ጋቢና እና ገበና

0
686

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ሚስታቸውን እቴጌ ተዋበች አሊን አብዝተው ይወዱ ነበር። ተዋበች አሊ በበኩላቸው ከመልክ መልክ ያደላቸው፤ በጥበብና ብልሃትም የተደነቁ ሴት ነበሩ። ታድያ አንድ ቀን ተዋቡ ባለቤታቸውን ቆጣ ሲሉ የአጼ ቴዎድሮስ የቀኝ እጅና ወዳጅ ገብርዬ ይመለከቱና የተዋቡ ቁጣ ልክ እንዳይደለ ይናገራሉ።

አጼ ቴዎድሮስ ታድያ ቀበል አድርገው «ገብርዬ! አንተ የምታውቀኝ ታጥቄ፤ እርሷ የምታውቀኝ አውልቄ» አሉ ይባላል። ነገሩን ቃል በቃል ያገኘሁት አይመስለኝም፤ ብቻ ግን በዚህ ንግግር ውስጥ አጼ ቴዎድሮስ ከሚስታቸው የተደበቀ ገበና እንደሌለ ለማጠየቅ እንዲያ እንዳሉ እናውቃለን።

ይህን ደስ የሚያሰኝ ታሪክ እንደመነሻ መጥቀሴ የዓለማችን ብዙ ገበና ያለው ሴቶች ጋር እስደሚመስለኝ ለማንሳት ነው። በምናውቀው ታሪክ በጭካኔ ተቀናቃኝ ከሌለው ሂትለር እስከ መብት ተሟጋቹና መልካሙ ሰው ማንዴላ ድረስ፤ ታሪካቸው በእናቶቻቸው፣ በእህቶቻቸውና በሚስቶቻቸው በሚገባ ይታወቃል። ብቻ እወቁልኝ! ነገሩን ፉክክር ለማድረግ አይደለም። ማለትም የእነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አባት ወይም ወንድም አልያም ወንድ ልጅ ስለእነርሱ ምንም አያውቁም ለማለት አይደለም።
ደግሞ ወዲህ ወደ ነገሬ ልግባ፤ በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥትም ይሁን የግል ተቋማት የሚታየው ነገር ይገርመኛል። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ጋቢናቸውን አሳምረው፣ ከረባታቸውን አስረው፣ ዶክተር እየተባሉ እጅ የሚነሱ ግን የግፍና የጥፋት ገበናቸው ሴቶች ጋር የተቀመጠ ‘ትልቅ’ ሰዎችን አስባለሁ። ‹‹ምን እያሰቡ ነው?››

ወደ መድረክ ሲወጡ ያሳፈሯት፣ ክብሯን የነኩባት፣ ሊጠቀሙባት የፈለጉና ያታለሏት ሴት ከሚያጨበጭብላቸው ሕዝብ መካከል ናት። ገበናቸውን እንደምትይዝ እንጂ እንደማታወጣ ስለሚያውቁ አያፍሩም። ያማረ ጋቢና ይዘው በቆሸሸ ገበናቸው ብዙዎች ፊት ይቆማሉ። ያ ጉድፋቸው የሚታየው ለዛች ሴት ብቻ ነው።
«ሴቷስ ለምን ዝም ትላለች?» ብዬም አጠይቃለሁ። እንደው ሁሉም ይወራ ቢባልና ቢነገር ስንት ባለሥልጣንና ሀብታም ነኝ ባይ ከነክብሩ የሚቆይ ይመስላችኋል? ስንት ሰውንስ በአንቱታ ይዘን እንዘልቅ ይሆን? ሴቷ ግን አትናገርም። ብትናገር እንኳ ሰሚው ሌላ ታሪክ ፈጥሮ ይለጥፍባታል። ብትናገርና ሁሉም ነገሩን ቢያውቅ እንኳ «እርሳቸውማ ምርጥ ሰው ነበሩ! ሴት ላይ ግን አስቸጋሪ ናቸው» እየተባሉ እንደተራ ነገር ይወራላቸዋል።

በባሕር ማዶ እንዲህ ያሉ የፆታዊ ጥቃት፣ ትንኮሳና በደሎች በአደባባይ ይወራሉ። በፊልሙ ዓለም አክብሮትና ዓለም ዐቀፍ ዝና ያገኙ ሰዎችም ሳይቀሩ እንዲህ ባለው ቅሌት ውስጥ ክብራቸው ወርዶና ተፈርዶባቸው አንገታቸውን ሲደፉ አይተናል። ይህ ጊዜም ወደኛ የሚመጣ ከሆነና እስኪመጣ ድረስ፤ ሰዎች ሆይ! እንደጋቢናችን ለገበናችንም እንጠንቀቅ።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here