻላቸውን ስሰማ ነው።

በወቅቱ አውሮፓ ስለነበርኩ ስልክ ደውዬ ከማፅናናት የተሻለ ምንም የማደርገው አልነበረኝም። ኢትዮጵያ ያሉ ወዳጅ ጓደኞቹ ማሳና ቤታቸው ተቃጥሎ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለው ጎንደር ከተማ የገቡ ቤተሰቦቹን ደግፈውለት ነበርና መፅናኛ ሆኖት ነበር። ለእኔ ግን በወቅቱ የመፈናቀሉ ዜና ከዜና በላይ ሆኖ ግዘፍ ነስቶ መጥቶ “በራሴም ቤተሰብ ሊደርስ ይችላል” ያስባለኝ ነበር።

ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጀምሮ ከሱማሌ ክልል ከቡራዩ ብጥብጥና ከጎንደር በታየው የሰላም መታጣት በድምሩ ከኹለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል። ጓደኞቼን ጨምሮ በጎ ፈቃደኞች ለጉጂ ተፈናቃዮች አልባሳትና ቁሳቁስ ሲያሰባስቡ ከመሳተፍ፣ በሆነው ከማዘንና በቁጥሩ ብዛት ከመደንገጥ ውጪ ተጎጂዎቹ እንደ ወዳጄ ቤተሰብ ፊትና ታሪክ ይዘው አልመጡልኝም። የመገናኛ ብዙኃኖቻችንም በሌሎች “አስቸኳይ” ጉዳዮች ተጠምደው በካምፖች ተገኝተው ተጎጂዎቹ ያሉበትን ኹኔታ አልቃኙም። በተለይ ከአዲስ አበባ ርቀው ያሉት ተፈናቃዮች የዕለት ዕርዳታ ማግኘታቸውን፣ ሌላው ማኅበረሰብ ድጋፍ ማድረግ ስለሚችልበት ኹኔታና መልሶ ለማቋቋም ስለሚጠይቀው ሥራ አይዘግቡም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ስለእነኝህ ግጭቶች በተከሰቱበት ወቅት እንኳን መግለጫ ሲሰጡ አይታዩም። ተናግሮ ማረጋጋት፣ ጥፋተኛ ካለም ጉዳዩን አጣርቶ ለመፍትሔ የሚሆን መረጃ አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋም፣ ሕዝብን ማወያየት፣ ሌላም ሌላም ሥራ በወቅቱ ካልተሠራ መፈናቀሉና መበደሉ ለግጭትና ለሰላም መታጣት ሊዳርግ የሚችል ብዙ የተዳፈነ ብሶት እንደሚፈጥር ግልጽ ነው።

ወቅታዊ ወደሆነው የአማራ ክልሉ ግጭት ስንመጣ ቀደም ሲል በታኅሣሥ ወር ከሰሜን ጎንደር ደንቢያ ወረዳና አካባቢው ባሳለፈው ሳምንት ደግሞ ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተከሰተ የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ90 ሺሕ በላይ መድረሱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።
በአካባቢው የተከሰተውን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ እስካሁን በተከታታይ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ናቸው። ባለኝ መረጃ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ መግለጫ መስጠታቸውም ሆነ በቦታው ተገኝተው ተፈናቃዮችን ስለመጎብኘታቸው አልተዘገበም። ይልቁንም በተለይ በመጀመሪያ አካባቢ ከላይ በጠቀስኳቸው በማውቀው ቤተሰብ ጭምር እንደተረጋገጠው መንግሥት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጭምር ለመስጠት እጅግ ዘግይቶ እንደነበር ነው።

 

የፖለቲካ ትርክትና የመከፋፈል ዘመቻ ውጤት በመሆኑ ይቅርታ መጠየቅም፣ ኃላፊነት መውሰድም፣ በተለየ የሚታይ አስተዋፅዖ ያለው ካለም እንዲጠየቅ ማድረግ ችግሩ እንዳይመለስ ያደርጋል። ካልሆነ ግን ከላይ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ እንዳሉት የማይታዩ ሥም አይጠሬ “የጥፋት ኃይሎች” ላይ ችግሩን መለጠፍ ካልተውን መፍትሔ አይመጣም።

 

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ግጭቱ ያገረሸው “በኹለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ዐቅደው በሚሠሩ ኃይሎች አማካኝነት” የተፈጠረ ነው።

