4 ወራትን ያስቆጠረው የሕንዳዉያን እገታ መቋጫ አላገኘም

0
745

ከህዳር 2011 ጀምሮ በእገታ ላይ የሚገኙት ሕንዳዊያን ጉዳይ አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱን ምንጮች አስታወቁ። ‘አይ ኤል ኤፍ ኤስ’ በተሰኘ የሕንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ኢትዮጵያዊያን ኩባንያው ለወራት ደሞዛችንን አለከፈለንም በሚል አራት ህንዳዊያን ሠራተኞችን በእገታ መያዛቸው የሚታወቅ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሕንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደረገ ሲሆን፤ የሕንድ ኤግዚም ባንክም በጥር 3/2011 ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክፍያ እንዲፈፅም ደብዳቤ ቢፅፍም እስካሁን ክፍያም ሳይከፈል፤ ታጋቾችም ሳይለቀቁ ቀርተዋል። በኩባንያውና በሠራተኞች መካከል በተደረገ ድርድርም በሠራተኞች ተጠይቆ የነበረው የ10 ወር የደሞዝ ጥያቄ ወደ አራት ወር ዝቅ ማለቱ ይታወሳል።

በድርጅቱ ውስጥ የ‘ፕላንቲንግና ኢኪዮፕመንት’ ሥራ ክፍል ኃላፊ እና የሠራተኞች ማኅበር ሰብሳቢ ኤርሚያስ ንጋቱ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው በቅርቡ አንድ የሕንድ ባለሀብት የታገቱት ሕንዳዊያንን ለማስለቀቅ በሠራተኞች እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠውን ክፍያ ለመክፈል መስማማታቸውን ገልፀዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ፣ የካቲት 15 ክፍያው እንደሚፈፀም መረጃው ቢኖራቸውም አዲስ ማለዳ ወደ ማተሚያ ቤት እስከገባችበት ድረስ ምንም ዓይነት ክፍያ አለመፈፀሙ ታውቋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰብሳቢው ሲናገሩ የታገቱት ሕንዳዊያን ጉዳይ በአገራቸው ትልቅ መነጋገሪያ እንደሆነና ባለሀብቱም ከዚህ በመነሳት ለመክፈል ፍላጎት እንዳሳዩ ተናግረው እስካሁን ለምን መክፈል እንዳልቻሉም ምስጢር እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ኤርሚያስ እንደገለፁት በእገታ ላይ ያሉት ሕንዳዊያን የገንዘብ ምንጫቸው እንደማይታወቅ ገልፀው፤ በየጊዜው ከባንክ ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርጉ እና የዕለት ተዕለት ውጪያቸውን እየሸፈኑ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሕንዳዊያኑ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም የማኅበሩ ሰብሳቢ ጨምረው ገልፀዋል።

ኩባንያው ከተጋረጠበት ኪሳራ ጋር ተያይዞ ደሞዛቸው ያልተከፈላቸው 207 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከዕለት ወደ ዕለት የኑሮን ጫና መሸከም እያቃታቸው እንደሆነ እና የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈንና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ በቀን ሥራ ላይ መሰማራታቸውን አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ዕትሟ ማስነበቧ ይታወቃል። ስለጉዳዩ ኤርሚያስ ንጋቱ ሲያብራሩ አሁንም ምንም የተለወጠ ነገር እንደሌለና በአካባቢውም ካለው ጠባብ የሥራ ዕድል የተነሳ የሠራተኞች ኑሮ አደጋ ላይ መውደቁን ተናግረዋል።

ኩባንያው በሥሩ ካሉት ተቋራጮች ጋር ባለው የፍርድ ቤት ክርክር ምክንያት በባንክ የሚገኝ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የዕግድ ትዕዛዝ የወጣበት መሆኑን ተከትሎ ለሠራተኞች ይከፍላል የሚለው ተስፋ እንደተሟጠጠ ለመረዳት ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here