ሰላም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በዘጠኝ ከተሞች በማክበር ላይ ይገኛል

0
721

ማክሰኞ የካቲት 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሰላም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን “የሴቶች እኩልነት ለነገ ብሩህ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 25 እስከ የካቲት 30 2014 ድረስ በዘጠኝ ከተሞች በማክበር ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሴቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ስኬቶችን የሚያከብር ዓለም አቀፍ ቀን መሆኑ ይታወቃል።

ቀኑ ለመጀመሪያ ጊዜም በኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን እና ስዊዘርላንድ እ.ኤ.አ በ1911 የተከበረ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም በ1996 “የኋላውን ማክበር፤ የወደፊቱን ማቀድ” በሚል መሪ ቃል በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። በዚህ ዓመትም 111ኛው የዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን እየተከበረ ይገኛል።

የ2022 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ንቅናቄ #BreakTheBias (አድሎአዊነትን እንስበር) የሚል ዘመቻን ያነገበ ሲሆን ሁሉም ሴት በአካባቢው፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታው ያለውን አድሎአዊነት ማላቀቅ እንደሚችል በተለያዩ ዘዴዎች ያሳየ ነው ተብሏል፡፡

በዓለም ለ111ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በመከበር ላይ ይገኛል።

ሰላም ኢትዮጵያም ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የሥርዓተ ፆታ ዘላቂ እኩልነትን ለማረጋገጥ ይህን ንቅናቄ መቀላቀሉን አስታውቋል።

ይህ ሰላም ኢትዮጵያ እያከናወነው የሚገኘውና ከየካቲት 25 እስከ የካቲት 30 ድረስ የሚቆየው ንቅናቄ ስለሴቶች እኩልነት ግንዛቤን ለማሳደግና የሴቶች ስኬቶችን ለማሳየት ያለመ ሲሆን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ዘጠኝ ክልል ከተሞች የሰርከስ፣ ድራማ፣ ሙዚቃ ና ስነጽሁፍን ፕሮግራሞችን ይዞ መቅረቡ ተገልጿል፡፡

ይህን ንቅናቄ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ድሬደዋ፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፣ ሀረር እና በአዲስ አበባ ከተሞች ላይ በሚገኙ በገበያ ማዕከሎች፣ በመዝናኛ ስፍራዎች፣ በሆቴሎችና በባህል አዳራሾች በሚከናወኑ ፕሮግራሞች በሴቶች ብቻ ደምቀው እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡

ሰላም ኢትዮጵያ ለ17 ዓመታት የኢትዮጵያን የባህል ዘርፍ ሲደግፍ የቆየ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፤ በዘጠኝ ክልሎች ቁልፍ ተዋናዮችን በማብቃት ዘርፉን በመደገፍ ይታወቃል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here