“የክልሉ መንግሥት በንፁኃን ዜጎች ላይ በደረሰው የሕይወት መጥፋትና ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፥ ጉዳት ለደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው” ብለዋል። በበኩሌ ካለው ቀውስና ከችግሩ ስፋት አንፃር የክልሉ ፕሬዚዳንት ወጥተው የሆነ ነገር ማለት ነበረባቸው ባይ ነኝ። የመጀመሪውና ታኅሣሥ ላይ ተከስቶ የነበረው መፈናቀል ከተከሰተስ በኋላ የሕዝብ ንቅናቄና የተግባቦት ሥራ አልተሠራም? የችግሩ ሥረ መሠረት ተጠንቶ ይህም ለሕዝብ ተገልጾ ዘላቂ መፍትሔ እንዲደረግለት ለምን አልሆነም? ሌላ ጥያቄ ነው።

መረጃዎች በሕዝብ ግንኙነቶች ቢሮ በኩል መምጣታቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ይህን ያህል ተደማምሮ ብዙ ሰዎችን ለችግር ከመዳረጉና ከአሳሳቢነቱም አንፃር ምናልባት የክልሉ ፕሬዚዳንት በተከታታይ መልዕክት የሚስተላልፉበት፣ ሕዝቡንም የሚያረጋጉበት ሒደት መኖር ነበረበት። በተለይ ያሁኑ ችግር በድንገት የመጣ ሳይሆን ቀደም ሲል የነበረውና የአሁኑ የክልሉ አመራር ላይ ያሉ ኃላፊዎች ጭምር ሥልጣን ላይ በነበሩት ለዓመታት በነበረ የፖለቲካ ትርክትና የመከፋፈል ዘመቻ ውጤት በመሆኑ ይቅርታ መጠየቅም፣ ኃላፊነት መውሰድም፣ በተለየ የሚታይ አስተዋፅዖ ያለው ካለም እንዲጠየቅ ማድረግ ችግሩ እንዳይመለስ ያደርጋል። ካልሆነ ግን ከላይ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ እንዳሉት የማይታዩ ሥም አይጠሬ “የጥፋት ኃይሎች” ላይ ችግሩን መለጠፍ ካልተውን መፍትሔ አይመጣም።

እሳት አጥፊ አዘጋገብ
በዚህ በዐሠር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ለጉዳት በተዳረጉበት ክስተት ላይ ሚዲያ ምን ብሏል የሚለውን ለማየት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ጉግል ላይ ፍለጋ ሳደርግ በቅድሚያ “አብቁተ በአማራ ክልል ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የ25 ሚሊየን ብር ድጋፍ ሰጠ” የሚል የካቲት 11 የወጣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ኦንላይን ገጽ ዜና ተቀበለኝ።

ሌላው ጥር 30 ቀን የወጣ ዜና “በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ” ይላል። የዚህ ዜና ክስተት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ በአማራ እና ቅማንት ብሔረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ የሚል ነበር።

የክልሉ ይፋዊ ድምፅ ለመባል የሚችለውና በክልሉ የሚከናወኑ ክስተቶችን በዝርዝር በመዘገብ ቀዳሚ የሆነው የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ተፈናቃዮችን ለመርዳት እየተደረገ ያለውን ጥረትና የገንዘብ ማሰባሰብ ሒደቱን የተመለከቱ ዜናዎችን በተከታታይ አውጥቷል። ከዚህ ባለፈ ተለውጧል የሚባለው የድሮው ሚዲያ አዘጋገብ አልተለወጠም የሚያሰኘው ዘገባ “በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ተገቢ መሆኑን የሕግ ምሁር ተናገሩ” የሚለው ነው። ክልሉ ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ማመኑ እንዳለ ሆኖ ግጭት በተነሳ ቁጥር ፌደራል ፖሊስ ጣልቃ እየገባ ይቻላል? በዘላቂነትስ በየክልሉ የመከላከያ ሠራዊት ተከፋፈፍሎ ሰፍሮ እየኖረ ነው ሰላም የሚመጣው የሚለው ትንሽ አሳሳቢ ነው።

አንድ ሌላ ከኢትዮጵያ ውጪ ያለ የዳያስፖራ የዜና ምንጭ በበኩሉ የካቲት 11 ባወጣው ዘገባ ግሎባል አሊያንስ የተሰኘ ተቋም 20 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ጠቁሟል። በተጨማሪም አንድ የእንግሊዝኛ ዜና በምዕራባዊና ማዕከላዊ ጎንደር መከላከያ ሠራዊት መግባቱን የሚያትት ዜና ሠርቷል።

በተረፈ ሌሎች የኅትመት ውጤቶች ካለፈው ታኅሣሥ ጀምሮ የነበረውን የሰሜን ጎንደር የበርካታ ዜጎች የመፈናቀል ዜና ትኩረት ሰጥተው አልዘገቡትም ማለት ይቻላል።
“እንደ ሰጎን አንገትን ከአሸዋ ውስጥ ቀብሮ ችግሩ በኖ ይጠፋል ብሎ ተስፋ የማድረግ፣ እስኪያልፍ የመደበቅ ዘመን አልፏል” ይላል በቀውስ ወቅት መደረግ ያለበትን የተግባቦት ሒደትና እና ቶሎ ቶሎ መረጃ የመስጠት አስፈላጊነት የሚያትት አንድ ጽሑፍ። ጽሑፉ በአብዛኛው ተቋማት ችግር ውስጥ በሚገቡ ጊዜ ወቅታዊ መረጃ ባለመስጠታቸው የገቡበትን ጣጣ ሲተነትን ብዙ ዋጋ እንደከፈሉበትም ጭምር በማተት ነው።

እኛም በተለይ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት በቀረው የለውጥ አየር ወቅት የተግባቦትና መረጃ የመስጠት ሒደት እንደሚቀየር ሰምተን አምነን ነበር። “በግልጽ እንጂ በድብቅ የሚሆን የለም” ከተባልን በኋላ “የምንናገረው፣ መረጃም የምንሰጠው እኛ በፈለግነው አጀንዳ ላይ ነው” ማለት የሚመስል ዝምታ በተለይ በተጎጂዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ የሚፈጥር ነው።

እንደኛ አገር ኹኔታ የተፈጥሮም ባይሆን ሰው ሰራሽ ቀውስ ሲከተል ሰዎች ሲፈናቀሉ ተከታታይ የመረጃ መስጠት ሥራ ማከናወን ተጎጂዎችን ከማፅናናት ባሻገር ድጋፍ ለመስጠት የሚሹ አካላትን ድጋፍ ለማግኘትና በተሻለ ኹኔታ ለማስተባበር በቶሎም ከችግሩ እንዲያገግሙ ለማድረግ ይረዳል። ተጎጂዎችን ጨምሮ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተስፋ መቁረጥ እንዳይሰማቸውና ግራ ተጋብተው በግብታዊነት አደጋን የሚባብስ ተግባር ላይ እንዳይሠማሩ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ጥሩ አመራርና በቂ ቅድመ ዝግጅት፣ የአሠራር መዋቅር ይጠይቃል። ድሮ ያልነበረ የተቀናጀ አሠራርና ሥራን በአግባቡ የመምራት መረጃዎችንም በግልጽና በወቅቱ የመስጠት ባሕል በድንገት ችግር ሲከሰት አይመጣም።

የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ ቀውሶች ተፈጥሮንና የማኅበረሰብን አኗኗር ስለሚያዛቡ ለመሪዎች አስቸጋሪ ኹኔታን ይፈጥራሉ። መንግሥት ያስቀመጣቸው የማስተዳደር ስርዓቶችና የሕግ የበላይነትም ይጣሳሉ። በምዕራቡ ዓለም መሪዎችና ፖለቲከኞች አንዳንድ ክስተቶችንና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለፖለቲካ ዓላማ ለማዋል በጉዳቱ ሥፍራ ቀድሞ በመገኘት በመታየት ለብዙኃን መገናኛ ሽፋን ለማዋል ሲሯሯጡ ይታያሉ ይወቀሱበታልም። የእኛዎቹ ምናልባት ከላይ እንደተጠቀሰው እንደ ሰጎኗ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። ቆይ ፀጥ ልበልና ልየው፣ ተደብቄ ላሳልፈው ዓይነት። ይኼ በተለይ ፍትሐዊ ምርጫና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ባሉበት የሚታሰብ አይደለም፤ ነገ በምርጫ ካርድ መወገድን ሊያመጣ ይችላልና። ዛሬ ያለህን ሥልጣንና ተሰሚነት ተጠቅመህ ድጋፍ እንዳገኝ ካላደረክ ያንተ መሪነት ምኔ ነው መባልም አለና።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here